Get Mystery Box with random crypto!

ጦርነት የምናባዊ ተረክ ውጤት ነው!! #repost በአለም ታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ ለተሳሳተ ምናባ | የሀሳብ መንገድ

ጦርነት የምናባዊ ተረክ ውጤት ነው!!
#repost

በአለም ታሪክ ውስጥ የሰው ልጅ ለተሳሳተ ምናባዊ ተረክ ብዙ የህይወት መስዋአትነትን ከፍሏል።ለምናባዊ ተረኮቻችን ብለን ትልቅ ዋጋ በከፈልን ቁጥር ደግሞ ተረኩ ይበልጥ እየጠነከረ መሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ለከፈልናቸው ዋጋዎችና ላደረስነው ጉዳት ትርጉም መስጠትን አብዝተን እንሻለን።

በፖለቲካ ቋንቋ ይህ 'ልጆቻችን በከንቱ አልሞቱም' የሚባል አባዜ ነው። በ1915 ዓ.ም. ጣሊያን የወዳጅነት ሀገራቱን በመቀላቀል ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገባች። ጣሊያን ዓላማዬ ብላ የተነሣችው በኦስትሪያ-ሀንጋሪ ግዛት ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የተነጠቁትን ትሬንቶና ትሪስቴ የተባሉ ሁለት የጣሊያን ግዛቶችን ነፃ ለማውጣት ነበር። የጣሊያን ፖለቲከኞች ፓርላማ ውስጥ ታሪክን ለማስተካከልና ታላቋን ሮም ዳግም ለመመለስ ቃል በመግባት ሳቢ የሆኑ ንግግሮችንአደረጉ።በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩጣልያናዊያን“ለትሬንቶና ለትሪስቴ!” እያሉ በመፎከር ወደ ግንባር ነጎዱ። በቀላሉ ድል እንደሚያደርጉ አስበው ነበር።

የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር። የኦስትሪያ-ሀንጋሪ ጦር በኢሶንዞ ወንዝ ዙሪያ ጠንካራ የመከላከያ መሥመር አቁመው ጠበቋቸው። ጣሊያኖቹ ራሳቸውን ደም አፋሳሽ በሆኑ ዐሥራ አንድ ውጊያዎች በመክተት ከጥቂት ኪሎሜትሮች ያልበለጠ ስፍራ መቆጣጠር ቢችሉም ድል ሊያደርጉ አልቻሉም። በመጀመሪያው ውጊያ የ5 ሺህ፤ በሁለተኛው ደግሞ የ40 ሺህ ወታደሮችን ነፍስ ገበሩ። በሦስተኛው ውጊያ 60 ሺህ ወታደሮችን አጡ። ለሁለት አሰቃቂ ዓመታት እንዲህ ከቀጠለ በኋላ በዐሥራ አንደኛው ዙር ኦስትሪያዊያን በመጨረሻ የመልሶ ማጥቃት ጀምረው በካፖሬቶ ጦርነት ጣሊያኖችን በማሸነፍ እስከ ቬኒስ መግቢያ ድረስ መልሰው አባረሯቸው፡፡ ታላቁ ዘመቻ የደም ገንዳ ሆኖ አረፈው። ጦርነቱ ሲጠናቀቅ 700,000 የጣሊያን ወታደሮች ሲገደሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆሰሉ።


