Get Mystery Box with random crypto!

ዱኒያ ▬ ▬ ▬ «ዱኒያ ማለት ፈተና የበዛበት የውሸት አለም ነች፣ በአጭሩ ይች ዱንያ ማለት | Yasin Muhammed - Official Channel✔

ዱኒያ
▬ ▬ ▬
«ዱኒያ ማለት ፈተና የበዛበት የውሸት አለም ነች፣ በአጭሩ ይች ዱንያ ማለት ወደ አኼራ የምንሸጋገርባት አጭር ድልድይ ነች»!!
||
አንድ ኡስታዝ ዱኒያን ሲገልፅ የማረሳውን አገላለፅ ላካፍላችሁ እንዲህ አሉ:-

ዱንያን ሲመስላት «ዱኒያ ማለት አደባባይ ላይ የቆመች ቆንጆ ሴት ነች! አንዱ መጥቶ በቁንጅናዋ ተማርኮ "ላግባሽ ይላታል" እርሷም እሺ! ትለዋለች። ቆንጆይቱ የቆመችው አደባባይ ላይ ነው ሁሉም ያያታል! በመቀጠልም ሌላኛው መጣ፤ እርሱም "ላግባሽ" ይላታል። እርሷም እሺ! አግባኝ የሚል መልስ ለሁሉቱም ትሰጣለች። በዚህ ግዜ ሁለቱ ሰዎች አደባባይ ላይ ባለችው ቆንጆ ይጣላሉ።
*
ይህንንም ተከትሎ ወደ ፍርድ ቤት ያቀናሉ። ፍርድ ቤት ቀረቡ። ዳኛውም በምን ተጣልታችሁ ነው እዚህ የመጣችሁት ይላቸዋል። መጀመሪያ ላይ ላግባሽ ያላት እንዲህ አለ "እኔን እንደምታገባኝ ከእኔ ጋር ቃል ገብታ ነገር ግን ይኸኛው በእኔ ላይ ጣልቃ ገብቶብኝ ነው የተጣላነው" የሚል ክሱን አቀረበ። ዳኛውም እስኪ አንድ ግዜ ሁለታችሁም ውጭ ቆዩ እርሷንም በምን እንደተጣላችሁ ልጠይቃት ይላቸዋል።
እነርሱም ተያይዘው ወጡ።
*
ዳኛው በቁንጅናዋ ተማርኮ፤ ቆንጆዋን "ለምን ከዚህ ሁሉ እኔ አላገባሽም" ይላታል። እርሷም እሺ! ትለዋለች።

በዚህም ምክንያት ሊካሰሱ የመጡትና ዳኛው በልጅቱ ይጣላሉ።
ነገር ግን በዚህ መሀል እርሷ እንዲህ አለች:- "ከዚህ ሁሉ ሶስታችሁንም የሚያስታርቅ ሀሳብ አለኝ ከተስማማችሁ?" ትላቸዋለች።
*
" እኔ ወደፊት እሮጣለሁ እናንተ ከሗላ ተከተሉኝ፤ እኔን መጀመሪያ የያዘኝ ያገባኛል ነገር ግን በዚህም ውስጥ አንድ መስፈርት አለኝ፤ እርሱም ስትሮጡ እኔን ብቻ ተመልከቱ ወደ ጎን መዞር፣ እርስ በእርስ መተያየት አይቻልም ይህ ነው ሀሳቤ" ትላቸዋለች። በዚህ ሀሳቧም ይስማማሉ።
*
ሩጫውም ተጀመረ እርሷ ላይ ለመድረስ ሲሮጡ፤ ዳኛው ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ወድቆ ይሞታል፣ ሁለቱ አላዩትም! በመቀጠልም አንድኛው ይከተላል፣ ሌላኛውም ይቀጥላል።

በመጨረሻም ሶስቱም አግቢኝ ባዮች ቆንጆይቱን ሳይደርሱባት ሞቱ።

ይህቺ ናት ዱኒያ እኛ ዛሬ አንዱን ወንድማችንን ወደ አኼራ ሽኝተን በዱኒያ ቁንጅና ተማርከን መሮጣችንን ቀጥለናል፤ ከጎናችን ዱኒያን ትተዋት የሄዱትን አንመለከትም ነገ ከነገ ወዲያ እኔ፣ አንተ፣ አንቺም ተረኞች ነን።
*
በመጨረሻም ሽይኹ ይህንን ጨመሩ «ዱኒያ ማለት አደባባይ ላይ የቆመች የአሮጊት ቆንጆም ናት» አሉ። አባባሉን ሲያብራሩም እንዲህ ይላሉ:-
ዱኒያ አደባባይ ላይ የቆመች ናት ሲባል:- ዱኒያን ሁሉም ያያታል፣ ለመያዝም ይፈልጋታል፣
የአሮጊት ቆንጆ ነች ሲባል ደግሞ:- ዱኒያ ያኔ የእኛን ቅድመ አያቶች፣ አባቶች አድክማ ሳይዟት ትተዎት የሄዱ፣ እንዲሁም እኛም የምንይዛት እየመሰለንና ሁሌም ቆንጆና፣ አዲስ መስላ እየታየችን እርሷን ለመያዝ እንደክማለን ለዚያም ነው ዱኒያ የአሮጊት ቆንጆ ናት ያልኳችሁ» ብለው ዱኒያን ገለፁ።

