Get Mystery Box with random crypto!

ኦሾ እንዲህ ይላል:- ፖለቲከኛ የስነልቦናና የመንፈስ ታማሚ ነው። በአብዛኛው ፖለቲከኞች ጤናማ ተ | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

ኦሾ እንዲህ ይላል:-

ፖለቲከኛ የስነልቦናና የመንፈስ ታማሚ ነው። በአብዛኛው ፖለቲከኞች ጤናማ ተክለ ቁመና ይኖራቸዋል። አካላቸው እንከን አልባ ሲሆን ዋናው ሸክም የሚያርፍበት አእምሮአቸው ግን ህመምተኛ ነው። አእምሮአዊ ህመማቸው ሲበዛ ደሞ የመንፈስ ታማሚ ይሆናሉ። የህመሙ አይነት የዝቅተኝነት ( የበታችነት) ስሜት ወይም Inferiority complex የሚባለው አይነት ነው።

የስልጣን ጥማት ያለበት ማንም ሰው የበታችበት ስሜት ተጠቂ ነው። በውስጡ የሚሰማው ዋጋ ቢስነትና ከሌሎች ማነስ ብቻ ይሆናል። በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች እናንሳለን። ይህ ማለት ግን የበታችነት ስሜት ሊሰማን የግድ ነው ማለት አይደለም። ፖለቲካኛ ግን የበታችነት ደዌ ተጠቂ ነው። ራሱን ምጡቅ ከሆኑ የሰው ልጆች ጋር ሊያነጻጽር መሞከሩ የበታችነት እንዲሰማው ያደርገዋል። ራሳችሁን ከአንስታይንና ሲግመንድ ፍሩድ ጋር የምታፎካክሩ ከሆነ ዋጋ ቢስነትና ትንሽነት ሊሰማችሁ ይችላል።
ይህ የዋጋቢስነት ስሜት በሁለት መንገዶች ይወገዳል። አንዱ ሀይማኖት ሲሆን ሌላው ደግሞ ፖለቲካ ነው።
ፔለቲካ ይህን ደዌ ይደብቀዋል እንጂ አያጠፋውም። የህመሙ ተጠቂ በዚህ የበታችነት ስሜት የሚሰቃየው ሰው ፕሬዚዳንት ሊሆን ይችላል። የመሪነትን ወንበር መያዝ በውስጣዊ ማንነታችሁ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
ከሞራርጂ ዴሳይ ጋር ያጋጨኝ ይኸው ጉዳይ ነበር።በህንድ ከሚከበረው አመታዊ የሀይማኖቶች የጋራ ጉባኤ አስቀድሞ የጃይና መነኩሴው አቻርያ ቱልሲ ከጋበዛቸው ሀያ እንግዶች መካከል እኔና ዴሳይ ነበርንበት። ወቅቱ 1960 ነበር ። ተጋባዦች በቀጣይ የሚሳተፉትን ሀምሳ ሺ የሀይማኖት ተከታዮች በተመለከተ ለመወያየት ነበር ለቅድመ ትውውቅ የተጋበዝነው። ሆኖም ግን ከመጀመርያው ነበር ችግር የተፈጠረው።
የችግሩ መነሻ ደግሞ ጋባዣችን የሆነው ቱልሲ ከፍ ካለው መቀመጫ ላይ ሲቀመጥ ሀያችን ደግሞ መሬት ላይ ተቀመጥን። አቀማመጡን የተቃወመው ብቸኛ ሰው ሞራርጂ ዴሳይ ነበር። ከሀያዎቻችን መካከል ዴሳይ ብቸኛው ፖለቲከኛ ሲሆን ሌሎቻችን ከተለያዩ መስኮች ነበር የመጣነው።
አጠገቤ የተቀመጠው ዴሳይ ተቃውሞውን እንዲህ ሲል ለጋባዣችን አቻርያ ቱልሲ አሰማ።
"...እኛ እንግዶቹ መሬት ላይ ተቀምጠን አንተ ከፍ ያለውን ወንበር መያዝህ ተገቢ አይደለም። ስብሰባ እየመራህ ቢሆን ችግር የለውም። ነገር ግን ከሀያችን ከፍ ብለህ መቀመጥህ ምን አይነት ስነ ስርአት ነው?"

