Get Mystery Box with random crypto!

¶ጥሎሽ °ተከታታይ ጽሑፍ(ምናባዊ ልቦለድ)° | የቃል ጠብታ

¶ጥሎሽ
°ተከታታይ ጽሑፍ(ምናባዊ ልቦለድ)°

(ከመኖር ብንሸራተትም
ልብሽ ደግፎኛልና አልወድቅም!)
ክፍል 2


እናቴ ከቤት ስትወጣ ገላዋን ፀሐይ ሲነካት ተሸሽጎ የነበረው ጥላ መሬት ላይ መሳል ጀመረ።

እንደ ጥላ ፈሪና እንደ ጥላ ክፉ አለ?

ጥላ አልወድም። በህይወቴ እንደ ጥላ የሚያስጠላኝ ነገር የለም። ለምንድነው ግን ሁሌም አብሮን ከማይሆን ጋር የምን'ሰፋው? ሁሌም ጉዟችን ወደ ማናገኘው የሚሆነው ለምንድነው? ወደማላገኘው ስጓዝ በእጄ የነበሩት ስንቱ ሻገተ? ለማግኘት ስሄድ ያጣሁት ፊቴ እየተደነቀረ መንገዴን የሚጋርድብኝ ሁኔታ ግራ ይገባኛል። ወደ ማጣት ግስጋሴ ብክነት...

ባለን ነገር ላይ እምነታችን የሳሳ ነው። ስስነት ደግሞ አንድ ቀን ይበጠሳል ወይ ይሰወራል።

በሩን ገርበብ አድርጋ እናቴ ወጣች። ሄደች። ምናለ በሩን በዘጋችው ወይ በከፈተቺው። ገርበብ ማለት ሲያስጠላ። ወደ አንዱ አለመሆን። መሃል ላይ መንገዋለል።

"መሌ አልተነሳህም እንዴ?" ፀሐይ ወጥታ(እናቴ) ፀሐይ ገባች(ርብቃ ገርበብ ያለውን በር ከፍታ)

"ስማ?"

ድምጿን ስሰማ የሆነ የማውቀው ስሜት ነፍሴን ሲያሽኮረምማት ከሰመመኔ ነቃሁ። ይህን ስሜት የት ነው የማውቀው?

"እህ መሌ!"

ካላየሁሽ የሰማሁሽ አይመስልሽማ? በብርድ ልብሴ እንደተጠቀለልኩ መለስኩላት።

"ትኩረትህ እኔ ጋር መሆኑን ለማወቅ እኮ ነው መሌ። መስማትማ ማንም ምንንም ይሰማል። ችግሩ ማድመጥን በመስማት ማሸሹ ላይ ነው። በል ተነስ! ጭራሽ ሻይ ቀድተህ ነው ትተኸው የተኛከው?" ጠረጴዛ ላይ ያለውን ሻይ በጣቶቿ እያነሳች...!

እማ ቀድታው ነው። ቀዘቀዘ እንዴ? ሳላውቀው ትንሽ ሸለብ አደረገኝ መሰለኝ። እስቲ ሞቅ አርጊልኝ።

"አንተን ሃሳብ እንጂ እንቅልፍ አይወስድህም! በል አሁን ተነስ ቤቱን ላስተካክለው!"

ርብቂዬ ትንሽ ብቻ ልተኛ!

ርብቂ አትበለኝ! ስንቴ ልንገርህ? ባንተ ምክንያት ይህን ስም ልጠላው ነው። እስከመቼ ነው ከዚህ ስም የምሸሸው? ንገረኝ እስከመቼ?

አንድ እግሩ በተንጋደደው ወንበር ላይ ልትቀመጥ ስትል አደናቅፏት በእጇ ጠረጴዛውን ስትደገፍ ሻዩ እላይዋ ላይ ፈሰሰ።

"የዚች ስም በተነሳ ቁጥር ሁሌ ችግር እንደተፈጠረ ነው። ባንተ ምክንያት የማላቃትን ሴት ልጥላ?" የረጠበ ቀሚሷን በጣቶቿ አደራርቃ መሬት ላይ ተቀመጠች።

አይኗ ውስጥ ናፍቆትና እልህ፣ ፍቅርና ጥላቻ፣ ከየዋህነት ጋር ተጋምደው ሲርመሰመሱ ሲቀጣጠሉ ህመም ያንገላታው እንባዋ በጉንጮቿ ላይ ኩልል ብሎ ወርዶ ከንፈሯ ውስጥ ተቀበረ። ለእንባዋ ሳታለቅስ እንባዋ ሞተ። እንባዋ ሲሞተ እንባዬ ተወለደ።

ምን ላርግ እሺ! ሁሉ ነገሬ ከትላንት ጋር ተሳስሮብኛል። ሮጬ አላመልጠው ነገር አቅም አጣሁ። ለኔ ከትላንት ውጪ ምን አለኝ? ከናፍቆት ውጪ ምን አለኝ? ረብቂዬ...

ስሟን አትጥራብኝ አልኩህ እኮ!" ከመቅጽፈት ከተቀመጠችበት ተነሳች። ከመሬት ተነስታ መሬት ላይ ቆመች። ከመሬት ወዴት ይሸሻል። "ክፉ ልታደርገኝ ነው እንዴ?"

እሺ ምን ላርግ?

"እኔ ብሌን ነኝ! እንደ ርብቃ ሳይሆን እንደ ብሌን ቅረበኝ!"

አልችልም! ድንገት ይህ ቃል ከአፌ ወጣ። አልችልም። ፊቷን ላለማየት ብርድ ልብሴን ተከናነብኩ። ሽሽት....


አልጨረስኩም ለነገሩ መች ጀመርኩና!


¶መላኩ ነኝ!
@yekal_tebta
@DBU111 Discussion
@Dbu11 Daily news
@dbu_entertain Entertainment on telegram

Subscribe our youtube channel

https://youtube.com/channel/UCAS829K6929J4CVsxrwsyzA
@dbudailyaskbot