Get Mystery Box with random crypto!

ያለፈው የዐማራ ትውልድ የፈጸመው ስሕተትና የተጠለፈበት ሴራ ባግባቡ ተመርምሮ ለአሁኑ ትውልድ ባለ | Yalelet Wondye

ያለፈው የዐማራ ትውልድ የፈጸመው ስሕተትና የተጠለፈበት ሴራ ባግባቡ ተመርምሮ ለአሁኑ ትውልድ ባለመተላለፉ ይኸም ትውልድ እንዳለፈው ትውልድ ሁሉ በተመሳሳይ ሤራ እየተጠለፈ ካሰበበት እንዳይደርስ ሆኗል። ያለፈው ትውልድ ከሰራቸው ስህተት መካከል ማርክሲዝም ሌኒኒዝም አምጦ የወለዳቸው ተማሪዎች ተፈረካክሰው ከተበታተኑ በኋላ በየፊናቸው የራሳቸውን ነገድና ጎሣ ነጻ ለማውጣት የነጻነት ግምባር ንቅናቄዎችን ሲያቋቁሙ የዐማራ ተማሪዎች በዐማራነት መሰባሰብ አልቻሉም ነበር። የትግሬው ወያኔ፣ የኤርትራው ሻዕቢያ፣ የምዕራብ ሱማሌ ነፃነት ግምባር፣ የሲዳማ ነፃነት ግምባር፣ በኦሮሞ ስም የተቧደኑት ኦነግ፣ ኦብነግ፣ የኦሮሚያ እስላማዊ ነፃነት ግምባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አድነት ድርጅት (ቶኪቹማ)፣ የኦሮሞ አቦ ድርጅት፣ እና ሌሎችም በነጻ አውጭነት ሲቧደኑ በዐማራ ስም የተደራጀ አልነበረም።

ዐማራው በ1966 ዓ.ም. እንደ ሕወሓት፣ ኦብነግ፣ ኦነግ፣...ነጻ አውጭ ግንባር ቢኖረው ኖሮ ዐማራው በጨቋኝነት አይከሰስም ነበር። ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ኢትዮጵያ ዐማራው በአምሳሉ የፈጠራትና ብሔሮችን የጨቆነባት ሀገር ናት የሚለውን አፍራሽ ታሪክ እንዲጸና አድርጓል። በወቅቱ ኢትዮጵያ በኮሚኒዝም ርእዮተ ዓለም ስትናጥ፣ የዚህ አዲስ ርዕዮት ተቀጥላ የሆኑ ዐማራን ኢላማ ያደረጉ የብሄር አስተሳሰቦች በኢትዮጵያ አየር እንደ ጆፌ አሞራ ሲያንዣብቡ፣ ዐማራው መኢሶን፣ ኢሕአፓ፣ ኢዲዩ፣ ወዝ ሊግ፣ ማሌሪድ፣ ሰደድ (ኢሠፓአኮ እና ኢሠፓ) ወዘተ በሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተከፋፍሎ፣ ልክ እንደ እንደ ዘመነ መሣፍንቱ፣ እንደ ዳግማዊ ቴዎድሮስና ተክለጊዮርጊስ ዘመን ርስበራሱ ይባላ ነበር።

ሁለተኛው ችግር ዐማራ ለውጥን መምራት እንጂ ለለውጥ ትግል የማድረግ ችግር የለበትም። ዐማራ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እስከ ኢሕአዴግ ትግል በመጀመር ቀዳሚ ነው። ነገርግን የታገለለት ዓላማ በአንድም በሌላም መንገድ እየተጨናገፈ ግቡን ሳይመታ ቀርቷል። የ1953ቱ የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራ ያደረጉት መንግሥቱ ነዋይ፣ ገርማሜ ነዋይና ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ዐማሮች ናቸው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዘውድ ያነቃነቀው የጎጃም ገበሬዎች አመፅ ነው። በተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ዐማሮች ነበሩ ነገርግን ዘውዱን ታግሎ ደርግን ወለደ፣ ደርግን አሸንፎ መንበረ ሥልጣኑን ለሕወሓት አስረከበ፣ ወያኔን ታግሎ ብልፅግናን አነገሠ። እነዚህን ሁለት ተከታታይ ሥርዓቶች ደርግና ወያኔን በዐማራ ውድ ልጆች ከፍተኛ መስዋዕትነትና በሌሎችም ሕዝቦች ተጋድሎ ቢገረሰሱም ቀጥሎ በመጣው የብልጽግና ሥርዓት ዐማራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተሳዳጅና የትም የሚገደል ሆነ።

