2022-08-31 09:51:00
ሁለት ሰዎች ብቻ በጀማዐ ሲሰግዱ ተከታዩ ከኢማሙ ትንሽ ወደ ኋላ መሆን ልክ ነው?
~
ሁለት ሰዎች ብቻ ጀማዐ ሶላት የሚሰግዱ ከሆነ ተከታዩ ከኢማሙ ትንሽ ወደ ኋላ ሆኖ ሲቆም ማየት የተለመደ ነው። በርግጥ ይህንን የመረጡ ዓሊሞች አሉ። ይሁን እንጂ ትክክለኛው አፈፃፀም ተከታዩ ከኢማሙ ጋር እኩል ሆኖ መቆሙ ነው። ኢማሙል ቡኻሪ ረሒመሁላህ በሶሒሕ ኪታባቸው ውስጥ እንዲህ የሚል ርእስ አስፍረዋል፦
" يَقُومُ عَنْ يَمِينِ الإمَامِ بحذائهِ سواءً، إذا كَاناَ اثْنَيْن".
“ከኢማሙ በቀኙ በኩል እኩል ሆኖ ይቆማል፣ ሁለት ከሆኑ።”
ከዚያም ተከታዩን የኢብኑ ዐባስን ረዲየላሁ ዐንሁማ ሐዲሥ አስፍረዋል፦
"بِتُّ فِي بَيْتِ خَالَتِي مَيْمُونَةَ، فَصَلَّى رَسُولُ اللَّهِ ﷺ العِشَاءَ، ثُمَّ جَاءَ فَصَلَّى أَرْبَعَ رَكَعَاتٍ، ثُمَّ نَامَ، ثُمَّ قَامَ، فَجِئْتُ فَقُمْتُ عَنْ يَسَارِهِ، فَجَعَلَنِي عَنْ يَمِينِهِ،... "
“ከየሹማዬ መይሙና ዘንድ አድሬ ነበር። የአላህ መልእክተኛ ﷺ ዒሻእን ሰገዱ። ከዚያም (እቤት) መጡና አራት ረከዐዎችን ሰገዱ። ከዚያም ተኙ። ከዚያም ለሶላት ቆሙ። በግራቸው በኩል ቆምኩኝ። በቀኛቸው አደረጉኝ።...” [ቡኻሪ፡ 697]
“ይሄ የኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁማ ሐዲሥ እኩል ሆኖ መቆምን ያስጨብጣል ወይ?” ከተባለ “አዎ” ነው መልሱ። ኢብኑ ሐጀር ረሒመሁላህ “ከቀኝ ጎናቸው አደረጉኝ” የሚለውን የኢብኑ ዐባስን ንግግር ሲያብራሩ “ጉልህ መልእክቱ እኩል ሆኖ መቆም ነው” ብለዋል።
የቡኻሪን ርእስ አስመልክተውም እንዲህ ብለዋል፦
በዚህ ርእስ አሰጣጣቸው የፈለጉት በሶላት ውስጥ ኢማምና ተከታይ ብቻቸውን ከተገኙ ተከታዩ ከኢማሙ በቀኝ ጎን እኩል ሆኖ ማለትም በመቆሚያው ቦታ ላይ መቀደምም ሆነ መዘግየት ሳይኖር እኩል መሆናቸው ነው።” [ፈትሑል ባሪ፡ 6/197]
.
በሌላ ዘገባ ላይም ኢብኑ ዐባስ ረዲየላሁ ዐንሁ እንዲህ ብለዋል፦
" أَتَيْتُ رَسُولَ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ مِنْ آخِرِ اللَّيْلِ، فَصَلَّيْتُ خَلْفَهُ، فَأَخَذَ بِيَدِي، فَجَرَّنِي، فَجَعَلَنِي حِذَاءَهُ، فَلَمَّا أَقْبَلَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ عَلَى صَلاتِهِ، خَنَسْتُ، فَصَلَّى رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ، فَلَمَّا انْصَرَفَ قَالَ لِي: مَا شَأْنِي أَجْعَلُكَ حِذَائِي فَتَخْنِسُ؟
فَقُلْتُ: يَا رَسُولَ اللهِ! أَوَيَنْبَغِي لِأَحَدٍ أَنْ يُصَلِّيَ حِذَاءَكَ، وَأَنْتَ رَسُولُ اللهِ الَّذِي أَعْطَاكَ اللهُ؟
قَالَ: فَأَعْجَبْتُهُ، فَدَعَا اللهَ لِي أَنْ يَزِيدَنِي عِلْمًا وَفَهْمًا... "
“የአላህ መልእክተኛ ﷺ ዘንድ የሌሊቱ መጨረሻ ላይ መጣሁኝ። ከኋላቸው ልሰግድ ቆምኩኝ። እጄን ይዘው በመጎተት ከሳቸው ጎን ትይዩ አቆሙኝ። የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶላታቸው ላይ ሲያተኩሩ ጊዜ ወደኋላ አልኩኝ። የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሰገዱ። ባጠናቀቁ ጊዜ፦ ‘ምነው? እኔ በጎኔ ሳደርግህ ወደኋላ ትላለህሳ?’ አሉኝ።
‘የአላህ መልእክተኛ ሆይ! በአንተ ትይዩ ሆኖ ለማንስ ሊሰግድ ይገባዋልን? አንተ አላህ ያደለህ የአላህ መልእክተኛ ሆነህ ሳለ?’ አልኳቸው። ገረምኳቸው። እውቀትንና ግንዛቤን እንዲጨምረኝ አላህን ለመኑልኝ።” [አሶሒሐህ፡ 6/174 - 175]
ከጃቢርም ተመሳሳይ መልእክት ተላልፏል። [ሙስሊም፡ 3010]
በተጨማሪም ዐብዱላህ ብኑ ዑትባህ ብኒ መስዑድ እንዲህ ብለዋል፦
دخلت على عمر بن الخطاب رضي الله عنه بالهاجرة «فوجدته يسبح، فقمت وراءه. فقربني حتى جعلني حذاءه عن يمينه»
“ዑመር ብኑል ኸጧብ ረዲየላሁ ዐንሁ ዘንድ ቀትር ላይ ስገባ ሱና እየሰገዱ አገኘኋቸው። ከኋላቸው ቆምኩኝ። በቀኛቸው በኩል አድርገው አቀረቡኝ።” [ሙወጦእ ማሊክ፡ ሐዲሥ ቁ. 364]
.