የጣሊያን ፖለቲከኞች ከኢሶንዞ ጦርነት ሽንፈት በኋላ ሁለት አማራጭ ነበራቸው። መሳሳታቸውን አምነው ከኦስትሪያ-ሀንጋሪ ጋር የሰላም ስምምነት ይፈርማሉ። ኦስትሪያ ሀንጋሪ ጣሊያን ላይ የይገባኛል ጥያቄ ስለሌላቸው የሰላም ስምምነቱን ለመፈረም ደስተኛ ይሆኑ ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ይበልጥ ጠንካራ ከሆኑት ከሩሲያዊያን የሞት ሽረት እያደረጉ ነበር። ሆኖም ፖለቲከኞቹ ወደ 15 ሺህ የሟች ወታደር ወላጆች “ሚስቶችና ልጆች ጋር በመሄድ “ይቅርታ ስሕተት ሰርተናል። ብዙም አትዘኑ፤ ግን የእናንት ጂኦቫኒና ማርኮ የሞቱት በከንቱ ነበር” አሊያም “ጂኦቫኒና ማርኮ ጀግኖት ነበሩ! የሞቱት ትሪስቴ የጣሊያን ግዛት እንድትሆን ብለው ስለሆነ ደማቸው በከንቱ ፈሶ እንዳይቀር እናደርጋለን፤ ድል የኛ እስክትሆንም እንፋለማለን!” ሊሏቸው ይችላሉ። እንደሚገመተው ፖለቲከኞቹ ሁለተኛውን አማራጭ በመምረጣቸው ሌላ ጦርነት ውስጥ ገብተው 40,000 ተጨማሪ ወታደሮች ሞቱ። ፖለቲከኞቹ አሁንም ቢሆን ውጊያውን መቀጠል መረጡ፤ ምክንያቱም "ልጆቻችን በከንቱ አልሞቱምና።"

ሆኖም ፖለቲከኞቹን ብቻ ልንወቅስ አንችልም። ብዙ ሕዝብም ጦርነቱን እየደገፈው ነበር። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጣሊያን ድንበሮቹን መልሳ ማግኘት አልቻለችም። የጣሊያን ዴሞክራሲም “ሀገሪቱ ለከፈለችው መሥዋዕትነት በሙሉ ካሳ እንድታገኝ እናደርጋለን” ያለውን ቤኒቶ ሙሶሊኒና ፋሺስት ጭፍሮቹን የበላይ አድርጎ አስቀመጠ። ለወላጆች ልጃቸው ያለ በቂ ምክንያት ሕይወቱን እንዳጣ መንገር ፖለቲከኞቹ ቢከብዳቸውም ወላጆች ይህንን ለራሳቸው መንገር ይበልጡኑ ይከብዳቸዋል፤ ለተጎጂው ደግሞ ከዚያም የባሰ ነው። በጦርነት እግሩ ተቆርጦ አካል ጉዳተኛ የሆነ አንድ ወታደር ለራሱ “የገዛ አካሌን መሥዋዕት
ያደረግኩት ለዘለዓለማዊቷ ሀገሬ ጣልያን ክብር ነው” ሲል ይመርጣል እንጂ “በሞኝነት ራስ ወዳድ የሆኑ ፖለቲከኞችን በማመኔ የገዛ እግሬን አጣሁ” ሊል አይችልም። ምናባዊ ታሪክን ተቀብሎ መኖር እጅግ ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ለስቃያችን ትርጉም ይሰጣልና።

