2022-10-24 07:14:59
+ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? +
ዮሴፍ በግፍ የሸጡት ወንድሞቹን ለሁለተኛ ጊዜ ሲያገኛቸው እንዲህ ሲል ጠየቃቸው ‘የነገራችሁኝ ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’ እነርሱ መለሱ ፦ አባታችን ደህና ነው ገና በሕይወት አለ አሉት፡፡ (ዘፍ 43:27)
ዮሴፍ የጠየቀው የአረጋዊውን አባቱን የያዕቆብን ደህንነት ነበር፡፡ እርሱ ወንድማቸው መሆኑን ገና ስላላወቁ ‘አባቴ ደህና ነው?’ በማለት ፈንታ ‘ሽማግሌው አባታችሁ’ አለው፡፡ እርግጥም ያዕቆብ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሴፍ እንደፈራው አልሞተም፡፡ ገና በሕይወት ነበረ፡፡
ይህንን ዮሴፍ ለወንድሞቹ የጠየቀውን ጥያቄ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ጻድቁን አቡነ አረጋዊን ለመጠየቅ በሔደ ጊዜ ዳግም ተናግሮታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ወደ ደብረ ሃሌሉያ ዳሞ ተራራ በደረሰ ጊዜ ከተራራው ግርጌ ዮሴፍና ማትያስ የተባሉ ሁለት የአቡነ አረጋዊ ደቀ መዛሙርትን አገኘ፡፡
‘ዳኅንኑ ዝስኩ አረጋዊ አቡክሙ’ [ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነውን] ብሎም ጠየቃቸው፡፡ ይህ ንግግሩ መልስ አግኝቶ ሳያበቃ ምስጋና ሆኖ በአቡነ አረጋዊ ማሕሌት ይዜማል፡፡ ሽማግሌው አባታችሁ [አረጋዊ አቡክሙ] የተባለለት ጻድቁ አቡነ ዘሚካኤል አረጋዊ ተብሎ ለመጠራት እንደ ያዕቆብ 130 ዓመታት መቆየት አላስፈለገውም፡፡ ገና በዐሥራ አራት ዓመቱ መንኖ ለብዙዎች መመነን ምክንያት የሆነ በዕድሜው ሳይሆን በቅድስናው አረጋዊ ለመባል የደረሰ ጻድቅ ነበር፡፡
ዛሬም ላይ ሆነን የዮሴፍንና የቅዱስ ያሬድን ጥያቄ ደግመን እንመልስ፡፡ ‘’ሽማግሌው አባታችሁ ደህና ነው? ገና በሕይወት አለን?’’ ለሚለን ሁሉ መልሳችን ‘አረጋዊው አባታችን [አቡነ አረጋዊ] ደህና ነው፡፡ አሁንም ድረስ በሕይወት አለ ፤ እግዚአብሔር ሰወረው እንጂ አልሞተም፡፡ የሚል ነው፡፡
ጻድቁ አባታችን አረጋዊ ሆይ ዮሴፍ ስለ አባቱ ደህንነት እንደጠየቀ እኛ ስለ አንተ ደህንነት አንጠይቅም፡፡ እግዚአብሔር ያከበረህ ሆይ ባይሆን እኛ ልጆችህ ግን ደህና አይደለንም፡፡ ነፍሳችን ዛሬ በፊትህ የከበረች ትሁንና ልጆችህን በምልጃህ አስበን፡፡ ዮሴፍ ሽማግሌ አባቱን በፈርኦን ፊት እንዳቀረበ እኛም አረጋዊ አባታችንን በእግዚአብሔር ፊት ትማለድልን ዘንድ በጸሎታችን እናቀርብሃለን፡፡
ከዳሞ ተራራ ላይ ሆነህ ከችግር መውጫ ቸግሮአት ሰማይ ሰማዩን ለምታይ ሀገራችን የምልጃህን ገመድ ወርውርላት፡፡ ሊተናኮሏት የተጠመጠሙባትን ዘንዶዎችም ወደ መልካም ዘመን መወጣጫ መሰላሎችዋ አድርግላት፡፡ ካለችበት ውድቀት ወደ ከፍታ መወጣጫ ወደ መልካም መሸጋገሪያ ገመድ ትፈልጋለችና የጸሎት ገመድህን ላክላት::
ያን ጊዜ እንዲህ ትላለች ፦
ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ’ መዝ 16፡6
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 14 2013 ዓ.ም.
7.7K views04:14