Get Mystery Box with random crypto!

EOTC TV እና MK TV የት ናቸው? ዴር ሡልጣንን አስመልክቶ CTV (Coptic TV) የተባለው | ዳንኤል ገብረማርያም

EOTC TV እና MK TV የት ናቸው?
ዴር ሡልጣንን አስመልክቶ CTV (Coptic TV) የተባለው የግብጽ ቤተክርስቲያን ጣቢያ በየዕለቱ መረጃዎችን በዐረብኛ እየዘገበ ለግብጻዊያን ያደርሳል። ይህ ጣቢያ የግብጽ መነኮሳት ዴር ሡልጣንን የግብጽ ቀለም ከሚቀቡበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያዊያንን ተቃውሞ እንዲሁም አሁን የተቀባው የግብጽ ባንዲራ እስኪጠፋ ድረስ ቶሎ ቶሎ ከቦታው መረጃ በማድረስ ግብጻዊያንና ሌላው ዓለም ጉዳዩን እንዲያውቅ እያደረገ ቆይቷል። በዘገባዎቹ ኢትዮጵያ የግብጽን ይዞታ ለመውረር እንደሞከረች አድርጎ በማቅረብም የኢትዮጵያን ስም እያጠለሸ ነው። ሌሎች የግብጽ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችም በተመሳሳይ በንቃት ስለዴር ሡልጣን በዐረብኛና በእንግሊዝኛ ሲዘግቡ ሰንብተዋል።

ወደአገራችን ስንመለስ ግን የጉዳዩ ባለቤት ከኾነችው ከኢኦተቤክ ቴቪ ጣቢያ ጀምሮ አንድም የኢትዮጵያ ሚዲያ ስለዴር ሡልጣን አልዘገቡም። የማኅበረ ቅዱሳን ቴቪም ኾነ ኢኦተቤክ ቴቪ በዴር ሡልጣን ስለተፈጠረው ነገር ለኢትዮጵያዊያን አንድም መረጃ ማድረስ አለመቻላቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። የመንግሥት ሚዲያዎች ኾነ ብለው ዝም ቢሉም የቤተክርስቲያን ሚዲያዎች ግን ሊዘግቡት ይገባቸው ነበር። በዚህ ዘመን ሚዲያ ታላቅ ዐቅም አለው። እናም ቅድስት ቤተክርስቲያን በደል ደርሶባትም የተገላቢጦሽ ተከሳሽ ስትኾን የግብጽ መነኮሳትን ትንኮሳ የሚያጋልጡ ዘገባዎችን ሠርቶ ለዓለም ማስተዋወቅ የእኛ ቤተክርስቲያን ሚዲያዎች ግዴታ ነበር። ነገርግን አንዳቸውም ስለጉዳዩ ማውራት አልሞከሩም።

በእርግጥ የግብጽ ቤተክርስቲያን ዴር ሡልጣንን ከኢትዮጵያ ነጥቃ ለመጠቅለል በዕቅድ ነው እየሠራች ያለችው። ለዚህም ደግሞ የግብጽ መንግሥትን ጨምሮ አክራሪ የእስልምና ቻናሎች ሳይቀር ድጋፍ እያደረጉላት ነው። ጉዳዩን ከመንፈሳዊ ቦታ ይዞታ በላይ ፖለቲካዊ አድርገውታል። ግብጽ በራሳችን አገር የምታበላላንና የምትበጠብጠን አንሶ በእስራኤል ሀገርም በየጊዜው አባቶቻችንን ዕረፍት እያሳጣች ትገኛለች። ታዲያ የቤተክርስቲያን አካላትም ኾኑ የመንግሥት አካላት ጉዳዩን በዝምታ ማለፋቸው ለምን ይኾን? ይህ ዝምታ የሚቀጥል ከኾነ ለሦስት ሺህ (2974) ዓመታት ገደማ በእጃችን የቆየውን ዴር ሡልጣንን በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ማጣታችን የማይቀር ነው። ስለኾነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም ኦርቶዶክሳዊያን ለጉዳዩ ትኩረት ልንሰጠውና ልንታገል ይገባል። ቅዱስ ሲኖዶስም ተፈጻሚ የሚኾኑ መመሪያዎችን አውጥቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በመነጋገር ችግሩ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈታ ቢያደርግ መልካም ነው። ይህ ካልሆነ ግን በየጊዜው የሚነሡ የወረራ ሙከራዎች ዋጋ ያስከፍሉናል።

በእኛ ንዝህላልነትና ግዴለሽነት ሁልጊዜ ቤተክርስቲያንን ተሸናፊ የምናደርጋት እስከመቼ ይኾን?