Get Mystery Box with random crypto!

2ቱ መነኮሳት 'ሁለት መነኮሳት ወደ ገዳም ለመሄድ በጉዞ ላይ ሳሉ ከፊታቸው ወንዝ ያጋጥማቸዋል። | የኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ገፅ

2ቱ መነኮሳት

"ሁለት መነኮሳት ወደ ገዳም ለመሄድ በጉዞ ላይ ሳሉ ከፊታቸው ወንዝ ያጋጥማቸዋል። ያን ወንዝ ለመሻገር ሲሞክሩ ሌላ ጥሩ ልብስ የለበሰች አንዲት ሴት ወንዙ ልብሷን እንዳያበላሽባት ፈርታ ግራ በመጋባት ከዳር ቆማ አዩአት። ከሁለቱ መነኮሳት አንዱም ያቺን ሴት በጀርባው ተሸክሞ አሻገራት። ከዚም መንገዳቸውን ቀጠሉ። ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ አንደኛው መነኩሴ "እንዴት ከሴት ልጅ ጋር ያን ያህል ትቀራረባለህ? እንዴትስ እርሷን በመሸከም የምንኩስናን ሕግ የሚቃረን ነገር ታደርጋለህ? እንዴት...?" እያለ ተቃውሞውን ማሰማት ጀመረ። ይሁን እንጂ ያ መነኩሴ ግን ምንም መልስ ሳይሰጠው በዝምታ ይሄድ ነበር። አሁንም ወሳው ቀጥሏል "እንዴት የሴትን ሰውነት ትነካለህ? እንዴት ትሸከማታለህ?" እያለ ደጋግሞ እየተቆጣ ይጠይቀዋል። በስተመጨረሻም ያ መነኩሴ እንዲህ ሲል መለሰለት "እኔ ያቺን ሴት ቅድም ከወንዙ ዳር አውርጃታለሁ። አንተ ግን እስከ አሁን ድረስ ተሸክመሃታል? ለምን አታወርዳትም?"

አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር ይገጥመናል። ሌሎች ለደቂቃ የሠሩትን ጥሩ ያልሆነ ድርጊት እኛ ቀኑን ሙሉ በማሰብ ውስጣችንን እናረክሳለን። ወንድማችን አንድ ጊዜ የፈጸመውን በደል እኛ ኅሊና ውስጥ ሺህ ጊዜ እየደጋገምን እናየዋለን። ምናልባትም ያ ሰው ያንን የበደል ሸክም ፈጥኖ በንስሐ አራግፎት ይሆናል። እኛ ግን ለዚያ ኃጢአት በልባችን የተሻለ ቦታ በመስጠት ከፍ አድርገን እንሰቅለዋለን። ሠሪው ቶሎ ያወረደውን የኃጢአት ሸክም እኛ ታዛቢዎቹ ግን በኅሊናችን ተሸክመን በየሥፍራው እንዞራለን። ለምን አናወርደውም?