2022-07-04 21:38:34
"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"
#ሰኔ ፳፰ (28) ቀን።
እንኳን ለእስክድርያ (ለግብጽ) አገር ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስተኛ ለሆነው ሃያ ስምንት ዓመት ሙሉ በስደትና በመከራ ላሳለፈ ለታላቁ አባት ለአባ ቴዎዶስዮስ ለዕረፍት መታሰቢያ በዓልና ለአባ ያዕቆብ እል-በረዲ ለመታሰቢያ በዓሉ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰብ፦ ከቅዱስ ባስልዮስና ከቢፋሞን፣ ከባሊዲስና ከኮቶሎስ፣ ከአርዳሚስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
#አባ_ቴዎዶስዮስ፦ ይህም አባት ለእስክንድርያ አገር ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስተኛ ነው። በዚህም ቅዱስ በስሙ በግብጽ ምድር ውስጥ ምእመናን ቴዎዶስዮሳውያን ተብለው ተጠርተውበታል። ይህም የሆነው እንዲህ ነው ሊቀ ጵጵስና ከተሾመ በኋላ ክፉዎች ሰዎች በእርሱ ላይ ተነሥተው በንጉሥ ምክር ከመንበረ ሢመቱ አሳደዱት በእርሱ ፈንታም አስቀድሞ በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዲያቆናት የነበረ ስሙ አቃቅያኖስ የሚባለውን አንድ ሰው ሾሙ እርሱም ለአባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ጵጵስና እንዲገባው ከፈረሙት ቁጥር ውስጥ ነበር።
ይህም አባት ወደ ግርማኖስ አገር ሒዶ ሦስት ወሮች ኖረ በዚያም ወራት በግብጽ አገር ንቡረ እድ አባ ሳዊሮስ ነበር እርሱም በአባቶቻችን ሐዋርያት እንዲሁም በአትናቴዎስና በዮሐንስ አፈወርቅ የደረሰባቸውን መከራ እያስታወሰ ያጽናናቸው ነበር። ከዚያም ተነሥቶ መሊግ ወደሚባል አገር ሔደ በዚያም ሁለት ዓመት ተቀመጠ።
የእስክንድርያ ከተማ ሰዎችም የጠባቂያቸው የቴዎዶስዮስ መመለስ ሺተው በእስክንድርያው መኰንን ላይ ተነሡበት መኰንኑም ወደ መንበረ ሢመቱ መለሰው አቃቅያኖስንም አባረሩት። ይህም ነገር በንጉሥ ዮስጣቲያኖስና አምላክን በምትወድ በንግሥት ታዖድራ ዘንድ ተሰማ ንግሥቲቱም አስቀድሞ የተሾመው በሹመት ወንበሩ ይቀመጥ ብላ ጻፈች።
ሃምሳ ስምንት ካህናትም ጉባኤ አደረጉ "አስቀድሞ የተሾመ አባ ቴዎዶስዮስ ነው" ሲሉም ጻፉ። ያን ጊዜም አቃቅያኖስ በሕዝብ ፊት ቁሞ "ክፋዎች ሰዎች ስለ አስገደዱኝ ይህን ሥራ ለመሥራት ሕግን ተላልፌአለሁ" አለ። ከዚህም በኋላ አቃቅዮስን ከውግዘቱ እንዲፈታው ነገር ግን ክህነትም ሆነ ሊቀ ዲቁና ለዘለዓለም እንዳይኖረው ሕዝቡ አባ ቴዎዶስዮስን ለመኑት። አቃቅያኖስ "አዎ እንዲሁ ይሁን" አለ ይህም አባት ከግዝቱ ፈታው።
ሃይማኖቱን ያጠፋ ንጉሡ ግን በከፋች ሃይማኖቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ ከእርሱ ጋራ የሚስማማ መስሎት በእስክንድርያ ወዳሉ መኳንንቶቹ እንዲህ ብሎ ጻፈ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎዶስዮስ በሃይማኖት ከእኛ ጋራ የሚስማማ ከሆነ ሹመት ይጨመርለታል። ለእስክንድር ከተማ ገዥ ይሆናል። ይህ ካልሆነ ከሹመቱ ይሻር።
ይህም አባት ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ ሰይጣን "በበረሀ ጌታችንን ብትሰግድልኝ የዓለም መንግሥታትንና ክብራቸውን ሁሉ እሰጥሃለሁ" አለው። ያን ጊዜም ይህ አባ ቴዎዶስዮስ ተነሥቶ ከእስክንድርያ ወጣ ወደ ላይኛው ግብጽም ሔደ በዚያም ሕዝቡን እያስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም እያጸናቸው ጥቂት ቀኖች ኖረ። ንጉሥም አባ ቴዎዶስዮስ ከእስክንድርያ ከተማ እንደ ወጣ በሰማ ጊዜ እየሸነገለው ወደ እርሱ መልእክት ላከ እንዲህም አለው እኔ ከአንተ ጋራ ልነጋገር ከአንተም ልባረክ እንድትመክረኝም እሻለሁ"።
ከዚህም በኋላ ወደ ቊስጥንጥንያ ከተማ ሔደ የጳጳሳት አለቆችና ሕዝቡ ሁሉ ሠራዊቱም ተቀበሉት ከፍተኛ ወንበርም ላይ አስቀመጡት። እርስ በርሳቸውም ስለ ሃይማኖት ተከራከሩ ንጉሡም አብዝቶ ሲሸነግለውና ሲአባብለው ሰነበተ ቅዱስ አባት ቴዎዶስዮስ ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጥቀስ ይረታው ነበር። ከእርሱም ጋራ ባልተስማማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ወደ ላይኛው ግብጽ አሳደደው። በእርሱም ፈንታ ጳውሎስ የሚባለውን ሰው ሾመው።
ጳውሎስም ወደ እስክንድርያ ከተማ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ አልተቀበሉትም ዓመት ሙሉም ኖረ በእጁም ማንም ቊርባንን አልተቀበለም። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ለመናፍቁ ጳውሎስ እስከሚታዘዙ ድረስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲዘጉ አዘዘ። ምእመናንም ከእስክንድርያ በመውጣት ወደ ቅዱስ ወንጌላዊ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ቆዝሞስና ድምያኖስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዱ ነበር ካህናቱም በዚያ እየቀደሱ ያቆርኳቸው ነበር የአገር ልጆችንም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቋቸው ነበር።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲከፍቱላቸው አዘዘ አባ ቴዎዶስዮስም ሰምቶ ንጉሡ እንዳያስታቸው ፈራ ማጽናኛ ቃልን የተመላች መልእክትም ጽፎ በቀናች ሃይማኖት እያበረታቸው ወደ ምእመናን ላካት እንዲህም አላቸው "በዚያ ከሀዲ ጳውሎስ እንዳትታዘዙ ተጠበቁ"።
ይህም አባት ሃያ ስምንት ዓመት በስደት ኖረ። መላው የሹመቱ ዘመን ሠላሳ ሁለት ነበር። ይኸውም በእስክንድርያ አራት ዓመት በስደትም ሃያ ስምንት ዓመት ነው።
ይህም አባት ብዙ ድርሳናትን ደርሷል ምእመናንም በያዕቆብ ዘመን ያዕቆባውያን እንደ ተባሉ በስሙ ቴዎዶስዮሳውያን እየተባሉ ሲጠሩ ኖሩ። መልካም ጉዞውንም ፈጽሞ ሰኔ 28 ቀን በሰላም ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 25 ስንክሳር።
+ + +
"ሰላም ለቴዎዶስዮስ ዘተወክፈ ክበዶ። ለሕማም ወለተሰዶ። በቃለ ሃይማኖት እንዘ ይሜህር ውሉዶ። በእንተ ዘገብረ ለክርስቶስ ፈቃዶ። ዐስበ ሐዋርያት ሎቱ ምንተኒ ኢውሕዶ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 28።
=>#ሰኔ 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ ቴዎዶስዮስ ሊቀ ዻዻሳት
2.ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳይ
3.ቅዱስ ባስልዮስ
4.ቅዱስ ባሊዲስ
=>#ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
=>+"+ ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብጹዓን ናቸው:: መንግስተ ሰማያት የእነርሱ ናትና:: ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብጹዓን ናችሁ:: ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ:: ሐሴትም አድርጉ:: ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳደዋቸዋልና:: +"+ (ማቴ. 5:10)
+ + +
#የዕለቱ_ምስባክ፦ "ጸላእኩ ማኅበረ እኩያን። ወኢይነብር ምስለ ጽልሕዋን። ወአሐፅብ በንጹሕ እየውየ"። መዝ 25፥5-6።
#የሚነበቡት_መልዕክታት ቲቶ 1፥7-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥1-7 እና የሐዋ 7፥1-9።
#የሚነበበው_ወንጌል ማቴ 10፥23-32።
#የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ባስልዮስ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችን ይሁንልን።
51 views18:38