Get Mystery Box with random crypto!

መንፈሳዊነት ከነፍስህ ውስጥ ተፈልቅቆ የሚገኝ እንጂ ከሃይማኖትህ ተቋም የሚሰጥህ አይደለም! (Ret | የሀሳብ መንገድ

መንፈሳዊነት ከነፍስህ ውስጥ ተፈልቅቆ የሚገኝ እንጂ ከሃይማኖትህ ተቋም
የሚሰጥህ አይደለም!
(Rethinking of your spirituality)
(እ.ብ.ይ.)
ብዙ ሰው በሕይወቱ ለሚገጥመው አስከፊ ሁኔታ አምላኩን ያማርራል፡፡ ሰው
በራሱ ስህተት ተጠያቂ የሚያደርገው ሌላ ሰውን ወይም አምላኩን ነው፡፡ ብዙ
ሰው ለራሱ ጥፋት ሃላፊነት መውሰድ አይፈልግም፡፡ ዓላማውን ሲያሳካና
ፈተናውን ሲያልፍ ራሱን ያደንቃል፤ ፈተናውን ሲወድቅ አልያም ከዓላማው
ሲደናቀፍ ግን ሌላ አካልን ያማርራል፡፡ ሐገራችን ዛሬ ለገጠማት ችግር፤
የእርስበርስ እልቂቱ፤ ለፖለቲከኞች የስልጣን ዙፋን ሲባል የሰው ደም
የሚፈሰው፤ ሐገር የሚተራመሰው ድግምት ስለነበረብን ወይም የአምላክ
ቁጣውን ስለገለፀብን አይደለም፡፡ ይሄ በራሳችን ያመጣነው የራሳችን ክፋት ነው፡፡
ሐቁን ዋጠው ወዳጄ!
ታላቁና ታዋቂው ህንዳዊ አባት ማህተመ ጋንዲ፡-
‹‹እግዚአብሔር ሃይማኖት የለውም›› ይላሉ፡፡
እውነት ነው! ጋንዲ ለዚህ አባባላቸው ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ በየትኛውም
ሃይማኖት ላይ ጥላቻ እንደሌላቸው ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን ሰውን ነፃ የሚያወጣው
ሃይማኖቱ ሳይሆን መንፈሳዊነቱ ነው ለማለት ነው፡፡ ሃይማኖት ጥቅም የለውም
እያሉን ሳይሆን ጥቅሙ ሁሉ መንፈሳዊ ለመሆን ካልሆነ ዋጋ የለውም እያሉን
ነው፡፡ ሰው መንፈሳዊ ሲሆን መንፈሳዊነቱ ውስጥ ምግባርና ግብር አለ፤
በውስጡ የሰውነት ፍሬዎች፣ የሞራል ከፍታዎች፣ የስነምግባር ዕውቀቶች
ሞልተውታል እያሉን ነው፡፡ ሃይማኖት ወደመንፈሳዊነት የሚወስድ መንገድ እንጂ
በራሱ መድረሻ አይደለምና፡፡
ድሮ ድሮ የተማረ ካልተማረው የሚሻለው በአስተሳሰቡ ነበር፡፡ ዛሬ ከተማረው
ይልቅ ያልተማረው የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጥንት ሃይማኖት ያለው ፈሪዓ
እግዚአብሄር እንዳለው ይቆጠራል፤ ስራው ክቡር እሱም የተከበረ ነበር፡፡ ዛሬ
አብዛኛው አማኝ አምላክን የሚፈራው በአፉ ነው፤ በስራው ግን የሚያመልከውን
አምላክ ተዳፍሯል፡፡ ሃይማኖትና አማኝ፤ ፈጣሪና የሰው ፍጥረት አልተገናኝቶም
እየሆኑ ነው፡፡ የሐገራችን ምስቅልቅል የሚያሳየን ይሄንኑ ነው፡፡ ነጋዴው በሸማቹ
ላይ ጨክኗል፡፡ ባለስልጣኑ የሚመራውን ሕዝብ እሱን ለማገልገል ለእሱ
እንደተፈጠሩ ተላላኪዎች አድርጎ ነው የሚያስበው፡፡ ሁሉም ሚናውን ስቶ
ከቦታው የለም፡፡ ሰውነቱን የጣለ ነው ዓለሙን የሞላው፡፡
አስራ አራተኛው የቲቤታውያን የእምነት አባት ሆነው እያገለገሉ ያሉት ዳላይ ላማ
እ.ኤ.አ. በ2011 ዓ.ም. ‹‹Beyond Religion›› በሚል ርእስ መፅሐፍ ፅፈው
ነበር፡፡ ሰውየው የእምነት አባት ቢሆኑም ሃይማኖት ብቻውን ሰውን ሊለውጥ
አለመቻሉን ያሰምሩበታል፡፡ ሰው ከሃይማኖቱ ባሻገር መጀመሪያ ራሱን ማወቅ፤
ሰውነቱን መረዳት እንዳለበት በመፅሐፋቸው አበክረው ይገልፃሉ፡፡ ሳይንስም
ቢሆን ምንም እንኳን የቁሳዊ ሕይወታችንን ችግሮች ቢፈታም የሰውን ውስጣዊ
ክፍተት ሊሞላ እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ሰው ለመሆን ሳይንሰም ሆነ ሃይማኖት በቂ
አይደሉም ይላሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸውን ሲያስረዱ አንደኛ ነገር አብዛኛው ሰው
ሃይማኖቱን በተግባር መከተል አቁሟል፡፡ ስለዚህ የዛሬው አማኝ ሃይማኖቱ
የሚያቀርበውን የስብዕና እና የስነምግባር ፍሬዎች መልቀም አይችልም፡፡ ሁለተኛ
ዓለም እርስበርሱ በሉላዊነት እየተያያዘ ስለመጣ ሰው የራሱን ሃይማኖት ብቻ ይዞ
