Get Mystery Box with random crypto!

እንኳን አደረሰን - አደረሳችሁ ኅዳር 17 የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ፍልሰተ ዓፅሙ ነው። | ጥበብ በእርስው

እንኳን አደረሰን - አደረሳችሁ

ኅዳር 17 የቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ፍልሰተ ዓፅሙ ነው።

ይህ ታላቅና ክቡር፣ የዓለሙ ኹሉ መምህር፣ የቊስጥንጥንያ ፓትርያርክ የኾነው አባት ያረፈው በ407 ዓ.ም. በስደት እያለ ነው፡፡ ወደ ስደት ያጋዘችውም በመንግሥት ይደረጉ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችን እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ፊት አይቶ ሳያዳላ ይገሥጽ ስለ ነበር፥ አውዶክስያ የተባለች የንጉሥ አርቃድዮስ ሚስት ነች፡፡ ፍልሰተ ዓፅሙ የተከናወነው በንግሥቲቱ ልጅ በቴዎዶስዮስ ዘይንእስ ዘመነ መንግሥት በ438 ዓ.ም. ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሕዝቡ ዘንድ እጅግ ይወደድና ይከበር የነበረ አባት ስለ ነበር ገና በስድሳ ዓመቱ ማረፉ ለሕዝቡ እጅግ መራር ኀዘን ነበር፡፡ ይህም ዘወትር በልቡናቸው ሰሌዳ በሕሊናቸው ጓዳ ይኖር ነበር፡፡

በ434 ዓ.ም. የቊስጥንጥንያ ፓትሪያርክ የኾነውና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ደቀ መዝሙር የነበረው ቅዱስ ኤራቅሊስ አንድ ቀን በሃጊያ ሶፊያ እያስተማረ ሳለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን እያመሰገነ ሰበከ፡፡ እንዲህም ይል ጀመር፡- “ዮሐንስ ሆይ! መላ ዘመንህን በኀዘን በመከራ አሳለፍህ፤ ዕረፍትህ ግን የተወደደች የተከበረች ኾነች፡፡ ቅዱሱ ሰውነትህ ያረፈባት መካን ንዕድ ክብርት ናት፡፡ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረትና ቸርነትም የጊዜንና የቦታን አጥር ወሰን ድል አደረግህ፡፡ ፍቅርህ የቦታን ወሰን አለፈ፤ መታወስህ መዘከርህ ይህን አጥርና ድንበር አፈረሰ፡፡...”

ቅዱስ ፓትሪያርኩ ኤራቅሊስ ይህን እየተናገረ ሳለ ቃሉን ያደምጡ የነበሩት ኹሉ ማልቀስ ጀመሩ፤ ስብከቱን እንኳን ሊያስፈጽሙት አልተቻላቸውም፡፡ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በፓትሪያሪኩ እግር ሥር ወድቀው ወደ ንጉሡ ኼዶ የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ዓፅም ወደ ቊስጥንጥንያ ተመልሶ ይመጣ ዘንድ እንዲማልደው ተማጸኑት፡፡

ቅዱስ ኤራቅሊስም ወደ ንጉሡ ኼደ፤ የምእመናኑን ተማጽኖም ነገረው፡፡ ንጉሡም ይኹን ይደረግ ብሎ ፈቀደ፡፡ የቅዱሱን ሰውነት የሚያመጡ መልእክተኞችንም አዘዘ፡፡

ኾኖም መልእክተኞቹ የቅዱሱን ሰውነት ማንሣት አቃታቸው፤ እጅግ ከበዳቸው፡፡ ይህንንም ለንጉሡ ነገሩት፡፡ ንጉሡም የጻፈው ትእዛዝ እንደ ነበረ በማስታወስ ለቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የተማጽኖ ደብዳቤ ላከ፡፡ ይቅርታን እንዲያደርግለትና ወደ ቊስጥንጥንያ ይመጣ ዘንድ ፈቃዱ እንዲኾን የሚማጸን ደብዳቤ ነበር፡፡ ደብዳቤው በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ መካነ መቃብር ላይ ተነበበ። መዝሙር ተዘመረ። ምስጋና ደረሰ። ከዚያም መልእክተኞቹ የቅዱሱን ሰውነት ማንሣት ተቻላቸው፡፡ የዕንቊ ፈርጦች ባሉት የእብነ በረድ ሳጥን ውስጥ አድርገውም በታላቅ ክብር ወደ ቊስጥንጥንያ አፍልሰው አመጡት፡፡

የቅዱሱ ሰውነት መጀመሪያ ያረፈው በሃጊያ ኤሬነ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤራቅሊስ ሳጥኑን በከፈተው ጊዜም የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰውነት ሳይፈርስ ሳይበሰብስ ተመለከተ፡፡ ንጉሡም እጅግ እያነባ ስለ አሳደደችው እናቱም ይቅርታን እየለመነ ወደ ቅዱሱ ሰውነት ቀረበ፡፡ ሕዝቡም ቀኑን ሙሉና ሌሊቱን ኹሉ የቅዱሱ ሰውነት ካለበት ሳጥን ሳይርቁ ውለው አደሩ፡፡

ጠዋት ሲኾንም የቅዱሱ ሰውነት ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ተወሰደ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፡- “አባ አባ መንበርህን ተረከብ” እያሉ አሰምተው ተናገሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ከቅዱሱ ሰውነት አጠገብ የነበሩት ቅዱስ ኤራቅሊስና ካህናት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ሰላም ለኵልክሙ - ሰላም ለእናንተ ይኹን” ሲል ሰሙት፡፡ ብዙ ሕሙማንም ተፈወሱ፡፡
------------
የቅዱሱ በረከትና ረድኤት አይለየን!
------------