Get Mystery Box with random crypto!

ሳይወድቁ የተሠበሩት የ92 ዓመት ታካሚ! —————————————————— ዶ/ር ሠዒድ መሐመድ (የአጥ | ♒Orthopedic Surgery in Ethiopia ♒

ሳይወድቁ የተሠበሩት የ92 ዓመት ታካሚ!
——————————————————
ዶ/ር ሠዒድ መሐመድ (የአጥንት ስፔሻሊስት)
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ሠሞኑን ቀዶ ህክምና ከሠራሁላቸው ታካሚዎች ውስጥ እንደተለመደው ገጠመኙ ትምህርት ይሠጣል ብዬ የገመትኩትን ላካፍላችሁ ነው…

የራጁ ምስል የዘጠና ሁለት ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ ታካሚዬ የዳሌ መገጣጠሚያን የሚያሳይ ሲሆን፣ በግራ በኩል ያለው ("Before" image) የዳሌ መገጣጠሚያቸው አንገት (femoral neck) እንደተሠበረ ያሳያል። በቀኝ በኩል የሚገኘው ("after" image) ደግሞ የዳሌ መገጣጠሚያ ቅየራ (hip replacement) ከሠራሁላቸው በኋላ አርቴፊሻል መገጣጠሚያውን የሚያሳይ ነው።

እንደዚህ አይነት ከፍተኛ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ጉዳቶች በመሠረቱ ከፍተኛ አደጋን ተከትለው የሚከሠቱ ቢሆንም፣ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች ላይ ሲሆን ግን ብዙውን ጊዜ ሻወር ሲወስዱ እንደ መውደቅ አይነት ቀላል አደጋዎችን ተከትለው ሲከሠቱ ይስተዋላል። የዛሬውን ባለታሪካችንን ገጠመኝ ግን "ትምህርት ሠጪ" ያስባለው እና ለመተረክ ያበቃው ግን የተለመደው አይነት "ቀላል የመውደቅ አደጋ" እንኳን ሳይደርስባቸው በመሠበራቸው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው…

አዛውንቱ አባት በደረሰባቸው ከፍተኛ የሳንባ ኢንፌክሽን እና ኢንፌክሽኑን ተከትለው በተከሠቱባቸው ሌሎች ችግሮች ምክንያት ከሁለት ወራት በላይ ተኝተው እየታከሙ ስለነበረ ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀሱ በመቆየታቸው ምክንያት ፣ በእርጅና ጥንካሬውን ያጣው አጥንታቸው ይበልጥ ሊሳሳ ችሏል። አገገሙ ከተባለ በኋላ እንኳን ከአልጋ የሚወርዱት መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም ብቻ፣ እሱም በአስታማሚዎቻቸው (ልጆቻቸው) እገዛ ነበር።

ከአንድ ወር በፊት  ታዲያ አንድ ልጃቸው ለሽንት ብሎ ከአልጋ ላይ ሊያወርዳቸው ሲሞክር ያለምንም ይህ ነው የሚባል አደጋ፣ እግራቸው በአልጋው ጠርዝ ንክኪ ምክንያት ድንገት ስለዞረባቸው ብቻ  ከፍተኛ ህመም ተሰምቷቸው ወደ አልጋቸው ሊመልሳቸው ተገደደ። ራጅ ሲነሱም ከላይ የጠቀስኩት ከፍተኛ ጉዳት እንዳላቸው ታወቀ። ደግነቱ ጊዜው የአጥንት ህክምና በቴክኖሎጂ እና ዘመናዊ አርቴፊሻል መገጣጠሚያዎች የተደገፈበት ጊዜ ስለሆነ በአጭር ጊዜ አገግመው ዳግም ለመራመድ የበቁ ቢሆንም፣ ክስተቱ ግን ቢያንስ ለሌሎቻችን ትምህርት ሊሆን ይገባል።

——————————————————
Take home message:
* የአልጋ ቁራኛ አዛውንቶች አጥንት ያለአደጋም ሊሠበር ስለሚችል፣ አስታማሚዎች ልዩ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። መራመድ እስኪጀምሩ ድረስም፣ የአጥንታቸውን ጥንካሬ ለማቆየት ከምግብ ተጨማሪ ሰፕሊመንቶች ያስፈልጓቸዋል።
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
Follow us on:
YouTube: " Doctor Seid"
የቴሌግራም ቻናል: https://t.me/patientstories
የፌስቡክ ገፅ: የአጥንት ህክምና/Orthopedic Surgery (https://www.facebook.com/EthioOrthopedics/)
ስልክ: +251930099067/ +251935402078