2022-05-09 23:36:50
ሜርሲ
እራሴን እረሳለሁ... እራስን መርሳት የመሰለ ነገር የለም... ለዛ በሱስ ውስጥ እደበቃለሁ.. "
"እስከመች?" ስትሰማው ቆይታ ጠየቀችው
"እስከመች ነዉ የምታኖረው ብለሽ ጠይቂው... የመጨረሻውን ቀን ይነግርሽ እንደሆነ... እና እስከእስትንፋሴ ህቅታ ከሱሴ ጋር ነኝ" በንቀት መለሰላት
"ከጌታ ቤት ከራቅክ ስንት ጊዜ ሆነህ? "
ፊቱን ቅጭም አደረጋባት.. "የፈረደበትን ያንን ተረታችሁን ይዘሽ ነዉ አአ የመጣሽው... ድሮም ቀልቤ አልወደደሽም ነበር "
"የጠየቅኩህን መልስልኝ" ረጋ ብላ ነበር
"ስድስት ዓመት.... ለምን ጠየቅሽኝ?"
"ዛሬም ከልብህ እንዳልጠፋ ለማወቅ"
"አልገባኝም"
"ከሶስት ቀን በፊት የበላሀውን ቁርስ ታስታውሰዋለው? "
"እንደውም... ምን ስትይው ጠየቅሽኝ "
"አታስታውሰውም... ምግብ ለቀን ስለሆነ አታስታውሰውም.. ፍርፍር ይሁን እንቁላል ለአንተ በጊዜው ካልሆነ ቦታ የላቸውም... ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ከጌታ ቤት የወጣህበትን.. ወደ ሱስ የገባህበትን ምክንያት ጊዜ እና ቦታ ታስታውሳለህ.. ሁሉንም ዛሬ እንደተፈጠረ አይነት አድርገህ.. ተሳሳትኩ? "
"አይ... " ቀጣዩን እስክታወራ ልቡ እየጓጓ
"ፊትህን በመስታወት ማየት ትፈራለህ... መስታወት ፊት ስትቆም ከስድስት ዓመት በፊት የነበረው የልጅነት መልክህ ድቅን ይልብሃል... ተሳሳትኩ? "
እንዳልተሳሳተች አንገቱን በመነቅነቅ አረጋገጠላት
"የአንተ እኩዮች ሥራ ይዘው ቤት መስርተው ሲኖሩ ስታይ... ከስድስት ዓመት በፊት የነበረው ሕይወትህ ትዝ ይልህና ለዛ ፈተና እጄን ባልሰጥ እኔም እኮ ትላለህ "
"ከእኔ ጋር አብረሽ ነበርሽ? " በመደነቅ ጠየቃት
"አስጨርሰኝ... ብዙ ልልህ እችላለሁ.. ግና አንድ ነገር ብቻ ላክልልህ.. የትላንት ቤትህን አትረሳውም::የሞቀውን ቤት አትረሳውም:: ከስድስት ዓመት በፊት እዚሁ ስፍራ ላይ እኔ በአንተ ቦታ ላይ ነበርኩ ተመሳሳይ ጥያቄ ጠየቅከኝ.. ከዛ በመጨረሻም የወጣሁበትን ቤት ያልረሳሁት ቤቴ ስለሆነ እንደቤቴ የሚሆን ቦታ ስለሌለ እንደሆነ የጠፋውን ልጅ ታሪክ አንስተህ አጫወትከኝ... ቤቴ ስለሆነ እኔን አባቴ ለመቀበል በሩ ክፍት አድርጎ በደጁ ሆኖ በናፍቆት እየጠበቀኝ እንደሆነ አከልክበት... እኔ ወደ ቤቴ ተመለስኩ አንተ ግን እኔን ወደ ቤቴ አድርሰህ ኮበለልክ.. አሁን ፊቴን በመስታወት ሳይ በውበቴ እየተደነቅኩ የፈጠሩኝ እጆቹን እባርካለሁ... የከበረውን እለብሳለሁ.. ስለ እራሴ ሳስብ ውስጤ በሃሴት ይሞላል... ልበላ ከእርያዎች ጋር አልጋፋም.. ያለሁት በአባቴ ቤት ስለሆነ.. እና ዛሬ ወደ ሞቀው ቤትህ ልመልስህ መጣሁ ያለአንተ ቤቱ አልሞቀም መሰለኝ አባትህ እደጅ ሆኖ ሁሌ ይጠብቅሃለህ ዘጠና ዘጠኞቹ እያለን አንዱ አንተ ጠፍተህበት ሊፈልግህ መጥቷል... አብረን እንድንሄድ መጣሁ "
እንባ ፊቶቹን እያራሰው ቀና ብሎ አያት እግሩን ካጣጠፈበት ዘርግቶ ብድግ አለ አፉ ላይ የለጎመው ጫት እሬት እሬት አለው እያንገሸገሸው ተፋው እና አብሯት ወጣ እየጠበቀው ወዳለው አባቱና ቤቱ ናፍቆታልና ተቻኮለ...
#ዛሬም በሩ ክፍት ነዉ!
ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ወንጌላውያን ተማሪዎች ህብረት
እርስዎ አስተያየት አሎት?
ካልዎት እባክዎ ከታች በሚገኘው ሊንክ ይላኩልን ይደርሰናል!
@Wcu_EvaSUE
ከላይ በሚገኙት ሊንክ ይላኩልን! ተባረኩ!
@WcuEva
179 views20:36