Get Mystery Box with random crypto!

ሰአ(ዓ)ሊ ለነ ቅድስት በቸርነቱ ብዛት በአንቺ ምልጃ ኃጢአታችንን ከሚያሥተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት | ቅ/ማ/ዩኒቨርስቲ ግቢ ጉባዔ

ሰአ(ዓ)ሊ ለነ ቅድስት

በቸርነቱ ብዛት በአንቺ ምልጃ ኃጢአታችንን ከሚያሥተሰርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና፤ ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኝልን፤ አዕምሮውን ጥበቡን ለብዎውን በልቡናችን ሳይልን አሳድሪልን። 'ለነ' ለእኛ ጥቅም ነውና። ሳይብን አሳድሪብን ሰ(ዓ)አሊ ብነ ቢሆን ነበር።

ቅድስት አለ፦ ንጽሕት ፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው።

ንጽሕትም አለ፦ ሌሎች ሴቶች ከገቢር ቢነጹ ከነቢብ ከሀልዮ አይነጹም። ከነቢብ ቢነጹ ከገቢር ከሀልዮ አይነጹም። ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሀልዮ አይነጹም። እርሷ ግን ከነቢብ፣ ከገቢር ከሀልዮም ንጽሕት ናትና።
"ወኢረኲሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በህሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ" እንዲል።

ጽንዕትም አለ፦ ሌሎች ሴቶች በድንግልና ቢጸኑ ለጊዜው ነው። በኋላ ግን ተፈትሖ ያገኛቸዋል። እርሷ ግን ቅድመ ጸኒስ፤ ጊዜ ጸኒስ፤ ድኅረ ጸኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፤ ጊዜ ወሊድ፤ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት ናትና።

ክብርትም አለ፦ ሌሎች ሴቶችን ብናከብራቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ነገሥታትን፣ ነቢያትን ሐዋርያትን ወለዱ ብለን ነው። እርሷን ግን ወላዲተ አምላክ ብለን ነውና።

ልዩም አለ፦ እናትነትን ከድንግልና፤ ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ የምትገኝ ከእመቤታችን በስተቀር ሌላ ሴት የለችምና።

ሰዓሊ ለነ ቅድስት
ዐይኑ 'ዓ' ቢሆን አዕምሮውን (እውቀቱን)፤ ለብዎውን ( ያወቅነውን ማስተዋሉን)፤ ጥበቡን (በተገቢው ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ በሕይወት መተርጎሙን) በልቡናችን ሳይልን አሳድሪልን።

ሰአሊ ለነ ቅድስት

አልፋው 'አ' ቢሆን፦ ለምኝልን ማለት ነው። ልመናስ በወዲያኛው ዓለም እንኳንስ በእሷ በሌሎችም ቅዱሳን የለባቸውም በቀድሞ ልመናዋ የምታስምር ስለሆነ እንዲህ አለ እንጂ።

'ሰአ(ዓ)ሊ ለነ ቅድስ'ን ማን ተናግሮታል ቢሉ፦
ቅዱስ ኤፍሬም ተናግሮታል። ይህማ እንዳይሆን በግብጻውያን በመጽሐፋቸውም በቃላቸውም አይገኝምሳ ብሎ ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መክፈያ ተናግሮታል። ቅዱስ ያሬድስ ከየት አምጥቶ ከሰው መጽሐፍ አስገብቶታል ተናግሮታል? ቢሉ፦ 'ሰአሊ'ን 'ሰአሊ ለነ ሀበ ወልድኪ ኄር መድኀኒነ' ካለው 'ቅድስት'ን 'ኦ ድንግል ኦ ቅድስት' ካለው አምጥቶ አስገብቶታል ተናግሮታል።
አንድም የኋላ ሊቃውን ተናግረውታል ይላሉ።

ይሄን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ታርጋለች። እርሱም ተባርኮ እጅ ነስቶ ይቀራል። በነገው እለት ትመጣለች።

"ውዳሴሃ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ዘይትነበብ በእለተ..."
ይህ ጉባኤ ነው። ይቆየን!
አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!

ነሐሴ 1/2014 ዓ.ም

Hailat ze Dingil ሥመ ጥምቀቱ ወልደ ሐና በጸሎታችሁ አስቡኝ

በዚህ ቻናል የኢ/ኦ/ተ ቤ/ክ ትምህርቶች ይተላለፉበታል።
" አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤"
(2ኛጢሞ 3፥14)
ለማንኛውም ጥያቄና አስተያየት
@DnHaile ወይም
@DnHaileBot ላይ ያስቀምጡልን