Get Mystery Box with random crypto!

ጎረቤታችን ናቸው። አለም ለእነሱ መዋደድ ግድ የሚሰጠው ይመስላቸዋል ወይ ሰው ባለበት ለፍቅራቸው ም | የ ቃል ደብዳቤዎች💌

ጎረቤታችን ናቸው። አለም ለእነሱ መዋደድ ግድ የሚሰጠው ይመስላቸዋል ወይ ሰው ባለበት ለፍቅራቸው ምስክርነት መናገር ፍቅር ያጠናክራል የሚል እውቀት ጭንቅላታቸው ውስጥ ሰርጿል ።
እንዴት እንደሚከባበሩ ፣ እንደሚዋደዱ አንዳቸው ለአንዳቸው ስጦታ እንደሆኑ በሆነ ምክንያት ሰብሰብ ስንል መዘብዘብ ይጀምራሉ። የልጃቸውን ልደት አዘጋጅተው ማታ ከቤርሳቤት ጋ ሄድኩ ፤ ጥሩ ሰዎች ስለሆኑ እና ቤርሳቤት ማህበራዊ ህይወት ስለምትወድ ሄድን ። የተገናኙበትን እለት ለዘጠነኝ ጊዜ ሳያዛነፍ ሳይጨመር እየተቀባበሉ ተረኩልን ። ለዘጠነኛ ጊዜ ሰምተነዋል ሳንል ሁሌም ሲነግሩን የምንጠይቀውን ጥያቄ የምናጨበጭበውን ጭብጨባ አጨበጨብን ።
ድንገት እናንተ የት ነው የተገናኛችሁት አለችን ኤልሳ ። ከቤርሳቤት ጋ ተያየን። ፈጠን ብዬ ፦ አዳማ የ leadership ስልጠና ስሰጥ ቢሮዋ ወክሏት ሰልጣኝ ነበረች ። ተከይፌባት በሰበባ-ሰበብ ስልኳን ተቀበልኩ ። ደጅ ጠንቼ እትት ብዬ ይሄው አንድ ልጅ ወለድን
አልኩኝ፤ አለቀ። ውሸት ብዙ አይጎተትም ብዙ ካልተጠና በቀር ቤርሳቤት ዝም አለች።
የአወራሁት ውሸት ነበር ። ለካ ሁሉ እውነት አይወራም ። ለካ የሚከደን ገጠመኝ አለ። ለካ ለራሳችን ደግመን የማንነግረው የሚጎመዝዝ እውነት አለን። እውነታው ፦ ከቤርሳቤት ጋ የተገናኘነው ጭፈራ ቤት ነው የተገናኘን ቀን ነው የተናፋነው ፤ ወሲባችን ፍቅር አልነበረውም ፤ ከአንድ ዙር መፋተግ በኋላ፤ አንድ ዙር ፍቅር አልባ ወሲብ እንዳለቀ ፊቴን አዞርኩ ሲጋራዬን ለኮስኩ ፤ ፊቷን አዙራ ስልኳን መነካካት ጀመረች ። ሁለታችንም ጀብረር ብለን ነበር። ምንም ያላወራው ይመስለኛል ፤ እርግጠኛ ነኝ ከዚህ በኋላ አንገናኝም ፤ በአንድ ቀን የምትጋደም ፣ ከሴተኛ አዳሪ ገንዘብ ባለመቀበል ብቻ የምትበልጥ ወይም የምታንስ ልጅ ማን ቁምነገር ይሰጣታል። አስክሮ ፣ እትትት ብሎ የሚቾምስ አለሌ ሸሌ ወንድ ለቁምነገር እንደማይሆን እርግጥ ነው። ተኛን !
ሳንተቃቀፍ ተኛን።
እኩለ ለሊት እንዳለፈ ይመስለኛል አመመኝ ከተኛሁበት አልጋ ተስፈንጥሬ ከአልጋዬ ብዙ
ሳልርቅ ወለሉ ላይ አስመለስኩ ።
ከመቅፅበት ተነስታ ከጎኔ መጥታ ልቤን ያዘችልኝ ፤ ከሆዴ ጀምሮ አማጥኩኝ ፣ አማጥኩኝ አቅም አነሰኝ እና ጥምልምል አልኩ ፤ መታገል ፣ ማጓራት ብቻ የሚወጣ ግን የለም ውሃ ጠጣ ብላ ሰጠቺኝ ፤ ትንሽ ጠጣሁ አፍታ ሳይቆይ የጠጣሁትም ውሃ ወጣ ። ቀና በል ፥ ይሸትኻል አለቺኝ ፤ ትውከቱ እንዳይሸተኝ ቀና እያደረገችኝ ፤ እሷን ተደግፌ ቀና አልኩ ጨርቅ አምጥታ (ከውስጥ የለብስኩትን ቦዲ) ውሃ ነክራ አንገቴን ፣ ግንባሬን አራሰችልኝ ፤ ቅዝቅዝ አለኝ ። ቀስ ብዬ ጠቅልል ብዬ ተኛሁ ፤ ስትንጎዳጎድ እንቅስቃሴዋ ይሰማኛል ፤ አቅሜ ተዳክሞ ስለነበር ለጥ አልኩ ። ጠዋት ስነቃ እና ማታ የሆነውን ሳጤነው ሁኔታዋ እና እንክብካቤዋ አንጀቴን በላው።
ትውከቴ ከቦታው የለም ፤ እንዴት አልተፀየፈችውም ፤ ማን ስለሆንኩ አንደዚህ
ተንከባከበቺኝ ?! አብረን ቁርስ በላን ። ስለማታው ሁኔታ ምንም አላወራንም ፤ አፈርኳት ፤ ውለታዋ ቆጠበኝ። ከዛ ቀን በኋላ አብረን ነው የምንውለው። ተልካሻ ስፍራ ፤ በማይረባ ሁኔታ እንዴት እንደዚህ ግጣሜን ላገኝ ቻልኩ ።
በሁለት ወር ከአስራምስት ቀን ዳግም ለሁለተኛ ቀን ተዋሰብን ፤ ያኔ ሰውነቴ ተቀብሏት
ነበር ፤ ሰውነቷ ተቀብሎኝ ነበር እናም ተዋሃድን ፤ የሚዋደዱ ሰዎች ሲዋሰቡ ወሲቡ
ውህደት ነው ፣ የነፍስ ቁርኝት ፤ ተቆራኘን።
ውድ ቦታ እና ቅዱስ ቦታ ብቻ ነው ትክክለኛ ሰው የሚገኘው ያለው ማነው? ህይወታችን የሚመዘነው በምናገኘው ደስታ ነው ።
ዛሬ አምናታለሁ ! የምትንዘላዘልበትን ምክንያት ደፍኜዋለሁ ፤ ፍቅሬ እንድትታመነኝ ሰርቷታል
። እንደትላንት እንዳልሸረሙጥ ከእሷ ጋ ያለኝ ነገር ይጋርደኛል ። ሰው መቼ በተገናኘበት ስፍራ ብቻ ይመዘናል ፤ ያለንበት ስፍራ ሁሌ መቼ ልካችን ሆኖ ያውቃል። አጀማመራችን ሳይሆን አካሄዳችን ነው የማንነታችን ማሳያ ። ይሄ በልባችን የተፃፈ የምንኖረው እውነት ነው ። ይሄን እውነት መግለፅ ረብ ለሌለው ትዝብት መጋለጥ ነው። ሁሉ እውነት አይነገርም። አንዳንዴ አንዳንድ ውሸት ከእውነት ይበልጣል ።

#Adhanom Mitiku

@yekaldebdabewoch