Get Mystery Box with random crypto!

ከዚያም በአይቬሮን ገዳም ያለችው የእመቤታችን ሥዕል ድንቅ ተአምር በዓለም ኹሉ ላይ ከተሰማ በኋላ | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

ከዚያም በአይቬሮን ገዳም ያለችው የእመቤታችን ሥዕል ድንቅ ተአምር በዓለም ኹሉ ላይ ከተሰማ በኋላ በረከቷን ለማግኘት ክርስቲያኖች ወደዚያች ገዳም መኼድን ጀመሩ፤ ይኽ የተቀደሰ ሥዕሏና ታሪኳም ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለሙ ኹሉ ላይ ተሰማ፤ ምእመናንም ይህንን ሥዕሏን በመላው ዓለም በማሣል መማፀን ጀመሩ። ዛሬም በዚህች ሥዕል ምእመናን ይማፀኑበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሰበታ ጌቴሴማኒ ማርያም ገዳም በጼዴንያ ማርያም በክብር የተቀመጠች ሥዕሏን ለመመልከት ችያለሁ።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዐይናቸው ማየት አቁሞ የነበሩት ወይዘሮ አልማዝ ስለዚኽች የተቀደሰች ሥዕል ታሪክ ልጆቻቸው ሲያነቡላቸዎ ሥዕሏን ፕሪንት እንዲያደርጉላቸው በመናገር ዐይናቸው ላይ ማደረጉት ጊዜ የጠፋ ዐይናቸው በርቶላቸው ይኽንን ምስክርነታቸውን በእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳምና በሰአሊተ ምሕረት ደብረ ምጥማቅ ማርያም ወክርስቶስ ሠምራ ቤተ ክርስቲያን በነበረን የእመቤታችን ጉባኤ የተቀደሰ ሥዕሏን አጅበን ተባርከንበታል። እርሳቸውም በዐውደ ምሕረት ላይ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።




ለአባ ገብርኤል የተለመነች እና በረከቷን እንዳሳደረችበት ዛሬም በረከቷ ምንም ሳንይዝ ባዷችንን ጥለነው በምንሄደው በዚኽ ኃላፊ ጠፊ ዓለምና፤ በማያልፈውም በወዲያኛውም ዓለምም እንዳይለየኝ በመማፀን አባ ጽጌ ድንግል ስለዚኽች ሥዕል በማሕሌተ ጽጌ ላይ ባመሰገናት ምስጋና፦

“ቦ አመ ትትረከብ ምስለ ቃለ ነገር ጥዑም
ወቦ አመ ትትረአይ በለቢሰ አባል ልምሉም
ሥዕልኪ ማርያም ጽጌ ተአምር አዳም
ወአመ ዘበጣ በሰይፍ አይሁዳዊ ርጉም
እምኔሃ አንጸፍጸፈ ደም”

(ሥዕልሽ ቃልን ደስ ከሚያሰኝ ነገር ጋራ የምትገኝበት ጊዜ አለ፤ የለመለመ አካልንም ለብሳ የምትታይበት ጊዜ አለ፤ ማርያም ሥዕልሽ የተአምር አበባ ናት፤ ርጉም አይሁዳዊ በሰይፍ በመታት ጊዜ ከርሷ ሥዕል ደም ተንጠባጠበ) በማለት አመሰግናታለሁ፡፡

በመጨረሻም በጽሑፌ የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ በምልጃሽ እና በቃል ኪዳንሽ የማይጠገበው በረከትሽን ዕጽፍ ድርብ አድርገሽ አሳድርቢን በማለት "በኢትዮጵያ ወግብጽ ወሶርያ በአንጾኪያ ወሮም
ለሥዕላትኪ ዘሀለዋ ማርያም ሰላም"
(በኢትዮጵያና በግብጽ፤ በሶርያ በአንጾኪያና በሮም ላሉ ሥዕሎችሽ ማርያም ሆይ ሰላም እላለሁ) በማለት በሊቁ ሰላምታ ለከበረ ሥዕሏ የአክብሮት ሰላምታ በማቅረብ ጽሑፌን አበቃለሁ።

እስቲ እናንተም በተቻላችኊ መጠን በተሰማችኊ ልክ አመስግኗት። እመቤታችንም በዓለም ላይ ከፈሰሰው መቅሠፍት በቃል ኪዳኗ ትጠብቀን።

(ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ) በድጋሚ ፓስት የተደረገ