አሁን ደግሞ ሌላ ምናልባትም እረጅም ዓመት የሚወስድ ትግል ይደረጋል፣ አሁንም ለውጥ አምጥቶ ይቀማል።ስለዚህ ዐማራው የመታገል ሳይሆን ታግሎ ያመጣውን ለውጥ የማስቀጠል ችግር ነው ያለበት።

ሦስተኛው ችግር ለውጡን አምጥቶ፣ ለለውጡ አስፈላጊ ለሆኑ ሰዎች ግዜ ሰጥቶ አብሮ ከመሥራት ይልቅ መቃወምና ማደናቀፍ ሌላኛው ችግር ነው። ለምሳሌ፣ ዐማሮች የቴዎድሮስን መምጣት ይናፍቁ ነበር። በዘመነ-መሳፍንት እንደ ክረምት ዝናብ በማያባራ የእርስበርስ ጦርነት የተማረረው ዐማራ በፍካሬ ኢየሱስ ውስጥ፣ "ኢትዮጵያን ከወደቀችበት የሚያነሳ፣ ጠላቶቿን ከምድረ-ገጽ የሚያጠፋ ንጉሥ ይነግሣል። በዚህ ንጉሥ የስልጣን ዘመን በመላው ሀገሪቱ ሰላም ይሰፍናል። ይህም ንጉሥ ስሙ ቴዎድሮስ ይባላል።" የሚለውን ቃል እያሰበ፣ ያንን ዘመን እየናፈቀ የመከራውን ዘመን ሲገፋ ኑሯል።

ተናፊቂው ቴዎድሮስ መጣ፣ አዳዲስ እርምጃዎች መውሰድ ጀመረ። ቴዎድሮስ አገሪቱ በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር እቅድ ነበረው። በእቅዱ መሠረት ደብረታቦር፣ ጎንደር፣ መቅደላ፣ ደቡብ ጎጃም በመንገድ ተሳስረው ለጉዞ ምቹ እንዲሆኑ ይፈልጉ ስለነበር በጀርመናውያን ሚሲዮናውያን አማካኝነት የመንገድ ሥራ ንድፍ ወጥቶ አሰቸጋሪ ቋጥኞችን በድማሚት የመናድ ሥራ ተጀምሮ ነበር። ራሱ ቴዎድሮስ ቋጥኝ እየናደና አለት እየፈነቀለ መንገድ ለመሥራት ሞክሯል። ለዚህም ከጋፋት እስከ መቅደላ ድረስ ለሴባስቶፖል መድፍ መጓጓዣ እንዲውል ማድረጋቸው ይታወቃል። (ፊሊፕ ማርስዲን፣ 61)

ቴዎድሮስ በእርስ በርስ ሽኩቻና ጦርነት የወደመ ኋላቀር ሀገርን እቀይራለሁ ብሎ ሲነሳ ባለመታደል ይሁን፣ ወይም በእርግማን ወይም በሌሎች በማናውቃቸው ምክንያቶች ከዘመነ መሳፍንት ግፍና ፍዳ ነፃ ካወጡት ህዝብ የገጠማቸው ተቃውሞ ነበር። በዘመነ መሳፍንት ፍዳ የቴዎድሮስን መምጣት ይናፍቅ የነበረ ሕዝብ ቴዎድሮስ ሲመጣ መልሶ ቴዎድሮስን እየረገመ ሌላ ንጉሥ የሚናፍቅ ሆነ።

ቴዎድሮስ በአካባቢ ባለቤቶች ተከፋፍሎ ሕዝቡ የመከራ ሕይዎት የሚገፋባትን አገር፣ ወደ ጥንቱ አንደነቱ መልሶ የበለፀገ፣ የታፈረና የተከበረ አንድ ዐማራንና አንዲት ኢትዮጵያን የማየት ራዕይ ሰንቆ ነበር የተነሳው። የዐማራን አንድነት ትንሣኤ ለማብሰር ከ38 ጊዜ በላይ ጦርነት አካሂደዋል። ጦርነቱ የቴዎድሮስን አመራር አምኖ በተከተለ ዐማራ እና በሌላ በኩል ከእርሳቸው ዓላማ ተፃራሪ ሆነው በቆሙ ዐማሮች መካከል የተካሄደ ትግልና መስዋዕትነት ነው።

