ፍልስፍና ምንድነው? ምንጭ ፦ የፍልስፍና አፅናፍ ፀሀፊ ፦ አለማየሁ ገላጋይ ለፍልስፍና ቁርጥ ያለ ፍቺ ለመስጠት አዳጋች የሚያደርገው ተገለባባጭ ርዕሰ-ጉዳይና ዓላማ ላይ መቆየቱ ነው፡፡ በአንድ በኩል ነገሮች ተፈጥሯዊ ባህርይ ላይ መሰረታዊ እውቀት የማስጨበጥ ዘርፍ ተደርጐ ይታሰብ እንዳልነበር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ መልካም ኑሮ መመሪያም ይታይ ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመን ፍልስፍና እንደ ሃይማኖታዊ መቀሰቻ ድጋፍ ተደርጐ ተወስዶ ነበር። አሁን ደግሞ ብዙዎች እንደተፈጥሯዊና ማህበራዊ ሳይንስ ተራዳ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ «ፍልስፍና» ቃሉ ‹‹የጥበብ ፍቅር» (love of wisdom) ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ ፍልስፍና የጥሬ እውቀት ማካበቻም ሆነ ማስተላለፊያ ዘርፍ ሳይሆን በጥበብ ስለጥበብ የሚደረግ ከፍተኛ መነሳሳት እና መጠየቅ ነው:: ሶቅራጥስ እንዳመላከተው ፈላስፋ ጥበብን ለማፍቀር እንጂ የራሱ ለማድረግ መጠየቅ የለበትም። ሶቅራጥስ፣ ምርመራችን የትም ያድርሰን የትም፣ ያልተመረመረ ህይወት እርባና የለውም በማለቱ የፈላስፎችን መንገድ እንደጠረገና እንደደለደለ ተደርጐ ተቆጥሮለታል፡፡ አባባሉ ለፍልስፍና የመመርመር ግንዛቤና የመጠየቅ ባህርይ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም የመልካም ህይወት ስነ-ምግባራዊ ግንዛቤን መልሶ መላልሶ በፍልስፍና የመመርመር ትኩረትን እንደሚያሻ ይጠቁማል፡፡ አርስቶትል ታላላቅ የሚባሉ ስራዎችን በማጥናት የፍልስፍናን ጭብጦች ከፋፍሎ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ከዚህ ተነስቶ ፍልስፍናን በብዙ ዘርፎች ከፋፍሏል፡፡ አርስቶትል ያበቃበት ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ ይህም የሚያመላክተው መጓዝ የሚቻለውን ያህል እንደተጓዘ ነው፡፡ ነገር ግን ፍልስፍና አሁንም በአፍላነት እድሜ ላይ የሚገኝ ባለተስፋ ነው፡፡ እድገቱን ለማጠናቀቅም በሺህ የሚቆጠሩ አመታት ከፊቱ ተነጥፈውለታል፡፡ @Zephilosophy @Zephilosophy 121 views19:26