አልሓፊዝ ኢብኑ ረጀብም ረሒመሁላህ እንዲህ ብለዋል፦
" الإمام إذا لم يأتم به غير واحد، فإنه يقيمه عن يمينه بحذائه، ولو كان صبيا لم يبلغ الحلم. وهذا كالإجماع من أهل العلم.
وقد حكاه الترمذي فِي "جامعه" عَن أهل العلم من أصحاب النّبيّ - صلّى الله عليه وسلّم - فمن بعدهم، قالوا: إذا كان الرّجل مع الرّجل يقوم عن يمين الإمام. وحكاه ابن المنذر عَن أكثر أهل العلم... "
“አንድ ኢማም ከአንድ ሰው ውጭ የሚከተለው ከሌለ በቀጥታ ከቀኙ በኩል ሊያቆመው ይገባል። ለአቅመ ሃላፊነት ያልደረሰ ህፃን ቢሆን እንኳ። ይሄ የእውቀት ባለቤቶች ዘንድ ልክ እንደ ኢጅማዕ ነው። ቲርሚዚ በጃሚዐቸው ውስጥ ከነብዩ ﷺ ባልደረቦች እና ከነሱ በኋላ ከመጡ አዋቂዎች ጠቅሰውታል። አንድ ሰው ከአንድ ሰው ጋር ብቻ ከሆነ ከኢማሙ ቀኝ ይቆማል ብለዋል። ኢብኑል ሙንዚርም ከብዙ የእውቀት ባለቤቶች ጠቅሰውታል።” [ፈትሑል ባሪ፡ 6/197 – 198]
በተጨማሪም ኢብኑ ጁረይጅ ረሒመሁላህ “ 'አንድ ሰው ከአንድ ሰው ጋር ብቻ ሆኖ የሚሰግድ ከሆነ ከየት በኩል ነው የሚሆነው?' ብየ ዐጧእን ጠይቄ ነበር” ይላሉ።
ዐጧእ፦ “በቀኙ በኩል” አሉ።
ኢብኑ ጁረይጅ፦ “አብሮት እስከሚሰለፍ ድረስ በሱው አቅጣጫ ነው የሚሆነው? አንዱ ሌላውን ሳይቀደም?”
ዐጧእ፦ “አዎ!”
ኢብኑ ጁረይጅ፦ “በመሃላቸው ክፍተት እስከማይኖር ድረስ?
ዐጧእ፦ “አዎ!” [ሙሶነፉ ዐብዲረዛቅ፡ ቁ. 3870]
ስለዚህ ሁለት ሆነው በሚሰግዱ ጊዜ ከኢማም ትንሽ ወደ ኋላ መቅረት ምንም እንኳ የደገፉት ዓሊሞች ቢኖሩም ማስረጃ የሚደግፈው ግን አይደለም። ይህንን ማድረግ የተወደደ ቢሆን ኖሮ ተጨባጭ መረጃ ከነብዩ ﷺ ይተላለፍ ነበር። ነገር ግን የለም። ከሶሐቦችም ይገኝ ነበር። ይህም የለም። መረጃ አለመኖሩ መሰረት እንደሌለው ያሳያል። እንደሚታወቀው ነብዩ ﷺ “ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ” ብለዋል። [ቡኻሪ፡ 631] የሳቸው አሰጋገድ ውስጥ ደግሞ ከአንድ ተከታይ ጋር ብቻ ሆነው በሰገዱበት ላይ ትንሽ የተቀደሙበት አልተገኘም። ይልቁንም የተገኘው ከዚህ በተለየ እኩል ጎን ለጎን መቆም ነው። ይሄኛው አቋም ከዘመናችን ዓሊሞች ውስጥ የኢብኑ ባዝ፣ የአልባኒይ እና የኢብኑ ዑሠይሚን አቋም ነው።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor
132 views06:51