Get Mystery Box with random crypto!

የፍቅር ጥያቄ ያልተቀለችውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በስለት ወግቶ የገደለው ተማሪ እስራት ተቀጣ። በ | Zehabesha

የፍቅር ጥያቄ ያልተቀለችውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በስለት ወግቶ የገደለው ተማሪ እስራት ተቀጣ።
በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጫሞ ካምፓስ ጥር 23/ 2014 ዓ.ም ምሽት 4 ሰዓት ከ50 የሁለተኛ አመት የሆቴል ማኔጅመንት ተማሪ የሆነችውን ጽገሬዳ ግርማይን ደጋግሞ በስለት በመውጋት የገደላት ተከሳሽ ድርጊቱን በማመን እጁን ለፖሊስ መስጠቱን የዐቃቤ ህግ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
የጋሞ ዞን ፖሊስ ተከሳሽን በቁጥጥር ስር በማዋል ከዩኒቨርስቲው ተማሪዎችና የጥበቃ ሠራተኞች እንዲሁም ከሐኪም ያገኛቸውን ማስረጃዎችን አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ አቅርቧል።
ሟች የቀረበላትን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ ተከሳሽ በእልህ ስለት በመያዝ ጓደኞቿን ይቅርታ እጠይቃታለሁ አገናኙኝ በማለት አስጠርቶ ዘጠኝ ቦታ የወጋት ሲሆን ሟች ባሠማችው የጩኽት ድምጽ የዩኒቨርስቲው ጥበቃ ሰራተኞችና ተማሪዎች ደርሰው ወደ አርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ቢወስዷትም ምሽት 5:00 ህይወቷ ማለፉን የዐቃቤ ህግ መዝገብ ያስረዳል።


ከዐቃቤ ህግ የቀረቡለትን የሰው፣የህክምና እና የሠነድ ማስረጀዎች በጥልቀት የተመለከተው የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት የተሻሻለው የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመርያ ቁጥር 2/2006 መነሻ በማድረግ ግንቦት 19/ 2014 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት ተከሳሽ ብሩክ በላይነህ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

የወንጀል አፈፃፀም ሁኔታው በደረጃ 1 እርከን 38 የሚሸፈን መሆኑ በችሎቱ የተገለጸ ቢሆንም ከተከሳሽ የቀረቡ አራት የክስ ማቅለያዎችን በመውሰድ ከ15 ዓመት እስከ 18 የሚያስቀጣው እርከን 34 መሠረት ውሳኔ መተላለፉን ከከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የተገኘ መረጃ አመላክቷል።

በያምላክነሽ ተረፈ