ተገልሎ መኖር አይችልም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሣሌ አድርገው ያቀረቡት የራሳቸውን
ሕዝብ ትቤታውያንን ነው፡፡ ትቤታውያን ከዓለም ሕብረተሰብ ተነጥለው በተራራማ
ቦታዎች ተወስነው፤ በምንኩስና ዓለማቸው ፀንተው ለዘመናት ኑሯቸውን
ገፍተዋል፡፡ ዛሬ ግን ግሎባላይዜሽን መጥቶ የብቸኝነታቸውን ግርግዳ አፍርሶ
የዓለሙ አካል አድርጓቸዋል፡፡
ዳላይ ላማ በዚሁ መፅሐፋቸው ገፅ 3 ላይ፡-
‹‹እኔ የሃይማኖት ሰው ነኝ፡፡ ነገር ግን ሃይማኖት ብቻውን ችግሮቻችንን ሁሉ
አይፈታም፡፡ (I am a man of religion, but religion alone can not
answer all our problems)›› ይላሉ፡፡
እውነት ነው፡፡ ሰውየው ሃይማኖት አያስፈልግም እያሉ እንዳልሆነ መሰመር
አለበት፡፡ ራሱን የሚያውቅ፣ እምነትና ስራ ያለው፣ ተመራማሪ፣ ለችግሮቹ መፍትሄ
ማመንጨት የሚችል አማኝ፤ ሰውነቱን የተረዳ ሃይማኖተኛ ቢሆን ግን በራሱም
ሆነ በዓለሙ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላል ለማለት ነው፡፡ የብዙዎቻችን
ችግር ያለው በግለሰብ ደረጃ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ስብዕናውን ካጣ፣ ሞራልና
ስነምግባር ካነሰው፤ ሰውነቱን አውልቆ አውሬ ከሆነ ሃይማኖት ኖረው አልኖረው፤
ተማረ አልተማረ ለውጥ አያመጣም፡፡ የችግራችን አስኳል ያለው በእያንዳንዳችን
አስተሳሰብ ላይ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ሲሉን ነው፡፡
እኚሁ አባት ሃይማኖትንና መንፈሳዊነትን ለያይተው ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፡-
‹‹አብዛኛዎቹ የዓለማችን ሐይማኖቶች ስለፍቅር፣ ስለርህራሄ፣ ስለትዕግስት፣
ስለመልካምነት፣ ስለይቅርታና ምህረት ይሰብካሉ ያስተምራሉ፡፡ ሃይማኖቶች
የሰው ልጅ ውስጣዊ ዋጋው ከፍ እንዲል ያበረታታሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ ብቻ በቂ
አይደለም፡፡ ዛሬ ከሃይማኖተኝነት የበለጠ ስለመንፈሳዊነት የምናስብበት ጊዜ
ፊትለፊታችን ተደቅኗዋል፡፡ መንፈሳዊነት ከሃይማኖትም ከሳይንስም ከምናገኘው
የበለጠ ከፍ ያለ የስብዕና ከፍታ ላይ የሚያፈናጥጠን ነው፡፡ መንፈሳዊነት ማለት
የሰውነት ዋጋህን አውቀህ ሞራልና ስነምግባር፤ እምነትና ግብር ያለው ሰው
መሆነ ማለት ነው››
ወዳጄ ሆይ..... ሰው በጠፋበት ዓለም ሰው ሆኖ መገኘት ሊያስወግዝ፣ ከመንጋው
ሊነጥል፤ እጅ ሊያስጠቁም ቢችልም ከሰውነት በላይ ምንም የተሻለ ነገር
የለምና ሰው ለመሆን መልሰህ መላልሰህ አስብ፤ ደጋግመህ ራስህን ስራ፡፡
እንደገና ማሰብ ማርፈድ አይደለም፡፡ ከመቅረት ማርፈድ የተሻለ ነውና ራስህን
መልሰህ ለመስራት ትጋ፡፡ ራስን ማወቅ፣ ሰውነትን መረዳት፣ መንፈሳዊነትን
መያዝ፣ እምነትን በተግባር መግለፅ፤ የአፍ ብቻ ሰው አለመሆን ከችግራችን
የሚያላቅቀን፤ ከሐጢያታችን የሚያነጣን፤ ወደከፍታው የሚያወጣን መሰላል
ነው፡፡ ዛሬ ሰው ከቀልቡ አይደለም፡፡ ለመፋጀት የቸኮለ እንጂ ለይቅርታ የፈጠነ
የለም፡፡ ለማውገዝና ለመርገም እንጂ በፍቅር ለመቀበል የተዘጋጀ ሰው
ጠፍቷል፡፡ ዓለሙ በከንቱ ወሬ ጠፍቷል፡፡ አንተ ግን ከመንጋው ራስህን ነጥል፡፡
ሰው መሆንን ተማር፡፡ ሃይማኖትህን መርምር! እምነትህን አፅና፤ መንፈስህን ከፍ
አድርግ! መንፈሳዊነትህን አጥብቀህ ያዝ የዕለቱ ምርጥ መልዕክት ነው!
ራስህንም ዓለምህንም እንደገና አስብ! መንፈስህን አስውብ! መንፈሳዊነት የግል
ችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ነው!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!
ቸር መንፈስ!
____________
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

@yehasab_menged
@yehasab_menged