Get Mystery Box with random crypto!

ከዚያ የነበሩ አይሁድም በመደናገጥ “ሳሚናስ ምን አየኽ? ምን ትላለኽ?” አሉት፤ ርሱም “ከዚች ከሐ | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

ከዚያ የነበሩ አይሁድም በመደናገጥ “ሳሚናስ ምን አየኽ? ምን ትላለኽ?” አሉት፤ ርሱም “ከዚች ከሐና ማሕፀን የምትወለደው ሕፃን ሰማይ ምድርን የፈጠረ አምላክን ትወልዳለች እያሉ መላእክት ኹሉ ሲያመሰግኗት ሰማኋቸው፤ እኔንም ያነሣችኝ ርሷ ናት” አላቸው፤ እነርሱም ይኽነን በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ በቅናትና በክፋት ተመልተው ሐና በማሕፀን ባለ ፅንሷ ካዳነች በኛ ላይ ልትሠለጥን አይደለምን? “ንዑ ንገሮሙ ለሐና ወለኢያቄም” ሳትወልድ አስቀድመን ሐናና ኢያቄምን በድንጋይ ወግረን እንግደላቸው ብለው ተነሣሡባቸው።

ያን ጊዜ ታላቁ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገልጾ ሐናን ሊባኖስ ወደሚባል ተራራ እንዲወስዳት ነገረው፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ እንደምትወለድ ተገልጾለት፡-
“ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ እምሊባኖስ ንዒ ወተወፅኢ እምቅድመ ሃይማኖት እምርእሰ ሳኔር ወኤርሞን አምግበበ አናብስት ወእምአድባረ አናምርት” (ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ነዪ ከሊባኖስ ነዪ ከአማና ራስ ከሳኔር ከኤርሞን ራስ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ) በማለት የተናገረው ትንቢት ሊፈጸም ቅድስት ድንግል ማርያም በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች (ማሕ ፬፥፲)፡፡

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ የነገረ ማርያም መጽሐፋቸው ላይም፦
“ለንጉሠ ነገሥት ሰሎሞን ከመ ተፈሥሐ ልቡ
በዕለተ ወፃእኪ መርዓት ለአንበሳ ትንቢት እምግቡ
ማእከለ ማኅበር ፍሡሓን ተአምረኪ እንዘ እነቡ
እዜምር ለኪ ጽጌ ሐና ወፍኖተ ነፈርዐጽ እሌቡ
ከመ ጣዕዋ ሐሊበ ዘይጠቡ”

(ትንቢት ከተነገረለት ከአንበሳ ጉድጓድ፤ ድንግል ሙሽራ በተገኘሽ ጊዜ የንጉሦች ንጉሥ የሰሎሞን ልቡ እንደተደሰተ፤ ደስ ባላቸው በመላእክት አንድነት ፊት ታምርሽን እየተናገርኊ የሐና አበባ ማርያም እዘምርሻለኊ፤ ወተትን ጠብቶ እንደሚዘልል እንቦሳም ዝለል ዝለል ይለኛል) በማለት ሰሎሞን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቶ ታላቅ ደስታን ለኹላችን እንደሰጠን አብራርተው ገልጠዋል፡፡

ይኽ የእመቤታችን ልደት ለሰማያውያን መላእክትና ለደቂቀ አዳም ደስታ ሲኾን አካላዊ ቃል ክርስቶስ ከርሷ ተወልዶ ዲያብሎስ ፭ሺሕ፭፻ ዘመን በሲኦል ያኖራቸውን ነፍሳት ወደ ገነት የሚያስገባቸው ነውና፤ ሰይጣን በተቃራኒው ልደቷ እንዳላስደሰተው ሲገልጹ፦

“ተፈሥሐት ምድር ወሰማይ አንፈርዐጸ
በዕለተ ጸገዩኪ አብላስ ወአውጽኡ ሠርጸ
ተአምረ ሕይወት ማርያም ዘአልብኪ ቢጸ
እስከ ፈርሀ መልአከ ሞት ወሰይጣን ደንገጸ
ዜና ልደትኪ ነጐድጓድ እስከ (ውስተ) ሲኦል ደምፀ”

(በለሶች (ኢያቄምና ሐና) ቡቃያ አንቺን ባስገኙሽ ጊዜ ምድር ደስ አላት ሰማይም ደስ አለው፤ ጓደኛ (ምሳሌ) የሌለሽ የድኅነት ምልክት ማርያም፤ መልአከ ሞት እስከ ፈራና ሰይጣንም እስከ ደነገጠ ድረስ የመወለድሽ ዜና እስከ ሲኦል ድረስ (በሲኦል) ተሰማ) በማለት አስተምረዋል፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን አስቀድሞ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ በማሕልይ 6:10 ላይ “መኑ ይእቲ ዛቲ እንተ ትሔውጽ ከመ ጎሕ ሠናይት ከመ ወርኅ ወብርህት ከመ ፀሓይ” (ይኽቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጐበኝ እንደ ጨረቃ የተዋበች፤ እንደ ፀሓይም የጠራች ዐላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?) በማለት እንደ ፀሓይ የሞቀ እንደ ጨረቃ የደመቀ ንጽሕናዋና ቅድስናዋ የመልኳ ደም ግባት በነቢያት ትንቢት አስቀድሞ የተጐበኘላት የእውነት ፀሓይ የክርስቶስ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና ደም ግባቷን እንደተናገረ በሊባኖስ ተራራ በግንቦት ፩ በተወለደች ጊዜ ፊቷ በእጅጉ ያበራ ነበር፤ መዐዛዋም ከሽቱ ኹሉ ይበልጥ ነበር፡፡

የፈጣሪያችን እናት ቅድስት ድንግል የተወለደችበትን ግንቦት አንድን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን “ልደታ ለማርያም” በማለት ከጥንት ዠምሮ በታላቅ መንፈሳዊ ሐሤት በቅዳሴ፣ በማሕሌት የምታከብርላት ሲኾን፤ በተለያዩ ክፍላተ ዓለማት ያሉ ክርስቲያኖችም ይኽነን በዓል “The Nativity of the blessed Virgin Mary” (የተባረከችው የድንግል ማርያም ልደት (መወለድ)) በማለት ያስባሉ።

በጥንት ምሥራቃውያን (እንደ ቤዛንታይን ባሉ) ዘንድ ዐዲሱ ዓመት ልክ እንደኛ መስከረም ወር “September” ላይ ይውል ስለነበር መስከረም ፰ (September 8) ያከብሩት የነበረ እንደነበር ታሪክ ሲያስረዳ ይኽነን ይዘው በዚኽ ዕለትም የሚያከብሩት ብዙዎች የዓለማት ሀገራት አሉ፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
[ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፤ ነገረ ማርያም በሊቃውንት ክፍል አንድ ከሚለው መጽሐፌ የተወሰደ]

እኔ ታናሽ አገልጋይሽም እመቤቴ ወላዲተ አምላክ ሆይ የፀሐይ መገኛ ሰማይ፤ የመና እናት መሶብ፤ የፍሕም እናት ማዕጠንት፤ የብርሃን እናት መቅረዝ፤ የጠል እናት ፀምር ተገኝተሻልና በልደትሽ ደስ ብሎናል። እናቴ ሆይ እንኳን ተወለድሽ እላለሁ።