Get Mystery Box with random crypto!

በመግለጫ የሚፈታ የቤተክርስቲያን ችግር የለም! (ዳንኤል ገብረማርያም) ================= | ዳንኤል ገብረማርያም

በመግለጫ የሚፈታ የቤተክርስቲያን ችግር የለም!
(ዳንኤል ገብረማርያም)
====================
ዓርብ ዕለት የተሰበሰበው ቋሚ ሲኖዶስ ባለፈው እሑድ (መጋቢት ፳፭ ቀን) በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ወረዳ በመንግሥት ታጣቂ በጥይት የተገደለውን ኦርቶዶክሳዊ ወጣት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም "በአቃቂ ቃሊት ወረዳ በጸጥታ አካላት የተገደለውን ዘመድኩን አማረ ገዳዮች መንግሥት ለፍርድ እንዲያቀርብ ውጤቱንም ለሕዝብ እንዲያሳውቅ" ሲል ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የጠየቀው። እንደው አሁን ይህ መግለጫ ቤተክርስቲያንን ከመግለጫ የዘለለ ኃይል የሌላት ደካማ ኾና እንድትቆጠር ከማድረግ የዘለለ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ለቤተክርስቲያን የሚየስገኘው ረብ ምንድነው?

ለመኾኑ በቋሚ ሲኖዶሱ መግለጫ ላይ ወንጀለኞችን ለፍርድ ያቅርብ ተብሎ የተጠየቀው የትኛው መንግሥት ነው? የብልጽግና መንግሥት? ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ላይ ግፍና በደልን የፈጸሙ፣ ምእመናንንና ካህናትን የገደሉ ወንጀለኞችን መቼ ተጠያቂ አድርጎ ያውቅና? እንደው የብልጽግና መንግሥት መቼ ቤተክርስቲያንን ሰምቷት ያውቃልና ነው ቋሚ ሳኖዶሱ ጥያቄ የሚያቀርብለት? እንደው'ኮ አስገራሚ ነው በጣም። በክፍለ ሀገር የተፈጸሙ በደሎችን ትተን በዚሁ በአዲስ አበባ ብቻ ከተፈጸሙት መካከል በጣም ጥቂቶቹን ብንጠቅስ በ24 አካባቢ በሌሊት ቤተክርስቲያን ማፍረሱ ሳያንሰው ኹለት ወጣቶችን (ኦርቶዶክሳዊያንን) የገደሉ የጸጥታ ተቋማት መች ተጠየቁ? መንግሥትስ ለሟቾቹ ቤተሰቦች ካሣ እከፍላለሁ ብሎ የገባውን ቃል መቼ ፈጸመ? ለአብያተክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ እሰጣለሁ ያለው መንግሥት መቼ ቃሉን ፈጸመ? እንደው በጣም የቅርቡን እንጥቀስና የወይብላ ሰማዕታትን የገደሉ ወንጀለኞችን መንግሥት ተብዮው መቼ ለፍርድ አቀረባቸው?

ታዲያ ቋሚ ሲኖዶሱ የትኛውን መንግሥት ነው "ወንጀለኞቹን ለፍርድ ያቅርብ" ብሎ የጠየቀው? ወይስ እኛ የማናውቀው የቤተክርስቲያንን ጥያቄዎች የሚሰማ ሌላ መንግሥት አለ? ቋሚ ሲኖዶሱ ለምንድነው ከምእመናን ጋር ድብብቆሽ የገጠመው? ገና ምእመናን "አባቶች ለምን ዝም አሉ?" ይሉናል ተብሎ የወጣ እንጂ ይህ መግለጫ ለቤተክርስቲያን የሚያስገኘው አንድም ትርፍ የለውም። እንደውም ቤተክርስቲያን በደል በተፈጸመባት ቁጥር ከማለቃቀስና በዳዮችን ከመለመን ውጪ ዐቅም የሌላት ደካማ ኾና እንድትቆጠር የሚያደርግ ነው። በእርግጥ ቤተክርስቲያናችን ተንቃና ተዋርዳ እንድትታይ ከተደረገች ቆይቷል። ይኸውም ለአባትነት ያልበቁ አባቶች በውስጧ ስለተሰገሰጉ ነው።