ካህናት ይህንን ሕግ የተረዱት ከሺህ ዓመታት በፊት ነው። ይህ በርካታ ሃይማኖታዊ ስርዓቶችንና ትእዛዛትን የሚያድበሰብስ ነው። ሰዎች እንደ ሀገርና አማልክት ባሉ ምናባዊ አካላት ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ከፈለጋችሁ ዋጋ የሚሰጡትን አንድ ነገር መሥዋዕት እንዲያደርጉ ልታደርጓቸው ይገባል። መስዋዕቱ ከባድ በሆነ ቁጥር ሰዎች በመሥዋዕት ተቀባዩ ህልውና ላይ ያላቸው እምነት ይበልጥ ይጠነክራል። ለጁፒተር ውድ ንብረቱ የሆነ በሬውን የሚሰዋ አንድ ምስኪን ገበሬ፤ ጁፒተር ስለሚባል አምላክ ህልውና ያምናል። እንደዚያ ካልሆነ ድድብናውን በሌላ በምን ያሳብባል? ገበሬው ከዚህ ቀደም የሰዋቸው በሬዎች ባክገው እንዳልቀሩ ራሱን ለማሳመን ሌላ በሬ፣ እንደገና ሌላ በሬ፣ አሁንም ሌላ በሬ ለመሥዋዕት ያቀርባል። በተመሳሳይ ምክንያትም ለጣሊያን ክብር ስል ልጄን መሥዋዕት ካደረኩኝ ወይንም ለኮሚኒስታዊ አብዮት ስል እግሬ ከተቆረጠ፤ ይህ እኔን ወደ አክራሪ የጣሊያን ብሔረተኛ ወይም ወደ ኮሚኒስትነት ለመለወጥ በቂ ምክንያት ነው። የጣሊያን ብሔረተኝነት ትርክቶች ወይም የኮሚኒስት የፕሮፓጋንዳ ውሸት ሆነው ከተገኙ ልጄ በሞት የተነጠቀብኝ ወይም አካል ጉዳተኛ የሆንኩት ትርጉም ለሌለው ነገር እንደሆነ ለማመን እገደዳለሁ። ይህንን ለመቀበል ድፍረቱ ያላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው።


በዚህ ወጥመድ ውስጥ የሚወድቁት መንግሥታት ብቻ አይደሉም። የንግድ ኩባንያዎች አክሳሪ የሆኑ ሥራዎች ላይ ሚሊዮኖችን ያፈሳሉ፣ ግለሰቦች ደግሞ ጤናማ ያልሆነ ትዳራቸው ላይ የሙጢኝ ብለው ይቀራሉ ወይም እድገት በማያገኙበት ሥራ ላይ እድሜ ልክ ይቆያሉ። ተራኪው እኔነት(ኢጎ) ያለፈ ስቃያችን ምንም ትርጉም እንዳልነበረው ላለመቀበል ሲል ብቻ ወደፊትም እየተሰቃየን እንድንቀጥል ይፈልጋል። ካለፉ ስሕተቶቻችን ራሳችንን ለማውጣት ከፈለግን ተራኪ እኔነታችን እነኚህ ስሕተቶች ውስጥ ትርጉም የሚሸጉጥ አንድ ማምለጫ ታሪክን ይፈጥራል።

ሆሞ ዲየስ(ገፅ 81-83)
ኖኀ ሀራሪ

ይሄን ሀሳብ አሁን ወዳለው የሀገራችን ቀውስ እናመጣው። ህውሀት የትግራይ ህዝብ ላይ በቀላሉ የማይፋቅ የተዛባ 'ምናባዊ ተረክ' ፈጥሯል።እናም ይህም ተረክ" ትግራይ ነፃ እና ታላቅ ሀገር ትሆናለች ነገር ግን ጠላቶች ከበውሀል ከጠላቶችህም ነፃ የማወጣህ እኔ ነኝ።ለነፃነትህም ልጆችህን ሰውተሀል የልጆጅህም ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም እና ድል የኛ እስክትሆንም እንፋለማለን!”
የሚል ይመስላል።

ለተሳሳተ ምናባዊ ተረክ ብዙ የህይወት መስዋአትነትን ባስከፈላቸው ቁጥር ተረኩ ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ምክንያቱም ለከፈሉት ዋጋና ለደረሰው ጉዳት ትርጉም መስጠትን ይፈልጋሉ።ህዝቡም በጦርነቱ አሸናፊ እንደማይሆን እያወቀው። ጦርነቱን ቢያሸንፍም አትራፊ እንደማይሆን እየተረዳው ልጆቻችን በከንቱ አልሞቱም በሚል አባዜ ትርጉም ለሌለው ጦርነት ራሱን ይማግዳል።ይህም የማያባራ እልቂትን በመፍጠር ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ያኖራል።

@yehasab_menged
@yehasab_menged