ዱኒያ ላይ ዛሬ ተደስተህ፣ ነገ ታለቅሳለህ ዛሬ አግኝተህ፣ ነገ ታጣለህ ፈተናውን ሁሉ አልፌ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብለህ ኡፎይ ስትልና የእረፍት ኑሮ መኖር ስትጀምር፤ ድንገት ሳታስበው የሰበሰብከው ሁሉ ይበተናል።
ለእኛ ለሙስሊሞች ዱኒያ እዚህ ምድር ምንም አይደለች፣ እንደውም እስር ቤት ናት።

የአላህ መልዕክተኛ (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
«ዱኒያ ለሙዕሚኖች እስር ቤት ናት ለካፊሮች ደግሞ ጀነት ነች»።
ﻗﺎﻝ ﺭﺳﻮﻝ ﺍﻟﻠﻪ - ﺻﻠﻰ ﺍﻟﻠﻪ ﻋﻠﻴﻪ ﻭﺳﻠﻢ:
«ﺍﻟﺪﻧﻴﺎ ﺳﺠﻦ ﺍﻟﻤﺆﻣﻦ ﻭﺟﻨﺔ ﺍﻟﻜﺎﻓﺮ.»
ﺭﻭﺍﻩ ﻣﺴﻠﻢ
አምላካችን አላህም እወቁ ዱንያ የመታለያ ጥቅም እንጅ ሌላ አይደለችም ይለናል:-
اعْلَمُوا أَنَّمَا الْحَيَاةُ الدُّنْيَا لَعِبٌ وَلَهْوٌ وَزِينَةٌ وَتَفَاخُرٌ بَيْنَكُمْ وَتَكَاثُرٌ فِي الْأَمْوَالِ وَالْأَوْلَادِ ۖ كَمَثَلِ غَيْثٍ أَعْجَبَ الْكُفَّارَ نَبَاتُهُ ثُمَّ يَهِيجُ فَتَرَاهُ مُصْفَرًّا ثُمَّ يَكُونُ حُطَامًا ۖ وَفِي الْآخِرَةِ عَذَابٌ شَدِيدٌ وَمَغْفِرَةٌ مِّنَ اللَّهِ وَرِضْوَانٌ ۚ وَمَا الْحَيَاةُ الدُّنْيَا إِلَّا مَتَاعُ الْغُرُورِ۞
ቅርቢቱ ሕይወት ጨዋታና ዛዛታ፣ ማጌጫም፣ በመካከላችሁም መፎካከሪያ፣ በገንዘቦችና በልጆችም ብዛት መበላለጫ ብቻ መኾንዋን ዕወቁ፡፡ (እርሷ) በቃዩ ገበሬዎችን እንደሚያስደስት ዝናም፣ ከዚያም በቃዩ እንደሚደርቅና ገርጥቶ እንደምታየው፣ ከዚያም የተሰባበረ እንደሚኾን ብጤ ናት፣ በመጨረሻይቱም ዓለም ብርቱ ቅጣት ከአላህም ምሕረትና ውዴታ አልለ፡፡ የቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ ጥቅም እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡
ሱረቱል-ሐዲድ (20)

ጭንቀትህ ለዱኒያ ሳይሆን ለአኼራ መሆን ሲጀምር የውስጥ ሠላምና መረጋጋት ታገኛለህ።
*
ጀሊሉ እንኳን ርካሿን ዱኒያን ውድና ውብ የሆነቺዋን ፊርደውሰል አዕላን ይሰጣል!
ብዙ አትጨነቁ ዱኒያ ለተጨነቀላትና ለጓጓላት አትሆንም።
ረሱላችን (ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም) በሀዲሳቸው «ጭንቀቱ ዱኒያ የሆነች፣ አላህ (ሱብሃንሁ ወተዓላ) ድህነትን በዓይኖቹ መሀከል ያደርግበታል፣ ነገሩን ሁሉ ይበትንበታል፣ ከዱኒያም የተወሰነለት እንጂ ወደሱ አይመጣም» ብለዋልና!

ራስን ሳያስጨንቁና ድንበር ያለፈ ጉጉት ሳይኖር የተከተበልንን በሀላሉ መፈለግ ነው።
እና ለዱኒያ ብዙ መጨነቅ አያስፈልግም
ለዱኒያ ኑሮ፣ ጣጣ፣ የምንጨነቅ ሳይሆን ለአኬራችን የምንጨነቅ አላህ ያድርገን።

ለዛሬ ይህችን ካልኩ ይበቃኛል በሉ ይመቻችሁ!
ወሰላሙዓለይኩም!

መልክቱን ለሌሎችም እንዲደርስ ሁላችሁም ሼር አድርጉት
--------------------
ነሀሴ 18, 2014 E.C
ሙሐረም 26,1443 H.C
August 24, 2022 G.C
||
t.me/YasinMuhammed1