Get Mystery Box with random crypto!

እውነት ምንድነው? ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ ፀሀፊ ፦ አለማየሁ ገላጋይ በአንዳንድ መመዘኛዎች | ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ Philosophy

እውነት ምንድነው?

ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ
ፀሀፊ ፦ አለማየሁ ገላጋይ

በአንዳንድ መመዘኛዎች አብዛኛው ሰው እውነት ብሎ የተስማማበት ነገር ከሞላ ጐደል እውነትነት አለው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይሁንና ይሄ ብያኔ ከብዙ የእውነታ ማረጋገጫ መንገዶች አንዱ እንጂ የመጨረሻ ማጠቃለያው እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል፡፡ ስለዚህ አንተም ሆንክ የሀዲስ ኪዳኑ ጲላጦስ «እውነት ምንድር ነው?›› ስትሉ ለጠየቃችሁት የጓደኞችህ መደምደሚያ አርኪ ምላሽ አይሆንም።

ከሁሉም በፊት ውሸት እንድንናገር የሚገፋፉን ነገሮች ምንድን ናቸው ብለን መነሳት የእውነትን ተፈጥሮ መርምሮ ለማግኘት ይረዳናል:: አንድ ሰው እንደማያፈቅራት ልቡናው የሚያውቀውን ሴት ‹‹አፈቅርሻለሁ› ቢል ውሸት ተናግሯል ማለት ነው:: ወይም አንድ ልጅ የብስኩት ማስቀመጫውን አድፋፍቶ እያለ እናቱ ስትጠይቀው ‹‹አላደረኩም›› ቢል ዋሽቷል፡፡ ውሸት ማለት የምታውቀውን የምታስበውንና የሚሰማህን ክደህ መናገር ነው፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት በየዋህነት ወይም በስህተት ከሚፈፀመው የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የእግር ኳስ ዳኛ በአጠራጣሪ ሁኔታ የገባን ጎል ቢሽር ማለት ነው፡፡

የቅርብ ጊዜው አሜሪካዊው ታላቁ ፈላስፋ ጆሲያህ ሮይስ (Josiah Royce) ለውሸት ትርጓሜ ሲሰጥ የሰው ልጅ ይሆነኝ ብሎ የድርጊት መወከያ ቃላቱን በማቀያየር የሚያውቀውን እውነታ ሲቃረን ነው ይላል፡፡ «አይደለም» መባል የሚገባውን «ነው በሚልበት ጊዜ፤ ወይም «ነው» ማለት ሲገባው «አይደለም›› ለማለት ሲደፍር። ሮይስ ውሸትን የፈታበት መንገድ ወደ ጥንታዊ የእውነት ትርጓሜ ይመራናል፡፡ ከ2ሺህ 5 መቶ አመታት በፊት ፕሌቶና አርስቶትል በዚሁ መንገድ ለእውነትና ውሸት ብያኔ ሰጥተው ነበር፡፡

ፕሌቶና አርስቶትል እንደሚሉት የጨበጥነው አስተያየት ትክክለኛ መሆኑ የሚረጋገጠው <<ነው» መባል ያለበት <<ነው» ተብሎ ሲገኝ ወይም ‹‹አይደለም› መባል የሚገባው «አይደለም» ሲባል ነው፡፡ በአንፃሩ አስተያየታችን ሐሰት ሆኖ የሚገኘው ደግሞ የተገላቢጦሽ «ነው› መባል ያለበት <<አይደለም» በሚል ተለውጦ ሲገኝ ወይም ‹አይደለም›› በ«ነው» ተተክቶ ስናገኘው ነው፡፡ ፕሌቶና አርስቶትል እንደሚሉት የአስተያየታችን እውነትነት የሚረጋገጠው ከገሃዱ ዓለም ተጨባጭ ሁናቴና ከተፈጥሮ ህግ ጋር እየተመሳከረ ይሆናል፤ አስተያየታችን ከገሃዱ ዓለም ሆነ ከተፈጥሮ ህግ ጋር የተስማማ ሆኖ ከተገኘ እውነትነት ሲኖረው በአንፃሩ ከተጣረሰ ደግሞ ስህተት ተናግረናል ማለት ይቻላል ይላሉ፡፡

