Get Mystery Box with random crypto!

በረደኝ ይደክማል ጎዳናው የሰው ዋጋ መርሳት ከእንቅልፍ ሲነቁ ያ'ዘን መርዶ መስማት ይደክማል ጎ | ፍቅርና ተስፋ

በረደኝ


ይደክማል ጎዳናው የሰው ዋጋ መርሳት
ከእንቅልፍ ሲነቁ ያ'ዘን መርዶ መስማት
ይደክማል ጎዳናው የሰው እንባ ሲቀል
የሰው ልጅ ህይወቱ መንገዱ ሲነቀል
ይደክማል ጎዳናው ያለቦታው ማውራት
ሰው ሞቷል እያሉ ሁሌ ሻማ ማብራት
ይደክማል ጎዳናው ማንኳኳት የሰው በር
መኖር ያልጀመሩ ህፃናትን መቅበር
ይደክማል ጎዳናው እናት ስታለቅስ
ቤተክርስቲያን አዝና :ከፍቷት ስታስቀድስ
ይደክማል!
ይደክማል ጎዳናው በሰው መደራደር
ነገ ምን ይሆን ብለው? እየሰጉ ማደር


ምንድነው ባንዲራ?
ዝቅ ብሎ ይሰቀል ብሎ የሚነገር
የሞተውን ደሃ
ወደ ቤተሰቡ ላይመልሰው ነገር


በናት ቀሚስ ለቅሶ
ያለምንም ስስት ስልጣን እየገዙ
ነጋችን ወዴት ነው?
ዝቅዝቅ ነጠላዎች እንደዚ ከበዙ

እንደ ነኸምያ ቅጥር
እንባን ማበስ ማከም እጅህ ካልወደደች
አትኖርም ኢትዮጵያ
ቀስበቀስ እንዳምና በቀልድ ትሄዳለች


እግዚኦ ለትውልዱ እግዚኦ መአረነ
ህዝብህና ህዝብህ፡ ሄደ እየቀለለ(እየመነነ
እግዚኦ ለኢትዮጵያ እግዚኦ ለአገሬ
እንባዋ ይታበስ መዳን ይሁን ዛሬ
እግዚኦ ለትውልድህ እግዚኦ ላልቃሾች
ህመም ለለበሱ ለወደቁ ህዝቦች


ጌታ ሆይ

ሲነጋና ሲመሽ
እንደተራ ነገር ሰው መቅበር አመመኝ
እባክህ እንደ'ስራኤል
በ ክብርህ መተህ መባረክን ባርከኝ
ህዝቤን አስብልኝ!


ምንጮህበት አካል
እርዳኝ ምለው አባሽ ፡ወገን ስለሌለኝ
አቤቱ ጌታዬ
አሞኛል በሃይል ፈጥነህ መተህ እርዳኝ


የምስኪናን እንባ
እንደዘፈን አርገው በሚያደምጡት ጊዜ
አንተ ፊት ልደፋ
ማታ ልጩህ ፊትህ እግርህ ስር ወድቄ


ደከመኝ አመመኝ
ዛሬ አንድ ሰው ሄደ ትላንት ሁለት መቶ
ማነው የሚያወጣን
ከጭንቅ ጊዛያችን በታምራት መጥቶ????
በአራቱም አቅጣጫ
ብንሄድ ወገን ጋር መንገዱ ደም ብቻ

እኔ ልጠይቅህ

በደምህ የገዛኸው
ዋጋው ምን ያህል ነው የፍጥረትህ ዋጋ??



@tloveandhope