ይህ መንግሥት በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆም የገለጠው ቅዱስ ሲኖዶስ ይቀጥልና "በሃይማኖት ተቋማት የአምልኮ ቦታ መካከል ሊኖር የሚገባው ርቀት በሕግ በተቀመጠው መሠረት እንዲተገበር"ም ጠይቋል። ግሩም ነው በእውነቱ። በአፍሪካ ኅብረት (ከርቸሌ) ሚካኤል ቤተክርስቲያን ላይ የተፈጸመው በደል ተረስቶ ነው? ወይስ አሁንም "አባቶች ተናግረዋል" ለመባል ያህል ነው እንዲህ የተጠየቀው? ለመኾኑ የትኛው መንግሥት ነው የአምልኮ ቦታዎችን እርቀት የሚጠብቀው? የቤተክርስቲያንን ይዞታ እየነጠቀ ለሌሎች የሚያከፋፍለው የብልጽግና መንግሥት? ኧረ ተው አባቶች ተው ልጆቻችሁን እንዲህ እንደሞኝ አትቁጠሩን። ሌላው ቢቀር ከላይ የተጠቀሰውን ቤተክርስቲያን (አፍሪካ ኅብረት ቅዱስ ሚካኤል) ጉዳይ መቼ ፈታችሁትና? መቼ በሕጉ መሠረት መፍትሔ አስገኛችሁና ነው ዛሬ እንዲህ የምትጠይቁ? ያውም ፌዘኛውን መንግሥት!?

ከዚህም በተጨማሪ "መንግሥት ጸጥታ በማስከበር ስም ጥቃት የፈጸሙ አካላትን ለፍርድ ከማቅረብ በተጨማሪ ሌሎች የጸጥታ አካላት ከተመሳሳይ ድርጊት እንዲታቀቡ እንዲያደርግ" ሲልም ቋሚ ሲኖዶስ አስታውቋል። አይ አባቶቻችን! እስኪ እንደው እናንተ እንደጠየቃችሁት ይኹን። የጠየቃችሁት መንግሥት ቃላችሁን ተቀብሎ ተፈጻሚ ለማድረግ ያብቃው። ግን ጥያቄዎቻችሁን እንደማይሰማችሁ አንድ ሺህ በመቶ እርግጠኞች ነን። ምክንያቱም ወንጀለኛው ራሱ የጠየቃችሁት መንግሥት ስለኾነ። በእርግጥ እናንተም ተባባሪዎቹ ናችሁ። ይህን የምንለው ደግሞ በዐይናችን ስላየን፣ በጆሯችንም ስለሰማን እንጂ ከመሬት ተነሥተን አይደለም። ተባባሪዎቹ ባትኾኑማ ለአራት ዓመታት ሙሉ ቤተክርስቲያን ክፉኛ ስትፈተን እየተለማመጣችሁ ዝም ባላላችሁ ነበር። የመንግሥት ተባባሪዎች ባትኾኑማ ለሃያ ሰባት ዓመታት ቤተክርስቲያን ላይ ሴራ ሲሠራ እያያችሁ በዝምታ ባልኖራችሁ ነበር። የመንግሥት ተባባሪዎችና አጎብዳጆች ባትኾኑማ ደፍራችሁ ወጥታችሁ "ቤተክርስቲያን ላይ ግፍ እየተፈጸመ ነው፣ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመ ነው፣ መዋቅራዊ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፣ ቤተክርስቲያን በመንግሥት እየተሰደደች ነው!" ብላችሁ በሞገታችሁ ነበር። እንደአቡነ ጴጥሮስ እንደቅዱሱ ሰው ከምንም በላይ እረኝነታችሁን አስቀድማችሁ ለምእመኑ አርአያ የሚኾን ለቤተክርስቲያንም መፍትሔን የሚያመጣ በጎ ተጋድሎን ባደረጋችሁ ነበር። አጎብዳጆች ባትኾኑማ ኖሮ "የቤተክርስቲያን መከራ ይቁም!" ብለው የተነሡ ልጆቻችሁ ሲታፈሱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲገረፉ እያያችሁና እየሰማችሁ ዝም ባላላችሁ ነበር። የመንግሥት ተባባሪዎች ባትኾኑማ ኖሮ ለቤተክርስቲያን መብትና ህልውና ሆ ብሎ በወጣው ምእመን ስሜት ላይ አንዳች መፍትሔ የማያመጣ ስምምነትን ፈጽማችሁ፣ በጋለው የምእመኑ ቁጣ ላይ በረዶ ባልጨመራችሁ ነበር። መስቀል ዐደባባይ የማንም መፈንጫ ሲኾን የሕዝብን ቁጣ እንዲጠፋ ከማድረግ ይልቅ ከምእመኑ ፊት ተሰልፋችሁ ለቤተክርስቲያን በታገላችሁ ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል፦ መለካዊነት የገዛቸው፣ አድርባይነት የዋጣቸው፣ ግዴለሽነት ያጠቃቸው አባቶች በዙና የቤተክርስቲያን መከራ ማላገጫ በሚመስል መግለጫ ብቻ እየተድበሰበሰ እንዲቀር ይደረጋል። በእውነቱ ከእናንተ መካከል እውነተኛ እረኛ ማን ይኾን?

