2024-05-15 13:15:14
በሰሜን ሸዋ ዞን በሁለት ወረዳዎች በተመሳሳይ ቀን በደረሰ የድሮን ጥቃት የበርካታ ሰላማዊ ሠዎች ሕይወት አለፈ!!
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ ጉሎ በተባለ ትምህርት ቤት እና ሞላሌ ወረዳ እሁድ ግንቦት 4፤ 2016 ዓ.ም. በደረሰ የድሮን ጥቃት ከአስር በላይ ሠላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ተገለጸ።
ከቀወት ወረዳ ዋና መቀመጫ ሸዋሮቢት በግምት 20 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የጉሎ (ጎጥ) አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከቀኑ 7፡30 ገደማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አራት ሠዎች ሲገደሉ አምስት ሠዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዐይን እማኞችና የተጎጂ ቤተሰቦችን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል።
ዶይቼ ቬለ የዜና ወኪል በቀዎት ወረዳ እና ሞላሌ ወረዳዎች በዕለቱ ተፈጸመ በተባለ የሰውአልባ ድሮን ጥቃት 14 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ዘግቧል።
በትምህርት ቤቱ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት መምህራንና የአካባቢው ማሕበረሰብ የወላጅ መምህራን ህብረት (ወመህ) ስብሰባ ላይ በነበሩበት ቅጽበት መሆኑን ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የስብሰባው ተካፋይ፤ በጥቃቱ እሳቸውም ጭንቅላታቸው ላይ እንደቆሰሉ ገልጸዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ የስብሰባው ተሳታፊዎች ሲሆኑ፤ ሁለቱ ደግሞ የት/ቤቱ ዙሪያ ላይ የነበሩ ሠላማዊ ሠዎች እንደሆኑ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌላ የአይን እማኝ ተናግረዋል።
የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው ወደ አካባቢው በፍጥነት እንዳመሩ የተናገሩ አንድ የዐይን እማኝ እንደደረሱ አስከሬን ማየታቸውን ጠቅሰው፤ የአራት ሠዎች ሕይወት ማለፉንና በርካታ ሠዎች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
ተመሳሳይ ዞን በሞላሌ ወረዳ መዘዞ ተብላ በምትጠራው ከተማ አጠገብ በተጣለ ሌላው የድሮን ጥቃት ሶስት የፋኖ አባላት እና በመጠጥ ሽያጭ ላይ የተሰማራች አንድ ሴት ጨምሮ አራት ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዶይቸ ቼለ ዘግቧል።
@sheger_press
@sheger_press
8.5K views10:15