ስለዚህ ከላይ እንደተመለከትነው የእውነታን ምንነት አንጥሮ ማውጣት በጣም ቀላል ነው:: ፍቺውንም መረዳት ያን ያህል አዳጋች አይደለም፡፡ ጲላጦስ ኢየሱስን ስለእውነት ምንነት ሲጠይቅ ምናልባትም ምላሹ በኋላ ለሌላ ጥያቄ እራሱን አዘጋጅቶ ነበር «የተነገረን እውነት ይሁን ሐሰት እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን? በነገራችን ላይ አንተና ጓደኞችህ ስለእውነት መቋጫ ለመስጠት የሞከራችሁት ለዚህ ለጲላጦስ ያልተጠየቀ ጥያቄ ምላሽ በመሻት ነበር የተነገረን እውነት ይሁን ሐሰት እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?››

ለዚህ ጥያቄ ሶስት ዋና ዋና ምላሾች አሉ፡፡ አንዳንዱ ጉዳይ በራሳችን ተጨባጭ እውነታ የምንዳኘው ነው፡፡ «ድፍኑ ከቁራሹ ይበልጣል›> ይሄ እውነት በራሳችን አይተን ያረጋገጥነው በመሆኑ በየትኛውም አግባብ ተቀይሮ ቢመጣ ልንቀበለው የሚያዳግተን ነው፡፡ ድፍኑን እናውቃለን፤ ቁራሹንም እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ቁራሹ ከድፍኑ ሊበልጥ የሚችልበት አንድም መንገድ የለም፡፡ የአንዳንድ ነገር እውነትነት የምናረጋግጥበት አግባብ ቁራሹ ከድፍኑ የአለመብለጡ እውነታን መመዘኛ አድርገን ነው፡፡

ሁለተኛው እውነታን የማረጋገጫ መንገድ ደግሞ ልምድ ወይም ምልከታን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ አንድ ሰው ያለፈው አንድ ወር ሙሉ ቺካጐ ውስጥ አንዴም አለመዝነቡን ቢነግረን ሜትሮሎጂ ያዘጋጀውን የአየር ንብረት ሁኔታ መዝገብ በመመልከት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ወይም ስለመዋኛው ገንዳ ውሃ ሙቀት ቢነግረን አንድ እግራችንን ሰደድ አድርገን ማረጋገጥ ነው። እዚህ ላይ ሳይንስ ነክ ማጠቃለያዎች እንደ እውነታ የሚወሰዱት ተቃራኒ ሐሳብ እስካላጋጠማቸው ጊዜ ድረስ ብቻ ነው።

ሶስተኛው መንገድ በራሳችን ተጨባጭ እውነታ ሆነ በሶስተኛ ወገን ማረጋገጫነት የምንዳኘው እውነታ ሲያጋጥመን የምንጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ ስለአንድ ሰው ባህርይ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ስለአንድ ምርት ውጤታማ አገልግሎት እንዲህ ያለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ድምፅ በማሰባሰብ ሂደት አብላጫ ተቀባይነት ያለውን በመለየት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ነገር እንደ እውነት የመቆጠር እድሉ እጅግ በጣም ሰፊ ነው::

ይሄ ሶስተኛው የእውነታ ማረጋገጫ መንገድ ጓደኞችህ በደፈናው የነገሩህ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው ሰው በደፈናው የተስማማበት ነገር «እውነት ምንድነው» ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ ሰጪ አይሆንም፡፡ የዚያኑ ያህል የተሟላ ምላሽም ሊሆን አይችልም፡፡

እውነትን መግለጽ ቀላል ነገር ነው:: የሚነገረንን እውነት ይሁን አይሁን ለይቶ ማውቁ የበለጠ ከብዶ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የራስን እውነት ለሌሎች ለማስረዳት መሞከር ዋነኛው አዳጋች ጉዳይ ነው፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy