Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅር ከሁሉ ይበልጣል! ፍቅር የሚታየውና የሚለካው በግጭት ውስጥ ነው።ግጭት በሌለበት ፍቅር አ | ሰው መሆን...

ፍቅር ከሁሉ ይበልጣል!

ፍቅር የሚታየውና የሚለካው በግጭት ውስጥ ነው።ግጭት በሌለበት ፍቅር አይታይም። የፍቅር ከፍታና ልክ ማሳያው ግጭት ነው። የሚፋቀር ሰው ግጭትን ይታገሳል፣ ታግሶም ያልፋል። ፍቅር ላይ ታች እንደሚል የሚዛን ጨዋታ ነው።

በሚዛን ጨዋታ ከታች ወደላይ፣ ከላይ ወደታች፣ እንደገናም ከታች ወደላይ እያለ ጨዋታው ይቀጥላል። በሚዛን ጨዋታ ሚዛኑ አይሰበርም።ትዳርም እንደማይሰበር የሚዛን ጨዋታ ነው።ትዳር ከፍና ዝቅ አለው።

በሚዛን ጨዋታ የተቀመጡት ሰዎች አይወድቁም። የተቀመጡት ልጆች ፈሪዎች ከሆኑ ግን ፈርተው ወይም ተገን ፍለጋ ወደ አንድ ጎን አጋድለው ይወድቃሉ።

በትዳር ውስጥ ሆናችሁ አትፍሩ! ሁሌም ጥሩ ሁኑ! ሌላው ወገን ጥሩ ባይሆን እንኳ እናንተ ጥሩ ሁኑ። ፍቅር ማለት ያ ነው፤ ሌላው ወገን ሲከፋባችሁ፣ ሳይመቻችሁ ሲቀር ታግሶ መቆየት ነው። ስንት ዓመት እንታገስ? አይዞኝ አንቸኩል! ውሎ አድሮ ምናልባትም ዓመታት ቆይቶ ነገሩ ይስተካከላል።

"ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ስራው" ይላል ታላቁ መጽሓፍ። ታገስ! አትቸኩል። ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ የሀይማኖት መሪ፣ አዋቂ፣ ... ብቻ ማንም ይሁን ማን የሚላችሁን ሰምታችሁ ትዳራችሁን አታፍርሱ፣ ቤተሰብ አትበትኑ። ጽናት እንጂ ፍቺ አያኮራም!ፍቅር ስምምነት አይደለም። ፍቅር አይቀናም፣ ፍቅር ይታገሳል፣ ፍቅር አይታበይም!

ፍቅር የሚገለጸው በግጭት ውስጥ ልዩነትን በመቻል ነው። በእያንዳንዱን ልዩነት በመበሳጨት፣ ልዩነቱን መሸሽ፣ በልዩነቱ ወደ ፍቺ መሮጥ የፍቅርን ፍሬ አያበላም።

የፍቅር ፍሬ ሰላም ነው፣ ደስታ ነው፣ ቤተሰብ ነው።ፍቅር በልዩነት ውስጥ፣ በግጭት ውስጥ፣ ነገሮችን ታግሶ በመቻል ውስጥ ያለ የሚከፈል ክፍያ ነው።ልዩነትን መታገስ አቅቶን ፍቅር የለም። በልዩነት ምክንያት እየተሰዳደብን ፍቅር የለም። በልዩነት ምክንያት ወደ ፍቺ እየሮጡ ፍቅር የለም።

በፍቅር ውስጥ ስስት አለ። በፍቅር ውስጥ የማጣት ፍርሃት አለ። በፍቅር ውስጥ ናፍቆት አለ። በፍቅር ውስጥ ጉጉት አለ። በፍቅር ውስጥ አድናቆት አለ። በፍቅር ውስጥ ትዕግስት አለ። በፍቅር ውስጥ ተስፋ አለ።በፍቅር ውስጥ ስድብ የለም። በፍቅር ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የለም። በፍቅር ውስጥ ሽሽት የለም።

ፍቅር ማለት ሁሌ ምቾት፣ ሁሌ ሽርሽር፣ ሁሌ ሳቅ፣ ሁሌ መዝናናት፣ ሁሌ ጥጋብ አይደለም።ፍቅር ትዕግስት፣ ናፍቆት፣ መውደድ፣ መቻል፣ ወድቆ መነሳት እና መስዋዕትነት ነው! ፍቅር እስከ መቃብርን አላነበባችሁም።የፍቅር ጠላት ጥርጣሬ፣ አለመከባበር፣ አለመታመንና አለመተሳሰብ ናቸው።
የፍቅር ዋና ጠላት ግን ይቅርታ ማለት አለመቻል ነው።የፍቅር ጠላት ራስ ወዳድነት ነው።

ፍቅር አንዳንዴ ስቃይ ያለው መውደድ ይሆናል። ቢሆንም ፍቅር ከነስቃዩም ያስደስታል፤ ተስፋም አለው። ፍቅር በምቾትም በስቃይም አብሮ መሆን ነው።

ፍቅር ትርፉ ብዙ ነው፤ ለፍቅር ስትሉ ታገሱ! ፍቅር አትራፊ ነው። ፍቅር የበረከት ምንጭ ነው።
Getu k. Toughe

የደስታ ማቀፊያው አጥር ፍቅር ነው!

ከፍቅርና በፍቅር ከመኖር ውጭ ሌላ እዳ አይኑርባችሁ፡፡

@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni