2022-02-01 18:52:10
#3D_ፍቅር !!
"...የግራ እጄን በቀኝ እጇ ይዛ በግራ እጇ አቅፋኛለች።
ስንራመድ ሁለት ሳይሆን አንድ እንመስላለን እቅፍቅፍ ብለን ።
ቀና ብላ ስታየኝ ጥቁር ቸኮላት የመሰለው ውብ ፊቷ ፣ በረዶ የመሰሉት ነጫጭ ጥርሶቿ ፣ ጥቁር ዞማ ፀጉሯ ፣ ሰርጎድ ብላ የምትታየው ዲምፕሏ ፣ ትላልቅና የሚያማምሩ ዐይኖቿ ... አፍንጫዋ ላይ ያለችው ጌጥ ቀጥ ሊያደርጉኝ ሲሞክሩ እየሳቀች ጉንጬን ሳም ስታደርገኝ በቁሜ እፈዛለሁ፣ እደነዝዛለሁ!!
በዛፎች የተከበበችውንና ቀዝቃዛውን ከዚራን ለፍቅራችን ማድመቂያ አደረግናት።
አብዛኛው ሰው እዚያ ስፍራ የማዘውተሩን ሚስጥር የደረስኩበት ዘግይቼ ነው።
ማታ ማታ ጥንድ ጥንድ ሆነው በሚጓዙ ፍቅረኛሞች ትደምቃለች።
ትኩስ የፍቅር መናኸሪያ ትሆናለች። ከከንፈር ላይ የማር ጠብታን የሚልሱና የሚቀምሱ የሚመስሉ ተሳሳሚዎች፣ ድምፃቸውን ገደብ አልባ በሆነ ሳቅ የሞሉባት ሳቂታዎች በርክተው የሚታዩት ማታ ነው።
በዚህ መንገድ ነበር ብዙውን ጊዜያችንን ጥብቅ'ብቅ ብለን ብዙ ሳቅና ጨዋታ የሞላውን ወሬ እያወራን የምናዘግመው!
ከሩትዬ ጋር ድሬዳዋን ደመቅንባት ... ከግንፍሌ እስከ ቅዳሜ ገበያ ...ከኮንጎ ሜዳ እስከ ደቻቱ ሳባ ዳቦ ....ከሳሬምመጋላ ....ከፍል ውሃቀፊራ ያልተጓዝንበት የለም ።
አንድ ቀን ነምበር ዋን አከባቢ የሚገኘው ፋሲካ ሆቴል ቁጭ ብለን እያወራን ተቅበጠበጠች።
የጠጠጣችው ዋይን መሆኑ አልጠፋኝም።
ሞቅ ብሏታል በዚያ ላይ የለበሰችው ወይን መሳይ ቀለም ያለው ቀሚስ ጭኗን ገለጥ አድርጎ ያሳያል።
የልብሱ አሰራር ከወገቧ ቀጠን ብሎ ሽንጧን ይዞ ዳሌዋ አከባቢ የተወጠረ የልብስ መስቀያ ይመስል ሞላ ብሏል።
ጠይም ከንፈሯን በስሱ ጥቁር የከንፈር ቀለም ተቀብታዋለች።
ምሽቷ በዚያን ሳምንት ካሳለፍናቸው የፍቅርና የፍንደቃ ጊዜያት ምርጧ ምሽት ነበረች።
"....ሙቀቱ ከላይ የለበስኩትን የመኝታ ልብስ እንዳወልቅ አስገድዶኛል።
እንግዳ መሆኔ እንደፈለኩ እንድሆንና እንዳደርግ አልተመቸኝም።
በደብዛዛው የበራችው ዜሮ አምፖል ቤቱን ጭላንጭል ብርሃን እንዲበራ አድርጋዋለች።
ቤቱ ውስጥ የተኙት አብዛኞቹ እራቁታቸውን ናቸው።
ራቁቴን እገላበጣለሁ የበላሁት ለውዝ ከሙቀቱ ጋር ተደምሮ የሆነ ቀስቃሽ ሆነውብኝ ተወጥሬያለሁ።
ውሃ ሰማያዊ የተቀባው የግድግዳ ቀለም ላይ የተሰቀሉት የተለያዩ የቤት ውስጥ ጌጣጌጦች እይታን ይማርካሉ!!
ድሬዳዋ ከቀን ይልቅ ማታ ሞቃት ናት።
ሞቃት ብቻ ናት ከምል ትግላለች ብል ሳይቀል አይቀርም።
ቀን ላይ ጭር ትላለች በተለይ ከ8:00- 10:00 ሁሉም እረፍት ያደርጋል። መቃም የፈለገ በዛፎች ወደ ተከበበችው ከዚራ ጎራ ይልና ከዛፎቹ ስር ጎዝጉዞ ይቅማል፣ ይጫወታል።
ማታ እንደ ዲምላይት ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ በብርሃን ትጥበረበራለች።
ሩትዬ ሁልጊዜ እጆቿን ትከሻዬ ላይ ጣል ሳታደርግ አትንቀሳቀስም።
አንድ ቀን ቁርስ ልንበላ ከመንገድ ዳር ቁጭ ብለን
ፉል በሳልሳ አዘን እስኪወጣልን ዐይኔን በስስት እየተመለከተች ጉንጬን ሳም እያደረገች እኔ እየተሽኮረመምኩ እያለ አንዱ " ዋው ስታስቀኑ! " አለ
ፊቷ እንደ ሌሊት ጨረቃ ጥርት እንደ ፀሐይ ሙቀት ሲረጭ ተሰማኝ ።
እጆቻችንን አቆላልፈን ምግቡ ሲመጣ አንዳችን ሌላውን እየተጎራረስን መንገድ ዳር የተቀመጡት ሰዎች ሁሉ ይስመርላችሁ እያሉ ይመርቁናል።
ድሬዳዋ የመንገድ ላይ ምግብ መመገድ እንደ አንድ ባህል ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል።
ጥዋት ቀለል ያሉ ቁርሶች ...ፉል በድንች ... ፉል በእንቁላል፣ ፉል በሳልሳ ( የአከባቢው መጠሪያ ነው እኛ ጋር ስልስ በመባል ይታወቃል ቲማቲም ተቀምሞ ማለት ነው።) መሰል ምግቦች ተመራጭ ናቸው።
እራት ላይ እንዲሁ የተለያዩ ነገር ግን ድንች የሌለው ምግብ በጭራሽ አይኖርም።
ድንችን ጠዋትም ቀንም ማታም በሚመገቧቸው ምግቦች ስለማትጠፋ 3D ተብላ ትጠራለች።
ከሩትዬ ጋር ድሬዳዋን ክንፍ አውጥተን ቦረቅንባት አንድ ቀን የሆነ ቦታ ልውሰድህ አለችኝ።
እንግዳ መሆኔ ብዙ ቦታዎችን ለማየት ጉጉት አድሮብኝ እሺ ብዬ አብሬያት ሄድኩ!
ድሬደዋ ከተማን ለሁለት ሰንጥቆ የሚያልፈውን የጎርፍ መንገድ ወይም አሸዋ ሜዳ አቀናን ! ደስ ይላል በዚያው ስፍራ ያሉ ቤቶች ዙሪያቸውን በረጃጅም የኮንክሪት አጥር ታጥረዋል ለምን እንደሆነ አልጠፋኝም።
ከዚያ መልስ በድሬዳዋና ሐረር አከባቢ ከሚታወቁት ምግቦች ጣፋጮቹን እየዞርን ፈጀናቸው።
መላዋ ( በስንዴ ዱቂት አልያም በፉርኖ የሚሰራ ጣፋጭ ምግብ !
ሙሸበቅ፣ በቅላባ፣ ሀላዋ( ውስጡ ለውዝ ያለው ጣፋጭ ምግብ)
ፈጢራ (በማር የሚሰራ )
ባጊያ ይሄም በስኳርና በፉርኖ ዱቄት የሚዘጋጅ ...
ሚጣጢስ ብቻ ሁሏንሜ ጣፋጭ ምግብ የተባለ ሁሉ አልቀረንም ....እሱን ጨርሰን በኢትዮጵያ ብቸኛው የተማሪዎች ባንድ የተዘጋጀውን ሙዚቃ ታድመን ፣ ጨፍረን ... ጨረኔ ከጠረኗ ተደባልቆ ..ድክም ብለን መንገድ ላይ ስንሄድ መንገድ ላይ ሶስት ውሃ ሰማያዊ ቀለም ተቀብተው የተቀመጡ እንስራዎች አገኘን አስታውሳው እየሳቀች ይህ በእኛ አጠራር ጃህላ ይባላል እነዚህ የምታያቸው ደግሞ የተፈጥሮ ፍሪጆች ቀመባል ይታወቃሉ አለችኝ።
ከእንስራዎቹ አጠገብ ዕድሜ ጠገብ የዘንባባ ዛፎች አሉ ከውሃው ጎንጨት ስል ቅዝቃዜው ቶንሲሌን ሊቀሰቅሰው ትንሽ ቀረው።
በጉብኝታችን ወቅት ከዚራ አከባቢ የሚገኘውን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን .... የጃንሆይን ቤተ መንግሥት!!
ልዑል ራስ መኮንን በ 1885 ዓ.ም ቆርቁረው በ 1887 ዓ.ም ቤተመንግሥቱን ሠሩ። ሁለተኛም የኢትዮጵያ መንግስት አልጋወራሽና ባለ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ በነበረበት ጊዜ 1914 ዓ.ም ልዑል ራስ መኮንን የሠሩትን አሻሽለው እና አስፋፍተው ተሰራ።
በሶስተኛውም ጊዜ በ 1947 ዓ.ም ልዑል ራስ መኮንን ከመሠረቱበት ቦታ ላይ የመሠረት መልኩን ሳይለወጥ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ መስፍነ ሐረር ፕላኑን አሻሽሎ ባቀረበው አይነት ሁለተኛውን ፎቅ ተጨምሮበት እንዲሰራ ፈቅደው ይኸውም ሥራ 1947 ዓ.ም ተጀምሮ በ 1955 ዓ.ም ተጠናቀቀ።
ባሳለፍኳቸው ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በጣም ብዙ የተላመድኳቸው ቤተሰቦቿና አንዳንድ ጓደኞቿን መለየት እንደ ሞት ያህል ይሰማኝ ደመር።
ያንን አጉራሽ ፣ አልባሽ ፣ ሰው የሚጠግብ የማይመስለው ቤተሰቧን ጥሎ መሄድ አልቻልኩም ነገ ዛሬ እየተባልኩኝ ሁለት ቀናትን አሳልፌ በስተመጨረሻ እስከ ናዝሬት ድረስ የባቡር ቲኬት ቆረጥኩ !
እኔና ሩትዬ የምንገናኝ ቢሆንም ቤተሰቦቿንና አንዳንድ ሰዎችን ድጋሚ የማገኛቸው በፈጣሪ ፈቃድ ሴለሆነ ተላቀስን ስመው መርቀው ሸኙኝ።
ገና ባቡር ውስጥ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ነበር እያንዳንዱ ሁነት እንደመስታወት ጥርት ብሎ መታየት የጀመረው !
ጉዞውን አብዛኞቹ በእንቅልፍ ቢገፉትም እኔ ግን የሃይማኖት ግርማን " ከዚራ ነው ቤቴ እያልኩ በትኋንና በቁንጫ እንደ ተሰቃየሁ መዳረሻ ላይ ደረስኩ !
እግሬ መሬት ቢረግጥም መንፈሴ ግን እዛው ድሬ ሩትዬ ጋር ነው።
ትዝታዎቹ ክልልል ብለው ይመጡብኛል።
ጠዋት ማታና ቀን ላይ ልክ እንደ ድንቹ 3D ፍቅሯን የምትለግሰኝ!!
ምንም እንኳን እኔ ስፅፈው ባንዛዛውም ትክክለኛውን ስለድሬ መረጃ ስለሰጠኸኝ ደጀኔ ማሙዬ አመሰግናለሁ!!!
አብርሃም ኑናቶ
61 viewsአብርሃም, 15:52