Get Mystery Box with random crypto!

እውን ዑመር ብኑል ኸጣብ ሴት ልጃቸውን ከነ ህይወቷ ቀብረዋልን? ~ ብዙዎቻችን በተለያየ አጋጣሚ ታ | አስ–ሱናህ

እውን ዑመር ብኑል ኸጣብ ሴት ልጃቸውን ከነ ህይወቷ ቀብረዋልን?
~
ብዙዎቻችን በተለያየ አጋጣሚ ታላቁ ሶሐባ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ በጃሂሊያ ሴት ልጃቸውን ቀብረው እንደነበር እንደሰማን ወይም እንዳወራን እገምታለሁ። የሚያስደነግጠው ግን ዑመርን ባልሰሩት ጥፋት ስማቸውን ስናነሳው መቆየታችን ነው። መቼስ በዲናችን እውነት ያልሆነን ወሬ ማራገብ ያለውን አደጋ አናጣውም። በተለይ ደግሞ በዲን ስም በአላህ ቤት በመስጂድ ውስጥ ጥፋቱ ሲሰራ አስቡት። እርግጥ ነው ዑመር ጥፋቱን ሰርተውት ቢሆን እንኳን በጃሂሊያ ዘመን በተሰራ ጥፋት በኢስላም ተጠያቂ አይሆኑም። ይህን ቅጥፈት የፈበረኩት ሺዓዎች ግን በቀጥታ ዑመርን ሲያወግዙ ከሱኒው ዓለም ሰሚ ስላጡ እንዲህ በጀርባ ያሰርጋሉ፣ በጀርባም ይወጋሉ። በሚገርም ሁኔታም ጥረታቸው ተሳክቶ መሰረታዊ ጉዳዮችን የማያውቀው ሁሉ ይህን ቂሷ ያስተጋባል። ምንም በጃሂሊያ ዘመን ቢሆንም ዑመርን ባልተጨበጠ ወሬ መወረፍ ጥራዝ ነጠቅነት ብቻ ሳይሆን ፍረደ ገምድልነትም ነው። እስኪ ማነው ይህን ለራሱ የሚወድ? ለማስታወስ ያህል የቂሷው ጭብጥ ይህን ይመስላል።
(ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ ከጓደኞቻቸው ጋር ተቀምጠው ሳለ ትንሽ ከሳቁ በኋላ አለቀሱ። ምክንያቱን ሲጠየቁ እንዲህ ሲሉ መለሱ፡- “በጃሂሊያ ጊዜ ከተምር እየጨበጥን ጣኦት እንሰራ ነበር። እናመልከውም ነበር። ከዚያ ግን እንበላው ነበር። ይህ ነው የሳቅኩበት ምክኒያት። ያስለቀሰኝ ደግሞ አንዲት ሴት ልጅ ነበረችኝ። ከነህይወቷ ልቀብራት ፈለግኩኝ። ይዣት ሄድኩና ጉድጓድ መቆፈር ያዝኩኝ። አፈሩ እየተረጨ ፂሜ ላይ ሲደርስ እሷ ከፂሜ ላይ ታራግፍልኝ ነበር። እንዲህ እየሆነች ከነህይወቷ ቀበርኳት።”)
ታሪኩ ይሄው ነው። ወደ ፍተሻ እንግባ። ኢስላምን ከሌሎች እምነቶች ብቻ ሳይሆን “ዘመናዊ” ከሚባለውም የታሪክ አዘጋገብ ልዩ የሚያደርገው ድንቅ የታሪክ መመርመሪያ መኖሩ ነው። ለመመርመር ደግሞ ናሙና ያስፈልገዋል። ናሙናው ሽንት ወይም ደም ወይም አክታ አይደለም። ናሙናው “ሰነድ” ይባላል። ጉዳዩን ሲቀባበሉ የነበሩት ሰዎች ሰንሰለት። ሰንሰለቱም፣ በሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ሰዎች ታማኝነትና ብቃትም በጥብቅ ይፈተሻል፣ ይመረመራል። ሰነድ የዲናችን ክፍል ነው። ዲናችን ከሰርጎ ገቦች የሚጠበቅበት ልዩ ማበጠሪያ ወንፊት ነውና። ለዚያም ነው ኢብኑ ሙባረክ “ሰነድ ከዲን ነው። ሰነድ ባይኖር ኖሮ ማንም ተነስቶ የፈለገውን ያወራ ነበር” ማለታቸው። ታዲያ የላይኛው ታሪክ ወደ ምርመራ ክፍል ሲገባ ከናካቴው ናሙና ማግኘት አልተቻለም። ሰነድ የለውምና። ለአቅመ ምርመራ አልደረሰም ማለት ነው። ታሪኩ በሚገርም ሁኔታ ከየትኛው የቀደምት የሱናና የሐዲስ እንዲሁም የታሪክ ድርሳናት ውስጥ አይገኝም። እናስ ከየት መጣ? ዑመርን በክፉ ከሚወነጅሉት ሺዓዎች ዘንድ። ዘጋቢውም ኒዕመቱላህ አልጀዛኢሪ የተባለ የለየለት ዋሾ ራፊ - ዷ ነው፣ ሺዐ።
የታሪኩን ቅጥፈት ከሚያጋልጡ ነጥቦች ውስጥ:–
1. ታሪኩ በተጨባጭ ቅጥፈት እንደሆነ ከሚያጋልጡ ቀዳሚ ነገሮች ውስጥ አንዱ በቀደምት የሱኒዎች የሱናም ሆነ የታሪክ ድርሳናት ውስጥ ጭራሽ አለመገኘቱ ነው።
2. ዑመር ከመጀመሪያ ሚስታቸው ከዘይነብ ቢንቲ መዝዑን የወለዷቸው ልጆች እነኚህ ናቸው:– ሐፍሷ፣ ዐብዱላህ እና ዐብዱረሕማን አልክበር። (አልቢዳያ ወኒሃያን ይመልከቱ።) ከነዚህ ውስጥ ታላቋ ሐፍሷ ነች። ታዲያ ታላቋን ሐፍሷን ሳይቀብሩ እንዴት ነው ትንሿን የሚቀብሩት?
3. ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ በጃሂሊያም በኢስላምም ያገቧቸውም ሴቶች የወለዷቸውም ልጆች ስም ዝርዝር ሲተላለፍ ስለቀበሯት ህፃን ግን እንዴት አንድ እንኳን ከቤተሰባቸው ሳያወራ ይቀራል? ይህን ወሬ እውነት ቢሆን ኖሮ ከዑመር ቤተሰብም #ከቀደምት ታላላቅ የኢስላም ሊቃውንትም ሳንሰማው እንዴት ብሎ ከስንት መቶ አመት በኋላ ከመጣው ከዚህ የዑመር ጠላት ሺዐ እንሰማዋለን?
4. ሴት ልጅ ከነህይወት መቅበር በዐረቦች ዘንድ የነበረ አስከፊ ባህል ቢሆንም የሁሉም ዐረቦች ባህል ግን አልነበረም። ይሄ ባህል የዑመር ጎሳ በሆኑት በኑ ዐዲይ ውስጥም የተለመደ አልነበረም። ታዲያ በየት ብሎ ነው እንዲህ ዓይነቱን ታሪክ ያለ #ጠንካራ ማስረጃ ወደ ዑመር የምናስጠጋው? እዚህ ላይ የዑመር እህት ፋጢማ የአጎቷን ልጅ ሰዒድ ብኑ ዘይድን ማግባቷን እናስታውስ። ሳትቀበር በህይወት መቆየቷ ምን ያመላክተናል?
5. ሌላ የታሪኩን ቅጥፈት ከሚጠቁሙ ነገሮች ውስጥ ዑመር ረዲየላሁ ዐንሁ {ከነ ህይወቷ የተቀበረችውም ሴት ልጅ በተጠየቀች ጊዜ} (ተክዊር፡ 8) ስለሚለው የቁርአን አንቀፅ መልእክት በተጠየቁ ጊዜ እንዲህ ማለታቸው ነው፡- “ቀይስ ብኑ ዓሲም ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ዘንድ መጣና ‘እኔ በጃሂሊያ ስምንት ሴት ልጆቼን ከነ ህይወታቸው ቀብሬያለሁ’ አላቸው። እሳቸውም ‘ለእያንዳንዷ አንዳንድ ባሪያ ነፃ አውጣ’ አሉት። ‘እኔ ባለ ግመል ነኝ’ አለ። ‘እንግዲያውስ ከፈለግክ ከያንዳንዳቸው አንዳንድ ግመል መፅውት’” አሉት። (አሶሒሓህ፡ 3298 ይመልከቱ) እንግዲህ ተመልከቱ ይህን ታሪክ ያስተላፉትው ዑመር ብኑል ኸጣብ ናቸው። እሳቸው የጥፋቱ ተጋሪ ቢሆኑ ኖሮ ሊያወሩ የሚችሉበት ወሳኝና ተያያዥ ቦታ ነበር። ግን የቀይስን ሲያወሩ ስለራሳቸው ምንም አላሉም። እሳቸው የራሳቸውን ደብቀው ይሄ የሳቸው ጠላት የሆነው ሺዐ ደረሰበት ማለት የሚመስል ወሬ አይደለም።
ይታወስ ሺዐዎች በውሸት የተካኑ ፍጡሮች ናቸው።
1. ኢማሙ ሻፊዒይ እንዲህ ብለዋል፡- “ከስሜት ተከታዮች ውስጥ እንደ ራፊ - ዷ በአላህ ላይ በቅጥፈት የሚመሰክር አላየሁም።” (ኡሱሉል ኢዕቲቃድ፡ 8/2811)
2. ኢብኑል ቀይም እንዲህ ብለዋል፡- “ራፊ - ዳዎች ከአላህ ፍጡሮች ሁሉ የመጨረሻ ውሸታሞቹ ናቸው፡፡” (አልመናሩል ሙኒፍ፡ 52)
3. ኢብኑ ተይሚያ እንዲህ ብለዋል፡- “የእውቀት፣ የታሪክ፣ የዘገባና የኢስናድ ሰዎች በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት ነገር ቢኖር ራፊ - ዳዎች ከሁሉም አንጃዎች የመጨረሻ ውሸታሞቹ መሆናቸውን ነው። ውሸት እነሱ ዘንድ ጥንታዊ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የኢስላም ሊቃውንት ራፊ - ዳዎች በውሸት ብዛት ከሌሎች ልቀው መውጣታቸውን መስክረዋል።" (መጅሙዑል ፈታዋ፡ 1/59)
=
(ኢብኑ ሙነወር፣ መስከረም 17/2006)
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor