Get Mystery Box with random crypto!

ነፃና ብልህ መሆን ነፃነትን በማግኘት በኩል ስላለው ችግር ልነግራችሁ እወዳለሁ። ችግሩ ጥልቅ ጥ | የሀሳብ መንገድ

ነፃና ብልህ መሆን

ነፃነትን በማግኘት በኩል ስላለው ችግር ልነግራችሁ እወዳለሁ። ችግሩ ጥልቅ ጥናትና ግንዛቤ የሚፈልግ በጣም ውስብስብ ነዉ። ስለነፃነት፣ ስለሃይማኖት ነፃነት እና ያሹትና ማድረግ ስለሚቻልበት ነፃነት ብዙ እንሰማለን። ምሁራን ይህን ርዕሰ ጉዳይ ይዘው ብዙ መፃህፍትን ፅፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ እውነተኛው መፍትሄ በሚወስደን መልኩ በቀላሉና በቀጥታ ልንደርስበት እንደምንችል አስባለሁ፡፡

በምዕራብ አቅጣጫ ፀሃይዋ ልትጠልቅ ስትቃረብና ዓይናፋሯ ጨረቃ ከዛፎቹ በላይ ብቅ ስትል አስተውላችሁ ታውቃላችሁ? አብዛኛውን ጊዜ በዚያ ሰዓት ወንዞች በጣሙን ይረጋሉ፤ ሁሉም ነገር በላያቸው ላይ ይንፀባረቃል - ድልድዩ፣ በላዩ ላይ የሚያልፈው ባቡር፣ አስደናቂዋ ጨረቃ፣ በኋላ ላይ ብቅ የሚሉት ከዋክብት:: ኩነቱ እጅግ ውብ ነው። እንዲህ አይነቱን ውበት ለማስተዋል፣ ለመመልከት፣ በሙሉ ትኩረት ለማጤን አዕምሮ ነፃ መሆን አለበት፡፡ በችግሮች፣ በስጋቶች፣ በግምቶች መሞላት የለበትም። እንዲያ ሲሆን ብቻ ነው አዕምሮ ተረጋግቶ ማስተዋልና እጅግ ልዩ የሆነውን ውበት ማድነቅ የሚችለው።
ምናልባትም የነፃነት ችግራችን የሚፈታው በዚህ መልኩ ሳይሆን አይቀርም።

ነፃ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ነፃነት ማለት የሚፈልጉት ማድረግ፣ ወደፈለጉበት መሄድ፣ የፈቀዱትን ማሰብ ይሆን? ከጥገኝነት መላቀቅ ማለት ነፃነት ነውን? በዓለም ላይ ከጥገኝነት የተላቀቁ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ነፃ የሆኑት ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ነፃነት ትልቅ ብልህነትን ይፈልጋል ፤ ነፃ መሆን ማለት ብልህ መሆን ማለት ነው። ነገር ግን ነፃ መሆንን በመሻት ብቻ ብልህነት አይመጣም፡፡ ብልህነት የሚመጣው ጠቅላላ አካባቢያችሁን፣ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ቤተሰባዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎቻችሁን መገንዘብ ስትጀምሩ ነው። የተለያዩ ተፅዕኖዎችን ምንነት ለመረዳት - የወላጆችን፣ የመንግስትን፣ የማህበረሰብን፣ የባህልን፣ የእምነትን፣ የአምልኮን፣ ሳያስቡ የገቡበትን ባህል ተፅዕኖዎች- እነዚህን ሁሉ ተገንዝቦ ከእነዚህ ነፃ ለመሆን ጥልቅ ምልከታ ያስፈልጋል፡፡ሆኖም በውስጣችሁ ፍርሃት ስላለ በቀላሉ አትላቀቋቸውም። በህይወታችሁ ትልቅ ስፍራ አናገኝ ይሆናል ብላችሁ ትፈራላችሁ፤ ካህኑ አንድ የሆነ ነገር ይሉናል ብላችሁ ትፈራላችሁ፤ ባህሉን አልተከተልን፣ ትክክለኛውን ነገር አልፈፀምን ይሆን ብላችሁ ትፈራላችሁ። ነፃነት ፍርሃት ወይም አስገዳጅ ነገር የሌለበት፣ የደህንነትና የዋስትና ጥያቄ የማይነሳበት አዕምሯዊ ሁኔታ ነው፡፡

