Get Mystery Box with random crypto!

አድርሱልኝ ለክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ መቼ ነው በሉልኝ...? በቅድ | ታታ አፍሮ -Tata Afro

አድርሱልኝ ለክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/

መቼ ነው በሉልኝ...?

በቅድሚያ ግን ይኼንን ጽሁፍ እስካጠናከርኩበት ሰዓት ድረስ "ናዕት" /የህዝብ ድምጽ/ የሆነው ሙዚቃ ከተለቀቀ 18 ቀናቶችን አስቆጥሯል። በነዚህ ቀናቶች ውስጥ ሙዚቃውን በቀን ውስጥ ደጋግሜ ሳላዳምጥ ያለፍኩበት ቀን ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። መኪና ስነዳም ሆነ ስራ ቦታ ቁጭብዬ፥ ስተኛም ሆነ በቡና ሰዓት ላይ፥ ከተማው ውስጥ ስዘዋወርም ሆነ ከከተማ ውጪ ለጉዳይ በወጣሁበት አጋጣሚ ሁሉ ይኼንን ሙዚቃ ከመስማት አልቦዘንኩም።

ደጋግሜ ያለ መሰልቸት ማዳመጤ ሙዚቃውን ቴዲ አፍሮ ስለዘፈነው እኔም በማይናወጥ ጽኑ መውደድ ሰውዬውን ስለምወደው ብቻ አይደለም ይኼ ሊሆን የቻለው። ይልቁንም ለልቤ የዘመናት ጽኑ ቁስል፥ ግጥም አበጃጅቶ ዜማ ደርድሮ እውነተኛ ህመሜን ስላንጎራጎረው ጭምር ነው። ናዕት እየሰማሁት እንደ አዲስ ያመኛል። እያደመጥኩት እንደ አዲስ ተስፋን ያጭርብኛል። አብሬው እያዜምኩ የወገኔ ስቃይ ይነበበኛል። እየሰማሁት ወገኔ ከህመሙ ሲያርፍ በዐይነ ህሊናዬ ይቀረጽብኛል። ግን ለክቡርነታቸው ጥያቄ ለማቅረብ ልቤ ስለወደደ ከታላቅ አክብሮት ጋ እንደሚከተለው በአደባባይ የልቤን ጥያቄ እጠይቀዋለሁ።

መቼ ነው...?

የክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ሆይ እንዴት ነው እኛን በበደል አለንጋ ሲገርፉን አንተ መድማት የቻልክበት...? በምን ጥበብ ነው የኛ አካል ላይ ያረፈ ቁስል አጥንትህ ድረስ ዘልቆ የተሰማህ...? ምን ያህል ብትቀርበን ነው የውስጣችንን ሀዘን እያመመክ ያዜምከው...? እስከመቼስ ነው ድሆች ስንረገጥ አብረኸን የምትረገጠው...? መቼ ነው ደክሞህ የምትተወን..? መቼ ነው የኛ የወገኖችህ የገላችን ላይ ቁስል አንተን ውስጥ ውስጥህን ማቁሰሉን የሚተወው...? መቼ ነው የኛ ደም አደባባይ ላይ በፈሰሰ ቁጥር አንተ ውስጥ ውስጡን ከመድማት የምታርፈው...? መቼ ነው ልብህ ከእኛ የማያባራ ሀሳብ እርቃ እረፍት የሚኖራት...? መቼ ነው እኛ እንደ ዲዳ የተቆጠርንባቸውን ዘመናቶች አንተ ጮኸ ማስተጋባት የምታቆመው...? መቼ ነው ጎዳና ከወደቅን ጋ ትብብር አቁመኽ በብልጭልጭ ድንኳን ውስጥ የምታድረው...? መቼ ነው ድሃ ወገንህን ትተኽ እርፍ የምትለው...? መቼ ነው በግፍ መገደላችንን ችላ የምትለው...? መቼ ነው አንዴም ቢሆን እንኳን ግፈኞችን በድፍረት ከመናገር የምትቆጠበው...? መቼ ነው ግን እንደ ሌሎቹ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነን እቶን እሳት በላያችን እየዘነበብን ፀሐይ ነው እያልክ የምትፎግረን...? ቆይ እኛ ምን አድርገንልህ ነው እንዲህ በጽኑ የወደድከን...? መቼ ነው ለሁሉ እኩል ማዘን ለሁሉ እኩል መቆርቆር የሚደክምህ...? መቼ ነው እንደ ሌሎቹ አገሬን እወዳለሁ እያልክ የራስህን ጥቅም ለማስከበር የምትሰለፈው...? እኔ ወዳጅህ ልፋ ቢለኝ እንጂ ያንተን መልስ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ። በኩራቶ ሆነኽ እንዲህ ነው የምትለው...

"...በዚህ ለጸና እውነት
የፍቅር ሀገር ከጥንት
ዘብ ያድራል ሁሉም እስከ ሞት
ዶፍ ቢዘንብ እቶን እሳት...!
ዶፍ ቢዘንብ እሳት ሀገሬን ላልረሳት
ቃል አለኝ ኖሬ ሞቼም ልክሳት..."

ምክኒያቱም ባንተ ጨዋ ነፍስ እሳቤ እኛ ነን ላንተ አገር። እኛ ነን ላንተ ዜጎች። ድሃን መውደድ ልክ ሆኖ የታየኽ፤ ከወደቁ ጋ አብሮ ወድቆ መነሳት ስህተት ያልሆነው ባንተ ልብ ውስጥ ብቻ ነው። እግዚአብሔር በኳላቸው ብሩህ ዐይኖችህ አዳፋ ልብሳችን እና በችግር የገረጣው ሰውነታችንን በመጠየፍ ስሜት ሳይሆን በመጠሪያችን /ሰው በሚለው/ የክብር ገጻችን አንጥረኽ በማየት እና አክብረኽ በመጥራት የእግዚአብሔር ወገኖች መሆናችንን በማሳሰብ በናቁን እና በተጠየፉን ሰዎች ፊት ኩራት ሆነኸናል። መንግስት ስለፈሰሰው ደማችን በግፍ ስለተነጠቀች ነፍሳችን ግድ አልሰጥ ብሎት የሀዘን ቀን እንኳን ለማወጅ ቢጠየፈንም አንተ ግን በዜማ የዕልፍ ሰዎችን ስሜት አባብተኽ ልባችን በግፍ ስለወደቁ ወገኖቻችን በሀዘን ሆኖ እንዲያስባቸው አደረከው። ከምድር ሆኖ ወደ እግዚአብሔር የሚጮኸው የንጹሃን ደም አንዲት ቀን በጋራ ሀዘን ታስቦ ብቻ መረሳት ያለበት ሳይሆን የዓለም ህዝብ ተባብሮ ለዘመናት ሲያስባቸው ሊኖር ይገባል ስትል ውስጥን የሚሰብቅ ዜማ ደረደርክላቸው።

የክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን Teddy Afro ሁሌም ከጭቁኖች ጎን በኩራት የምትቆም ጽኑ ሰው ነህና ዛሬም ድረስ በማይናወጥ ጽኑ መውደድ እንወድኃለን!

ዝንፍ በማይል እውነተኛ መውደድ እ...ወ...ድ...ኃ...ለ...ሁ...!





✎ #ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/