Get Mystery Box with random crypto!

በአዲሱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ረቂቅ መመሪያ ለትምህርት፣ ስልጠና፣ ህትመትና የጤና አገልግሎት ዘ | Zehabesha

በአዲሱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ረቂቅ መመሪያ ለትምህርት፣ ስልጠና፣ ህትመትና የጤና አገልግሎት ዘርፎች የታክስ እፎይታ ያልተቀመጠ ሲሆን በአንፃሩ ከአልኮል ጋር ለተገናኙ ኢንቨስትመንቶች እፎይታ እንደሚሰጥ ካፒታል ጋዜጣ ዛሬ ዘግቧል፡፡ እንደዘገባው አዲስ መመሪያ ማውጣት ያስፈለገው ኢንቨስተሮችን ለማበረታታ በሚል ከሁለት አመት በፊት የወጣውን አዋጅ ተከትሎ ማሻሻያ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ መመሪያ መሰረት የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የቆዳና ቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የምግብ ኢንዱስትሪና የኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች ኢንዱስትሪዎች የታክስ እፎይታና ሌሎችም ማበረታቻዎችና ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡ እንደዘገባው የመጠጥ ኢንዱስትሪን በሚመለከት መመሪያው የአልኮል መጠጦችን ለሚያመርቱ ከአንድ እስከ ሁለት አመት የገቢ ግብር እንዳይከፍሉ የሚደነግግ ሲሆን፣ የወይን ጠጅ ለሚያመርቱ ኢንዱትሪዎች ደግሞ ከሶስት እስከ አራት አመት እፎይታን አስቀምጧል፡፡ መመሪያው በተመሳሳይ ለቢራና የቢራ ብቅል አምራቾችም ከሁለት እስከ ሶስት አመት የእፎይታ ጊዜ እንደሰጣቸው የጠቆመው ዘገባው ከጤናው ዘርፍ ለስፔሺያላይዝድ ሆስፒታል ብቻ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ከታክስ ነፃ ጊዜ መፍቀዱን አስረድቷል፡፡ ይሁንና የሆስፒታል አገልግሎት፣ የምርመራ አገልግሎትና የክሊኒክ አገልግሎት ከእፎይታው ውጭ እንዲሆኑ ረቂቅ መመሪያው ማስቀመጡን ገልፆም በተመሳሳይ የቱሪዝም፣ የኮንስትራክሽንና የህትመት ኢንዱስትሪዎች ከዚህ በፊት እንደነበረው የታክስ እፎይታ ጊዜ እንደሌላቸው መደንገጉንና ይህ ግን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ዘርፍ እንደማይጨምር አስታውቋል፡፡