+• የቀስት ጸሎቶች •+ የጊዜ ባለቤት ለሆነው ፈጣሪያችን "ጊዜ አጣሁ" ማለት ከጀመርን ሰንበትበት ብለናል:: የፈጣሪን በረከት መንዝረን ስናበቃ ለእርሱ የሚሆኑ ሽርፍራፊ ደቂቃዎችን ለመመደብ እናመነታለን:: አባቶቻችን እና እናቶቻችን "ጸልዩ! ኧረ ተዉ ጸልዩ!" ብለው ለዘመናት ወተወቱ:: ይህ ምክራቸው ግን ፍጹም ሰሚ አጣ:: በጊዜ ያልተካንነውን ጸሎት ሁሉም ጭንቅ ሲሆን በወከባው መሃል ለመጸለይ ብንፈልግም ተሳነን:: "ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ" እንደሚባለው ሠርግ የተባለ ሞት ደርሶ ስንኳ በርበሬ መቀንጥሱን አልቻልንም:: በተጋድሎው እጅግ ደክመን በመንፈሳዊው ውጊያው ላይ ሰይጣን ሙትና ቁስለኛ እያደረግን አለን:: ከትእዛዛቱ ምን ያህል እንደራቅን የምናውቀው "ሳታቋርጡ ጸልዩ" (1 ተሰ 5:17) መባላችንን ስናስታውስ ነው:: ጸሎቱ እንዳይቋረጥ የታዘዘው ውጊያውም ስለማያቋርጥ ነው:: ሰይጣን ድካም የሌለበት፣ እንቅልፍ የማያስፈልገው፣ ተስፋ የማይቆርጥ እና የብዙ ሺህ ዓመታት የሥራ ልምድ ያለው ከይሲ ነው:: የእኛን የሰዎችን ሁኔታ በሚገባ ስለተገነዘበም ቀጥታ ከመግጠም ይልቅ እንደ ደፈጣ ተዋጊ እየተደበቀ፣ እያዘናጋ እና እያደባ ያጠቃናል:: "የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።" (ኤፌ 6:11) የሚለው ቃል አንድም ሳይቀር ያሉንን መንፈሳዊ ትጥቆች ሁሉ ታጥቀን እንድንነሳ የሚያሳስብ ነው:: ይህ የውጊያውን ብርቱነት በአጽንኦት ያስታውሰናል:: የጥንቶቹ ብርቱ አባቶች እና እናቶች ሰይጣንን እያቆሰሉ ድል ከነሱበት መሣሪያ አንዱ የቀስት ጸሎት ነው:: የቀስት ጸሎት ማለት ከመንፈሳዊ መጻሕፍትም ሆነ ከራሳችን ሊገኙ የሚችሉ አጭር እና በተመስጦ የሚባሉ አጫጭር ጸሎቶች መጠሪያ ነው:: በተለይም ደግሞ የምንኩስና ተጋድሎ በተፋፋመበት የግብጽ በረሃ ከጥንት አንስቶ የዚህ አይነት ጸሎቶች ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ:: አባ ፖላሞን ከርሱ በቀደሙ ብርቱዎች ትምህርት ላይ ተመስርቶ አባ ጳጉሚስን ሲያስተምረው "ሳናቋርጥ እንድንጸልይ ታዝዘናልና፤ አጫጭር ጸሎቶቹን ሳንቆጥር ልንጸልይ ይገባናል" ብሎት ነበር:: ታላቁ ቅዱስ ወግሪስም "አጭር የተመስጦ ጸሎቶችን ተጠቀሙ" በማለት የሚመክር ሲሆን የእነዚህ ጸሎቶች ኃያልነትም ይታይ ዘንድ ቅዱስ ዮሐንስ ዘአስቄጥስ አጭርና በተመስጦ የሚባሉት ጸሎቶቹ ሰይጣንን ሲያቆስሉት በራዕይ ተመልክቶ ነበር:: ከእነዚህ የቀስት ጸሎቶች መካከል "ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረኝ" የሚለው ጸሎት ተወዳጅነትን ያተረፈ ነው:: ይህ ጸሎት በተለያየ አይነት ሁኔታ ለዘመናት አገልግሎት ላይ ውሏል:: በሀገራችንም "እግዚኦ ማሐረነ ክርስቶስ" (አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን) በሚለው