Get Mystery Box with random crypto!

#↑ከአፈር እስከ ጠፈር↓ ````` (ገጣሚ ብሩክ ቃልኪዳን) በቁንጅናሽ ትምክህት ከጨረቃ ጋራ ~ | ሰው መሆን...

#↑ከአፈር እስከ ጠፈር↓
`````
(ገጣሚ ብሩክ ቃልኪዳን)

በቁንጅናሽ ትምክህት
ከጨረቃ ጋራ ~ አትፎካከሪ፣
ከእቅፌ ላይ ወድቀሽ
ከኮከብ ንጉስ ጋ ~ በአሳብ አትዳሪ።

አንዳንዴ ብንጋጭ
እኔ ላንች ሰንኮፍ ~ አንች ለኔ ጌጤ፣
ወደ አጽናፍ አታንጋጭ
ሰው ነው ያንች እኩያ ~ ሰው ነው ያንች ቢጤ።

እርግጥ እውነት አለሽ
አንድ አይነት ነው ግብርሽ ~ ከጨረቃ መሳ፣
ለአንች መዋቢያሽን
ደሞ ለጨረቃ ~ ፀሐይን ቢነሳ፤
በደምግባታችሁ ~ መች ትመጻደቁ፣
በውሰት የወዛ
ፍግ ነው ተፈጥሯችሁ ~ ቢሸፈንም በእንቁ።

ውበት የአፈር ዑደት
በስንዝር የዕድሜ አንጓ ~ የሚከሰት ማማር፣
ቁንጅናን ለመግለጽ
ውብ ቃላት የሚያምጥ ~ እርባን ቢስ ነው ጦማር።

የልህቀቱ ተመን
አሀድ ቢገኝለት ~ ሚዛን ላይ ቢሰፈር፣
ቢከብደን ለማመን
ይሄ ነው የ ሰው ልኬት ~ ከአፈር እስከ ጠፈር "።

ቢያንስ አፈር ነው ልኩ ~
መሬት ላይ የረጋ ~ እንደ አቧራ ብናኝ ፣
ቢገዝፍ ጠፈር አያልፍ ~
ግዛቱን ቢያሰፋ ~ እንደ ህዋ መናኝ።

አፈር ትቢያ ጉድፍ ፣
አፈር የገላ እድፍ፣
ሰው የመሆን ግብዓት ~ መዋቅር ነው "አተም"፣
ኑረቱን የሚያውጅ
በፈጣሪ ፍቃድ ~ "በትንፋሽ" ማኅተም።

ያንችም የኔም ገላ
ለትቢያ የታጨ ~ ትቢያ ነው መነሻው፣
የሥጋ ጥርቅም
የህላዌ አቅም
ከኑረቱ ማግስት ~ መበሰበስ ነው ድርሻው።

ነገ በእርጅና ውርጭ ለሚቆረፍደው ~ አታድሊ ለሥጋ፣
የተፈጥሮን ቅኝት
ከነፍስ ቁርኝት
በአቻነት ሚዛን ላይ ~ ለማስሄድ ካልተጋ፤
ሰብ ሟች ነው ~ ሰብ ጠፊ፣
ግብዝ ግብር ጋልቦሽ
ወዙን ያጣ አፍቃሪ ~ ሲቀርብሽ አትግፊ።

ሰብ የሸክላ ውጤት
በአምሳሉ ለንቁጦ ~ ያበጀው ኤልሻዳይ፣
አፈር የሰው ቁራሽ ~ ለሰው "ትንፋሽ" ጉዳይ።
የሚል ነው ስብከቴ፣
አፈር ሁነሽ ሳለ
አፈር ስትገፊ ~ ገርሞኝ መመልከቴ።


ሌሎች እንዲያውቁ እናካፍል፡
መልካም እንሁን በፍቅር እንኑር።



@TIBEBnegni
@TIBEBnegni
@TIBEBnegni