Get Mystery Box with random crypto!

ኦ ሚካኤል! ሚካኤል ሆይ፤ የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው ከልዑል ስም አጠራርህ ጋር ለተባበረ ስም | መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር)

ኦ ሚካኤል!

ሚካኤል ሆይ፤ የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው ከልዑል ስም አጠራርህ ጋር ለተባበረ ስም አጠራርህ ሰላም እላለሁ፡፡ የእግዚብሔር የምክሩ አበጋዝ ሆይ፤ የተቸገሩትን፣ የተጨነቁትን ዘወትር እንደምትረዳቸው ሁሉ፤ እኔንም ለመርዳት ክንፍህን ዘርግተህ በፍጥነት ድረስልኝ፡፡

ሚካኤል ሆይ፤ ለሰው ልጅ ይቅርታን ለማስገኘት ወደ ልዑል እግዚአብሔር አሻቅበው ለሚማልዱ ዓይኖችህ ሰላምታ ይገባል፡፡ ሚካኤል ሆይ፤ በጠላት ተማርከው ለሚጨነቁና ለሚሰቃዩት ዋስ ጠበቃቸው አንተ ነህና፡፡ በእኔ ላይ የሚተበትቡትን የጠላቶቼን የምክር መረብ በጣጥሰህ ጣልልኝ፡፡ ነፍሴንም ሥጋዬንም ለአንተ አደራ ሰጥቻለሁና፡፡

ሚካኤል ሆይ፤ ስለ ሙሴ ሥጋ ከዲያብሎስ ጋር ክርክር በተደረገ ጊዜ የዘለፋ ቃል ላልተናገረ አንደበትህ ሰላም እላለሁ፡፡ ክቡር መልአክ ሆይ፤ ክብርህ ከመላእክት ሁሉ ክብር ከፍ ያለ ነውና፤ በሥነ ሥዕልህ ፊት ቆሜ ልመናዬን በማቀርብበት ጊዜ ሁሉ አይዞህ አለሁልህ በማለት ፈጥነህ ድምጽህን አሰማኝ፡፡

ሚካኤል ሆይ፤ የፍጥረታት ሁሉ መጠለያ ለሆኑ ክንፎችህ ሰላም እላለሁ፡፡ ክቡር የሰማውያን ካህናት አለቃ ሆይ፤ ከእለት እኪት አድነን፤ ከጥፋት ሁሉ ሰውረን፡፡

ሚካኤል ሆይ፤ የመብረቅ መስቀል ምልክት ያለበት በትረ ወርቅ ለጨበጡ እጆችህ ሰላም እላለሁ፡፡ ሊቀ መላእክት ሆይ፤ በገዳመ ራማ የምትኖር የዋህ ርግብ ወይም ዋልያ አንተ ነህና፤ የሕጻናት እድገት በነጋው በነጋው እንዲጨምር ጽድቅህ በእኔ በባርያህ ላይ እድገቷን ታሳይ፤ ትግለጽ፡፡

ሚካኤል ሆይ፤ ቂም በቀል የሌለበት የርህራሄ እና የየዋህነት መዝገብ ለሆነ ልቡናህ ሰላም እላለሁ፡፡ የሰማያዊያን ኃያላት አለቃ ሚካኤል ሆይ፤ የእስራኤልን ልጆች ባሕሩን ከፍለህ በባሕር መካከል እንዳሳለፍካቸው፤ እኔንም አገልጋይህን ከስውር ወጥመድ ሰውረህ በሰላም አሳልፈኝ፡፡

አማላጃችን ሚካኤል ሆይ፣ ፈጥኖ ደራሻችን ሚካኤል ሆይ፣ የጌታን ዙፋን ከሚያጥኑ ሱራፌል ካህናት አንዱ ሰማያዊ ካህን አንተ ነህኮ፡፡ የሰማያውያን ሊቃነ መላእክት ሁሉ አንተ አለቃቸው ነህኮ፡፡ ይልቁንም የልዑላን ልዑል አንተ ነህና፤ በጠራሁህ ጊዜ ሁሉ በይቅርታህ በቸርነትህ ድረስልኝ፣ አትራቀኝ፡፡