ነገርግን ለግል ጥቅሙ እንጂ ለሀገሩ እድገት፣ ለሀገሩ አንድነትና ልማት ለመሥራት የቆረጠ የዐማራ መሳፍንት አልነበረም። ተባባሪ ህዝብ አልነበረም፣ ህዝቡ መሻሻልና መለወጥን ሳይሆን የፈለገው በነበረው የዘልማድ ህይወት መቀጠሉን ነው የመረጠው። ህዝቡ ከቴዎድሮስ ምኞትና አሠራር ጋር የሚጣጣም አልነበረም፡፡ ይህንንም ቴዎድሮስ ለራሳም እንዲህ ነበር ያሉት፣

"በሰላም እንዲኖሩ ሞከርኩ፤ እንደሠለጠነው አለም ወደሥልጣኔ እንዲሄዱ ታገልኩ፤ በሥርአት እንዲኖሩ፣ ልጆቻቸው ተስፋ እንዲኖራቸው ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን ክፉ ናቸው" (መቅደላ የቴዎድሮስ ዕጣ፣ 45)

ቴዎድሮስ ህዝብ ሥርዓት እንዲገባ ወታደር በዲሲፕሊን የታነፀ እንዲሆን ሲመኙት የኖሩት ግን አልሳካ ያላቸውን ጉዳይ ነበር። ለናፒየር የጻፉትን ደብዳቤም እንዲህ የሚል ይገኝበታል፣

"...ያገሬን ሰው ግብር ስራት ግባ ብዬ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ። እናንተ ግን በስራት በተገዛ ሰው አቸነፋችሁኝ።...
የአገሬ ሰው የፈረንጅ ኃይማኖት ይዟል፣ አሰልሟል እያለ አስሩን ምክንያት ይሰጠኝ ነበር። እኔ ከከፋሁበት እግዚአብሔር መልካም ይስጠው። እንደወደደው ይሁን።"
(ፈሊፕ ማርስዲን፣ 484)

በመጨረሻም ጀግናው ተዋጊና የጦር አዛዥ፣ ሀገራቸው ከዘመነ-መሳፍንት መዳፍ ፈልቅቀው ለማትረፍ የተዋጉት፣ የራሳቸው የዐማራ ሕዝብ እንኳን ዓላማቸውና ራዕያቸውን ያልተረዳላቸው ቴዎድሮስ መቅደላ በእንግሊዞች እጅ መውደቁን ሲያዩ ሽጉጣቸውን ከወገባቸው ቀበቶ ላይ ላጥ አድርገው አፈሙዙን አፋቸው ውስጥ አስገብተው ምላጩን ሳቡት። ከምንም በላይ የሕይዎት፣ የአጥንት፣ የደም፣ የገንዘብ፣ የንብረት፣ የጊዜና ጉልበት ዋጋ የተከፈለበት የዐማራ አንድነት ከመቅደላ መውደቅ ጋር ተቀበረ።

ቴዎድሮስ እንደ ሩሲያዊው ንጉሥ ኒኮሊያ፣ እንደ ፈረንሳዩ ንጉሥ ናፖሊዮን ቦኖፓርቲ በልቡ ያሰበውን ዕቅድ ሳያሳካ የሞተው ጠመጃና መድፍ ስላልነበረው፣ ሥልጣኔን እንደኃጢያት በሚቆጥር ሕዝብ መካከል በመገኘቱ ጋፋት ላይ የተሰራው 16,000 ፓውንድ የሚክደው ሴባስቶፓል መድፍ የተዘጋጀለት ኢላማ ሳይመታ መንገድ ላይ እንደቀረው ሁሉ ህልማቸውም ከሸፎ ቀረ። የመሣሪያ ፋብሪካ እና መማሪያ ትምህርት ቤት የተከፈተባት ጋፋት ወድማ ወደጥንቱ ድንጋያማነት ተመለሰች። በጋፋት የተሰሩ ቤቶቹ ፈረሱ፣ የብረት