ይታወቃል:: እንዲህ አይነት ጸሎቶች በሀገራችን የምንኩስና ታሪክ ውስጥ እንደነበሩ ማሳያ ከሚሆኑት አንዱ ደግሞ ቅዱስ አቡነ ሃብተማርያም ናቸው:: የታላቁ አቡነ ሃብተማርያም ገድል እንደሚነግረን ከሆን አባታችን ይህንን ጸሎት ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮ ዘወትር እየደጋገሙ ይጸልዩት ነበር:: ዛሬም ድረስ ከመነኮሳት እስከ ምእመናን ድረስ ተወዳጅ ጸሎት ሆኖ እንደቀጠለ ነው:: የቀስት ጸሎቶች ሰይጣንን እረፍት ይነሱታል:: የእኛን ኅሊና ደግሞ ሁሌም ከፈጣሪ በማገናኘት "አልእሉ አልባቢክሙ" (ልቡናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ) የሚለውን ሰማያዊ ትእዛዝ ፈጻሚ ያደርጉናል:: የጸሎት መጽሐፍ መጨበጥ በማንችልባቸው ጊዜያት ሁሉ ከፈጣሪ የምንገናኝባቸው ድልድዮች ናቸው:: ከእነዚህ አጫጭር ጸሎቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት:- * ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ማረኝ * አቤቱ ንጹህ ልብን ፍጠርልኝ፤ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ (መዝ 50:10) * አቤቱ ጌታዬና ንጉሤ ሆይ፤ ለባልንጀሮቼ ክፉ ያለማሰብን እና የራሴን ኃጢአቶች የማየት ጸጋ ስጠኝ (ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ) * አቤቱ፥ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን። (መዝ 70:1) * ጌታ ሆይ፤ እንደ ፈቃድህ እና እንደ እውቀትህ ማረኝ! (ቅዱስ መቃርዮስ) * ጌታ ሆይ እርዳኝ! የሚከተሉት ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከደረሳቸው የሃያ አራት ሰዓት አጫጭር ጸሎቶች መካከል የተመረጡ ናቸው:- * አቤቱ ጌታ ሆይ፤ ከዘለዓለማዊ ስቃይ አድነኝ! * እቤቱ ጌታ ሆይ፤ ከፈተና ሁሉ አድነኝ! * አቤቱ ጌታ ሆይ፤ አትተወኝ! * አቤቱ ጌታ ሆይ፤ ትሕትናን፣ ንጽሕናን እና መታዘዝን ስጠኝ:: * አቤቱ ጌታ ሆይ፤ ስምህን አመሰግን ዘንድ ጸጋህን ላክልኝ:: * አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ በሕይወት መጽሐፍ ስሜን ጻፈው፤ መጨረሻዬንም አሳምርልኝ:: በእነዚህ እና መሠል ጸሎቶች ሕይወታችንን እናስጊጥ:: ለመጸለይ የግድ ሰዓት መጠበቅም ሆነ የጸሎት መጽሐፍ መጨበጥ የለብንም:: ልባችን ያረፈበትን አንድ አጭር ጸሎት (ወይም እንዳለንበት ሁኔታ ተስማሚ የሆነውን አጭር ጸሎት) የእግር ጉዞ ስናደርግ፣ በመኪና ስንሄድ፣ ስንቀመጥም ሆነ ስንተኛ በውስጣችን እየደጋገምን እንጸልይ:: ጸሎት የሁሉ ነገር መክፈቻ ቁልፍ መሆኗን አንዘንጋ! Fresenbet G.Y Adhanom 3.2K views06:46