ብፁዓን አባቶቼ ሆይ ቅድስት ቡራኬያችሁ ትድረሰኝ! ባከብራችሁም፣ ብወዳችሁም፣ ቤተክርስቲያን ለእናንተ ብቻ ሳትኾን ለእኔም ናትና በትሕትና እጠይቃችሁ ዘንድ ግድ ይለኛል። በእውኑ በመግለጫ መከራዋን ማስወገድ፣ ስደቷን ማስቆም የሚቻል ይመስላችኋል? ወይስ ቤተክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ አልተረዳችሁትም? እንደው ዓለማችን የደረሰችበትን ኢትዮጵያችንም ያለችበትን መንገድ የሚገልጽ መረጃ አይደርሳችሁ ይኾን?ይህ ነው እንዳልል ደግሞ ከብዛኞቻችሁ በውጪው ዓለም የኖራችሁ፣ በዓለማዊት ትምህርታችሁ ብዙ ዲግሪ ያላችሁ፣ ዘመናዊ የእጅ ስልኮችን የምትጠቀሙ ናችሁ። ብቻ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ የምታሳዩን ነገር ብዙም ደስ አይልም። ምናልባት "አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም" ከኾነ እያወቃችሁ ተኝታችኋልና የእኛ የምእመናን ለቅሶና መከራም አልቀሰቀሳችሁምና ቸሩ አምላክ እንዲያነቃችሁ እንማጸናለን።

ግድየለሾች ሆናችሁ ነው እንዳንልም ተቸግረናል። ሆድ አደሮች እያስጨነቋችሁ ነው እንዳንል ደግሞ የአቡነ ጴጥሮስ ልጆች ናችሁና ለማመን ይከብደናል። እኛን ልጆቻችሁን ስለሰማዕትነት የምታስተምሩን እናንተ፣ ፍርሃትን በመስቀሉ ኃይል አሸንፉ የምትሉን እናንተ የሚደርስባችሁን ነገር ፈርታችሁ የቤተክርስቲያንን መከራ እንዲሰፋና እንዲቀጥል እያደረጋችሁ ነው ብሎ ለመቀበል ይከብዳል። እንደው የእየሉጣ ፍርሃት ገዝቷችሁ ከኾነ በእርግጥ እኛ ልጆቻችሁ እንደቂርቆስ ልንጸልይላችሁ፣ ኑ ገድላችንን እንፈጽም ልንላችሁም ይገባናልና አሳውቁን። እኛ እናንተን ስንጠብቅ ቤተክርስቲያናችን የማይገባትን መከራ እየተቀበለች ነውና እባካችሁ