Get Mystery Box with random crypto!

[የአምላክ እናት ልደት (ልደታ ለማርያም)] በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ ቀደምት የቤተ | መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶክተር) Dr Rodas Tadese

[የአምላክ እናት ልደት (ልደታ ለማርያም)]
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መተርጒማን እንዳስተማሩንና አበው በነገረ ማርያም ላይ እንደጻፉልን ሐናና ኢያቄምንም “ወክልኤሆሙ ኄራን ወሥሙራን እሙንቱ ወየሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር እስመ እግዚአብሔር ኀረዮሙ ወአፍቀሮሙ ትካት” ይላቸዋል እግዚአብሔርን የሚወድዱ በሕጉ የሚኖሩ ደጋጎችና አምላክም የመረጣቸው ነበሩ።

ሐና መካን በመኾኗ ምክንያት ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ እንደነበር፤ “Protoevangelium of James” (ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) የሚለው ያዕቆብ የጻፈው ጥንታዊዉ መጽሐፍ በስፋት ይገልጻል፡፡

ከዕለታት ባንደኛው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ “ወርእዩ አርጋበ እንዘ ይትፌሥሑ ምስለ ውሉዶሙ” ይላል ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ሐና “አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሣኸኝ” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ወዲያው ሱባዔ ይገባሉ፤ ኢያቄም ወደ በረሓ ኼዶ ሲጸልይ ሐና ደግሞ በቤቷ ዙሪያ ባለው የተክል ቦታ ሱባዔ ያዘች።

በሱባዔያቸው ፍጻሜ ኹለቱም ራእይ አይተው ተነጋግረዋል፡፡ “ይቤላ ኢያቄም ለሐና ብእሲቱ እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ” ይላል ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዎፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ብሎ የተገለጸለትን ለሐና ነግሯታል።

ይኸውም የራእዩ ምስጢር፡- ወፍ የተባለው አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሲኾን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፤ ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ሲያጠይቅ ሲኾን፤ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልአቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ ናቸው፡፡

ሐናም ተገልጾላት “ትቤሎ ሐና ለኢያቄም ብእሲሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ” ይላል ለባሏ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ብላዋለች።

ይኽ የራእይ ምስጢር፡- ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትኾን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ ወደ ዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በዦሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መኾኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡

ኢያቄምና ሐናም ይኽነን ራእይ ሐምሌ ፴ ቀን ካዩ በኋላ “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ስእለት ከተሳሉ በኋላ ራእይ አየን ብለው ዕለቱን አልተገናኙም፤ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት” ብሎ የተናገረው አምላክ ለእኛም ይግለጽልን ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ እየብቻቸው ሰነበቱ።

ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን “ከሰው የበለጠች ከመላእክት ኹሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችኊ" ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሐና ነግሯት በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን ነሐሴ ሰባት እሑድ ተፀንሳለች፤ በእናቷ ማሕፀን ሳለችም “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ” እንዲል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥንተ አብሶ ባመጣው መርገም እንዳትያዝ ጠብቋታል፡፡

ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም መፀነስ ከሊቃውንት መኻከል አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ፦

“ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ
ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ
ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ
እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ
ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ”

(ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ) በማለት ዓለምን ኹሉ በደሙ ፈሳሽነት ያዳነ ንጉሣችን፣ ፈጣሪያችን ክርስቶስን በድንቅ ተአምር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችልን ምክንያተ ድኂን ርግበ ሰሎሞን የተባለች የቅድስት ድንግልን የመፀነሷን ነገር በአድናቆት ገልጸዋል፡፡

“ወእምድኅረ ስድስቱ አውራኅ ተዐውቀ ፅንሳ ለሐና” ይላል፤ ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ ሲመጣ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ይረዱ ዘንድ በአድናቆት ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፤ በተለይም ዐይኗ የታወረ የሐና ዘመዷ የአርሳባን ልጅ የምትኾን አንዲት ሴት የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በርቶላት በታላቅ ደስታ ኾና “ብፅዓን ለኪ ኦ ሐና እስመ እም ፍጥረተ ዓለም አልቦ ዘከማኪ ዘይፌውስ በከርሡ አዕይንተ ዕውራን” (ሐና ሆይ ብፅዓን ይገባሻል ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እንዳንቺ በማሕፀኑ የዕውራንን ዐይን የሚያበራ የለምና) በማለት አመስግናታለች፤ ከዚኽ በኋላ ዝናዋ በሀገሩ ኹሉ ተሰምቶ ሕሙማን ኹሉ ማሕፀኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፡፡

አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ይኽነን ሲገልጹ፦
“ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ
ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ
ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ
እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ
ለለገሰስዋ ላቲ ትፌውስ ዱያነ”

(ሳርን የኾንኊ እኔ የኪሩቤል አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር) በማለት እመ መድኅነ ዓለም ገና ሳትወለድ የተሠራውን ድንቅ ተአምር አመስግነዋል፡፡

ይኽ የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰት በዓል በመላው ዓለም የሚታወቅ ሲኾን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የአምላክ እናት የተፀነሰችበት ይኽነን በዓል ነሐሴ ፯ ቀን በታላቅ ድምቀት በማሕሌት፣ በቅዳሴ የምታስበው ሲኾን በዓሉም “ፅንሰታ ለማርያም” በመባል ይታወቃል።

በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በዓሉን “The conception of the Theotokos” (የአምላክ እናት መፀነስ) በማለት ሲያከብሩት ወሩን ግን የልደት በዓልን ለማክበር በሚዘጋጁበት በታኅሣሥ አድርገው በ፱ኛው ቀን “December 9” ላይ ያስቡታል ፡፡

በእጅጉ የሚደንቀው ደግሞ “ሳሚናስ ወልደ ጦሊቅ ዘይነብር ውስተ ቤተ ዶይቅ” ይላል ሳሚናስ የሚባል የጦሊቅ ልጅ ከኤዶቅ ካጐቱ ቤት ኼዶ ሞተ፤ ሐናም በሀገራቸው ልማድ የአልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ፈጥኖ ተነሥቶ “ሰላም ለኪ ኦ ሐና እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” (ሰማይና ምድርን ለፈጠረው አምላክ አያቱን የተባልሽ ሐና ሰላም ላንቺ ይኹን) አላት።