መነኩሴው ተደናገጡ። ከወንበራቸው ባይወርዱም በሀፍረት ተሸማቀዋል። ፖለቲከኛው ሞራርጂ ዴሳይ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የአቻርያ ቱልሲ ምክትል ነበር። የመነኩሴው አቀማመጥ ለውይይቱ አመቺነት ተብሎ መሆኑን በመጥቀስ ማንንም ዝቅ አድርጎ ለማየት አለመደረጉን ተናገረ።
ሞራርጂ ግን በቀላሉ የሚያቆም አልሆነም። "እዚህ ለተገኘነው በሙሉ አለቃችን አንተ አይደለህም። ለምን ከኛ ከፍ ብለህ ተቀመጥክ? ድርጊትህ ስርአት አልባ አይሆንም? በማለት ሲጠይቅ መነኩሴው ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም ተረበሽን።

" ከይቅርታ ጋር- እኔ ልመልስልህ?" በማለት ዴሳይን ጠየኩት።
"መልሱን ማወቅ እፈልጋለው- መልስልኝ" በማለት ሲፈቅድልኝ መናገር ጀመርኩ።

"በመጀመርያ እዚህ ብቻህን አይደለም የመጣኸው። ከአንተ ውጪ 19 እንግዶች ተገኝተናል። አንተን ብቸኛው ጠያቂ ያደረገህ ማነው?" በማለት ጠየኩትና ወደሌሎቹ ተጋባዦች ዞሬ "የመነኩሴው አቀማመጥ ላይ ተቃውሞ ያለው ሌላ ሰው ካለ እስኪ እጃችሁን አሳዩኝ" ስል ጠየኳቸው። አንዳቸውም አላሳዩኝም።

ከዛ ወደ ዴሳይ ዞሬ "በመነኩሴው አቀማመጥ ስሜቱ የተነካው ብቸኛ ሰው አንተ ነህ። በአስቸጋሪ የበታችነት ስሜት አረንቋ ውስጥ መሆንህን ያሳብቅብሀል።እንደ ዶ/ር ካታሪ ያሉ ምሁራን ፈጽሞ ቁብ ያልሰጡት ነገር አንተን ብቻ ነው ያስቀየመህ።
ከአቻርያ ቱልሲ በላይ ኮርኒሱ ላይ ምትኖረው ሸረሪት ትታይሀለች? ለመሆኑ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ መሆን የበላይ የሚያደርግ ይመስልሀል? እንግዲህ ስሜትህን የነካው ይሄ ነው። የህንድ የፋይናንስ ሚኒስቴር መሆን ያልፈወሰው ደዌ ውስጥህ አለ። አንድ ቀን የሀገራችን ጠ/ሚንስትር ለመሆን መፈለግህ አይቀርም" አልኩት።

በንግግሬ ተናደደ።"እብድ ነህ እያልከኝ ነው?" ሲል በቁጣ ጠየቀኝ

"አዎ" ስል መለስኩለት። "እነዚህ 18 ተሰብሳቢዎች ቅድም እጃቸውን አለማውጣታቸው ይህንኑ ያረጋግጥልሀል። የመነኩሴው ከፍ ብሎ መቀመጥ የረበሸው አንተን ብቻ ነው" ስል መለስኩለት።
"ለመሆኑመነኩሴው ቀድሞ ወንበሩ ላይ አስቀምጦህ ቢሆን ኖሮ መሬት ላይ ለተቀመጥነው ሌሎቻችን ክብር ስትል ተመሳሳይ ጥያቄ ታነሳ ነበር?" በማለት ጠየኩት።

"ፈጽሞ አስቤው አላውቅም ነበር። በርካታ ስብሰባዎች ስመራ ከፍ ያለ መድረክ ላይ ነው ምቀመጠው። ማንም ተሰብሳቢ ጥያቄውን አንስቶ አያውቅም።" በማለት መለሰልኝ።

"ጥያቄህ ለምን አቻርያ ቱልሲ ከፍ ያለ ቦታ ተቀመጠ የሚል አደለም። ያንተ ጥያቄ ለምን ከቱልሲ በታች ተቀመጥኩ የሚል ነው። የራስህን ህመም ወደ ሌላ ሰው አታጋባ።
" ምናልባት አንተ ብቻ ሳትሆን አቻርያ ቱልሲም የህመሙ ተጠቂ ይመስለኛል። በመነኩሴው ቦታ ብሆን ኖሮ መጀመርያ መድረኩ ላይ አልቀመጥም ነበር። ብቀመጥም ደግሞ ጥያቄ ስታነሳ ይቅርታ ጠይቄ እወርድ ነበር። ሆኖም ግን እንደምታየው አሁንም ከቦታው አልወረደም። ለጥያቄህ መልስ መስጠት ያቃተው ይመስላል። ከመነኩሴው ይልቅ እኔን ያሳሰበኝ የአንተ ሁኔታ ነው። በስልጣን ሚዛን እንዲሁም በበላይነትና በበታችነት የተሞላ ጭንቅላት ያላቸው ፖለቲከኞች ናቸው ።" በማለት ምላሽ ሰጠሁት።
በወቅቱ ዴሳይ ተናደደ። ላለፉት ሀያ አምስት አመታትም ቂም ያዘብኝ።


@Zephilosophy
@Zephilosophy