አብዛኞቻችን ደህንነታችን እንዲጠበቅ አንፈልግምን? ሰዎች ስለ ውበታችን፣ ስለመልካችን ወይም ስለእውቀታችን - እንዲነግሩን አንፈልግምን? እንዲህ አይነት ነገሮች የእርግጠኝነት ስሜት፣ የተፈላጊነት ስሜት ይፈጥሩብናል። ሁላችንም ዝነኞች መሆን እንፈልጋለን፡፡ ይሁንና አንድ ነገር በሆንን ቅፅበት ነፃ መሆናችን ያቆማል።

የነፃነትን ችግር ለመገንዘብ እውነተኛው ፍንጭ ይህ ነውና ይህንን በአፅንኦት ተመልከቱት፡፡ በዚህ የፖለቲከኞች፣ የስልጣን፣ የማዕረግና የደረጃ ዓለምም ሆነ ደግ፣ ሩህሩህ፣ ቅዱስ ለመሆን በምትመኙበት መንፈሳዊ ዓለም አንድ የሆነ ሰው ለመሆን ባሰባችሁ ቅፅበት ነፃ መሆናችሁ ይቀራል፡፡ የእነዚህን ነገሮች አይረቤነት የተገነዘበ፣ ልቡ ንፁህ የሆነና አንድ ሰው ለመሆን ምኞት የሌለው ሰው ነፃ ነው፡፡ የነገሩን ቀላልነት ከተገነዘባችሁ እጅግ የተለየ ውበቱንና ጥልቀቱን ታያላችሁ::

በትምህርት ውስጥ የሚገኙ ፈተናዎች አላማም ይኸው ነው - አንድ ደረጃ መስጠት፣ አንድ የሆነ ሰው ማድረግ፡፡ ማዕረጎች፣ ደረጃዎችና ዕውቀት አንድ የሆነ ሰው እንድትሆኑ ያበረታቷችኋል። ወላጆቻችሁና መምህራኖቻችሁ በህይወታችሁ አንድ ቦታ ላይ እንድትደርሱ፣ እንደ አጎታችሁ ወይም እንደ አያታችሁ ስኬታማ እንድትሆኑ ነግረዋችሁ አያውቁም? ታድያ አንድን ጀግና ወይም አንድን መምህር ለማስመስል ስትሞክሩ ነፃ አይደላችሁም:: የአንድን መምህር ወይም ወዳጅ ምሳሌ ከተከተላችሁ ወይም አንድ የሆነ ባህልን የምትከተሉ ከሆነ በውስጣችሁ አንድ የሆነ ነገር እንድትሆኑ ያስገድዳችኋል፡፡ ይህን ሃቅ ከተገነዘባችሁ ብቻ ነፃ ትሆናላችሁ፡፡

የትምህርት ዓላማ ከልጅነታችሁ ጀምሮ ሌሎችን እንዳታስመስሉ፣ ሁልጊዜም ራሳችሁን እንድትሆኑ ማስተማር መሆን አለበት- ምክንያቱም አስቀያሚም ሆናችሁ ቆንጆ፣ የዋህም ሆናችሁ ቀናተኛ ራስን መሆን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ራስን መሆን አስቸጋሪ የሆነበት ምክንያት አሁን ባላችሁበት ሁኔታ የማይረቡ እንደሆናችሁ ስለምታስቡ ነው፤ ራሳችሁን ስትለውጡ ብቻ የተሻላችሁ እንደምትሆኑ ታስባላችሁ፤ ነገር ግን ይህ አይከሰትም:: ይሁን እንጂ እውነተኛ ማንነታችሁን ከተመለከታችሁትና ከተገነዘባችሁት አንድ ለውጥ እንዳለ ማየት ትችላላችሁ። ስለዚህም ነፃነት የሚገኘው አንድ የተለየ ሰው ለመሆን በመጣር ወይም የሻቱትን ነገር በማድረግ ወይም የባህልን፣ የወላጆችን፣ የመምህርን ትዕዛዝ በመከተል ሳይሆን ከአንዱ ቅፅበት እስከ ቀጣዩ ቅፅበት ማንነትን በመረዳት ነው::

