Get Mystery Box with random crypto!

​​ርዕስ #ያልነገርኩሽ_ነገር #ሰውሲኖር ክፍል-፪ ሚናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት | 🤓 ሰው ሲኖር-Sew Sinor‍

​​ርዕስ #ያልነገርኩሽ_ነገር
#ሰውሲኖር
ክፍል-፪


ሚናን ለመጀመሪያ ጊዜ ያያት እሱ በሚያስተምርበት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመምህርነት ቅጥር ለቃለ መጠይቅ ቀርባ ነው፡፡ የቅጥር ኮሚቴ ውስጥ ነበረበት፤ ቃለ መጠይቅ ከሚያደርጉ አራት ሰዎች አንዱ እሱ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹ ተደጋጋሚ ስለነበሩ እና ተወዳዳሪዎቹም ብዙ ስለነበሩ ሰልችቶት፣ አቋርጦ ሲጋራ ሊያጨስ ወጣ፤ ሲመለስ ሚና እየተጠየቀች ደረሰ፡፡ ስታየው ደነገጠች፤ ሲያያት ደነገጠ፡፡ እርጋታዋ ገርሞታል፤ በጣም ተረጋግታ ነው የምትመልሰው፡፡
ፍርሃትም የለባትም፤ ለመመሰጥም አትሞክርም፤ ትጠየቃለች፤ በእርጋታ ትመልሳለች፡፡
“ሚና ጥያቄዎቻችን አልቀዋል፤ እናመሰግናለን፤ ውጤቱን ደውለን እናሳውቅሻለን፡፡” አለ የኮሚቴው ሰብሳቢ፡፡
“ቆይ፤ ቆይ እኔ አንድ ጥያቄ አለኝ፤ ለሚና፡፡” አለ ሀሌሉያ፡፡
“ጥሩ እንግዲህ፡፡” አለ የቅጥር የኮሚቴው ሰብሳቢ፤በቅሬታ፡፡
“ሚና?”
“እህ?”
“የወንድ ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልሽ ምን ታደርጊያለሽ?”
ያልተጠበቀ ጥያቄ ነበር፡፡ መገረም እና ፈገግታ ሰፈነ፡፡ሁሉም የሚናን መልስ እየጠበቁ ነው፡፡ ከረዥም ፀጥታ በኋላ፤ “የወንድ ተማሪዬ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ ምን አደርጋለሁ ነው አይደል ጥያቄው?”
“አዎ፡፡” አሉ አራቱም አንድ ላይ፡፡
“በመጀመሪያ ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ሁሉም ሳቁ፡፡
“እሺ ከዛስ?” አላት ሀሌሉያ ሲስቅ ያነባውን እንባ ከአይኑ እየጠረገ፡፡
“ከዚያ ባልቆነጠጥኩት ጆሮው በኩል አርፎ እንዲማር እነግረዋለሁ፡፡” ሳቅ፡፡
አሁን ሚና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የህግ የትምህርት ክፍልን ተቀላቅላ የመምህር ሀሌሉያ የስራ ባልደረባ ሆናለች፡፡ ሚና ስትቀጠር ሀሌሉያ ካቀረበላት አስቂኝ ጥያቄ ወዲህ አውርተው አያውቁም፡፡ ያኔ መጠየቅ የፈለገው ጥያቄ “ተማሪሽ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ሳይሆን “የስራ ባልደረባሽ የፍቅር ጥያቄ…” እንደሱም አይደለም፡፡ መጠየቅ የፈለገው “እኔ፣ ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ ባቀርብልሽ መልስሽ ምን ይሆናል?” ብሎ ነው፡፡ ሁለቱም ተግባብተዋል፤ ሁለቱም ተዋደዋል፡፡
እሷ “ሀሌሉያ የፍቅር ጥያቄ ቢያቀርብልኝ፤ በሀሴት ይህን ጥያቄ ያቀረበውን አፉን ድብን አድርጌ እስመዋለሁ፡፡” ብትለው ነበር ፍላጐቷ፤ ግን - “ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡” ብላ አሾፈችበት፡፡ የሚገርመው ይህን መልሷን ሲሰማ ሀሌሉያ እየሳቀ በግራ እጁ፤ ቀኝ ጆሮውን ሲያሽ ነበር፡፡ ይህ ፍቅር ይሉት ነገር ሁሌ ይገርማል፡፡ ሁለቱም ልጆች በዚያ ቅጽበት ተዋደዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ እንደተዋደዱ ማወቃቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በመጀመሪያ እይታ የሚከሰት ፍቅር ጣዕሙም፤ ጥልቀቱም፤ እርቀቱም፣ አንደኛ ነው፡፡
ከመላመድ የሚመጣ ፍቅር፣ ፍቅር አይደለም፤ ኑሮ ነው፡፡ ሚና ሥራ ከጀመረችበት ቀን አንስታ ተስፋ ነበራት፡፡ ይህ ዋዘኛ የስራ ባልደረባዋ አንድ ቀን፣ በቅርብ ቀን ጥያቄውን እንደሚያቀርብላት እርግጠኛ ነበረች፡፡
እንዲያውም መልሷን አዘጋጅታለች፤ ምን እንደምትል ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምትለውም ተለማምዳለች፤ ግን...
ይቀጥላል


ሌሎችም እንዲያነቡት በቅንነት ሼር አድርጉት
@Sewsinor @Sewsinor