እርግጥ ያ ይህን እንድታደርጉ አልተማራችሁም፤ የእናንተ ትምህርት አንድ ነገር እንድትሆኑ ነው የሚያበረታታችሁ፡፡ ይህ ግን ራስን መገንዘብ አይደለም፡፡ የእናንተ «ማንነት» በጣም ውስብስብ የሆን ነገር ነው፡፡ ወደትምህርት ቤት የሚሄደው፣ የሚጣላው፣ ጨዋታ የሚጫወተው፣ የሚፈራው ይህ አካል አይደለም ፤ አንድ ሌላ የተደበቀ ግልፅ ያልሆነ ነገር አለ፡፡ የምታስቡት ነገር ብቻ ሳይሆን በአዕምሯችሁ ውስጥ የተቀመጠው ነገር በሙሉ በሌሎች ሰዎች፣ በመፃህፍት፣ በጋዜጦች፣ በመሪዎቻችሁ የገባ ነው፡፡ ይህንን የምትገነዘቡት አንድ የሆነን ሰው ለመሆን ሳትፈልጉ ስትቀሩ፣ ማስመሰላችሁን ስታቆሙ፣ መከተላችሁን ስትተው ማለትም አንድ የሆነ ነገር እንድትሆኑ የሚገፋፋችሁን ባህል በሙሉ ስትቃወሙ ብቻ ነው:: እጅግ ልዩ ወደሆነው ነፃነት የሚመራው አብዮት ብቻ እውነተኛ ነው፡፡ የትምህርት ዓላማም ይህን ነፃነት መኮትኮት መሆን አለበት፡፡

ወላጆቻችሁ፣ መምህሮቻችሁ እና የራሳችሁ ፍላጐቶች አንድ ልዩ ሰው እንድትሆኑ ወይም ደስተኛና አስተማማኝ እንድትሆኑ ይፈልጋሉ። ታድያ ብልህ ለመሆን እስረኞች እንድትሆኑና እንድትጠፉ ምክንያት የሚሆኑት ተፅዕኖዎች በሙሉ መጥፋት ያለባቸው አይመስላችሁምን?

የአዲሱ ዓለም የመምጣት ተስፋ ሃሰተኛውን ነገር ለይተው በቃላት ሳይሆን በተግባር መቃወም በሚጀምሩ ሰዎች እጅ ውስጥ ነው። ለዛም ነው ትክክለኛው ትምህርት የሚያስፈልጋችሁ፡፡ በነፃነት ስትበለፅጉ ብቻ በባህል ላይ ያልተመሰረተ ወይም በአንድ ፈላስፋ ወይም ሃሳባዊ አስተሳሰብ ያልተቀረፀ አዲስ ዓለም መፍጠር ትችላላችሁ፡፡ አንድን ሰው ለመሆን ስትፈልጉ ወይም አንድን ሰው እንደ አብነት ወስዳችሁ እሱን ለማስመሰል ስትሞክሩ ነፃነት አይኖርም፡፡

ምንጭ ፦ ውስጣዊን ማንነት ማወቅ
ደራሲ :- ክሪሽና ሙርቲ
ተርጓሚ ፦ ተስፋሁን ምትኩ

@yehasab_menged
@yehasab_menged