Get Mystery Box with random crypto!

'በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን' #ሰኔ ፳፱ | ጥምር ግቢ ጉባዔ (በደ/መ/ቅ/ሚካኤል ካ/የፈለገ ዮርዳኖስ ሰንበት ት/ቤት)

"በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"

#ሰኔ ፳፱ (29) ቀን።

እንኳን ለንጉሥ ዳዊት ልጅ ለኢትዮጵያዊው ንጉሥ ለጻድቁ ለቅዱስ ቴዎድሮስ ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል፣ ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ ለከበረ ለቅዱስ ዐምደ ሚካኤል ለሥጋው ፍልሰት በዓል፣ ለንጹሕ ጻድቅ ለሆነ ለሮሜ ንጉሥ ለቅዱስ ማርቆስ ለዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል፣ ከቆና ገዳም ለሆኑ ለሰባት መስተጋድላን ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዐረፍታቸው በዓል መታሰቢያና ለቅዱሳን ለአባ ሖር፣ ለአባ ብሶይና ለእናታቸው ይድራ ከአንጾኪያ ንጉሥ ሠራዊት ውስጥ ለሆነ ለአባ ሖርሳም ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከክብር ባለቤት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታች ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከተወለደበት ከልደቱ (ከበዓለ ወልድ) ከወራዊ ከመታሰቢያ በዓል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
+ + +
#የንጉሥ_ዳዊት_ልጅ_የኢትዮጵያ_ንጉሥ_ቅዱስ_ቴዎድሮስ፦ ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ በዕውቀትና በተግሣጽ አደገ የቤተ ክርስቲያንንም መጻሕፍት የተማረ ደግሞም ቀስት ማፈናጠርንና ፈረስ ግልቢያን ተማረ ኃይል ያለውም ብርቱ ሰው ሆነ።

ከታናሽነቱም ጀምሮ በእግዚአብሔር ፍቅር ታሠረ ገንዘቡን ለድኆችና ለችግረኞች ይመጸውት ነበር። አብያተ ክርስቲያንንም እጅ መንሻ ከመያዝ ጋራ ይጎበኝ ነበረ በጸሎቱና በጾምም ይጋደል ነበር። ካንዲት ሴት በቀር አላገባም በማንም ላይ ዐመጻና ግፍ ከቶ አልሠራም።

ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ በአሰበ ጊዜ አባ ማርቆስን አማከረው እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ያውቅ ነበርና "ክፍልህ አይደለም" አለው።

ከዚህም በኋላ ባረፈ ጊዜ በክረምት ወራት በድኑን ሲወስዱ ሞልቶ የነበረው ወንዝ ወዲያና ወዲህ ተከፍሎ ተሻገሩ በቀበሩበትም ቦታ ሕይወትነት ያለው ውኃ መነጨ እስከ ዛሬም አለ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ንጉሥ በቅዱስ ቴዎድሮስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
በዚችም ቀን የከበረ ዐምደ ሚካኤል የሥጋው ፍልሰት ሆነ መጀመሪያ በንጉሥ እስክንድር ዘመነ መንግሥት ወደ አባቶቹ መቃብር ዳግመኛም በንጉሥ ልብነ ድንግል ዘመን በአረፈ በአርባ ዓመቱ ፈለሰ አባቶቹ ነገሥታት ወደተቀበሩበት ወደ አትሮንሰ ማርያም አፍልሰው እንዲወስዱት ንጉሡ አዝዞ ነበርና። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
"ሰላም ለከ ለብሔረ አግዓዚ ንጉሣ። ቴዎድሮስ ዕጓለ አንበሳ። ተዝካረ በዓልከ ዮም በጥብሐ አባግዕ ወእንሰሳ። አኮ ዘገብረት ባሕቲታ እምከ ጽዮን ሞገሳ። ደመናትኒ አንጠብጠቡ ዓሣ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የሰኔ 29።

+ + +
#የሮሜ_ንጉሥ_ቅዱስ_ማርቆስ፦ ይህም ቅዱስ ንጹሕ ጻድቅ ነበር። በድንግልናው አምስት ዓመት ነገሠ ሕዝቡንም እግዚአብሔርን በመፍራትና በቅን ፍርድ ጠበቀ። እርሱንም ከመውደዳቸው የተነሣ ሚስቱን እንዲአገባ መኳንንቱ አስገደዱት እርሱ ግን በሌሊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቁሞ ጸለየ "እመቤቴ ሆይ ላንቺና ለማይሻር ንጉሥ ልጅሽ እገዛ ዘንድ ወደ ምሔድበት ምሪኝ" አላት። እርሷም "ወደ ቶርማቅ ተራራ ሒድ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይኑር" አለችው።

ከዚህም በኋላ በሌሊት ወጥቶ ሔደ ወደ ባሕር ወደብም በደረሰ ጊዜ ያለ መርከብ ተሻግሮ ወደ ቶርማቅ ተራራ ደረሰ ያም ቦታ ደረቅ ነበረ ከአጋንት ጋራም እየተጋደለ በውስጡ ስልሳ ዓመት ኖረ። ሰኔ 29 ቀን በዐረፈ ጊዜም መላእክት በክብር ቀበሩት። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ንጉሥ በቅዱስ ማርቆስ በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
#በቆና_ገዳም_የነበሩ_ሰባት_መስተጋድላን_ሰማዕታት፦ የእሊህም ስማቸው አባ አብሲዳ፣ አባ ኮቶሎስ፣ አባ አርድማ፣ አባ ሙሴ፣ አባ እሴይ፣ አባ ኒኮላስና አባ ብሶይ ናቸው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጾ እንዲህ ብሎ "አዘዛቸው ክብር ይግባውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ግለጡ"።

ያን ጊዜም ወደ መኰንኑ ሊሔዱ ተነሡ መርከብንም አገኙ በመርከቧም ውስጥ አምስቱን መስተጋድላን አገኙአቸውና ከእነርሱ ጋር ተስማሙ ወደ መኰንኑም ደርሰው በፊቱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ታመኑ። መኰንኑም ከእርሳቸው አንዱን ስለ ሀገራቸው ጠየቀው እርሱም ቆና ከሚባል አገር እንደሆኑ አስረዳው መኰንኑም ያሥሩዋቸው ዘንድ አዘዘ።

ከዚህም በኋላ ደግሞ ከእሥር ቤት አውጥተው ጽኑ ሥቃይን ያሠቃዩአቸው ዘንድ ደግሞም በአንገቶቻቸው ከባድ ደንጊያዎችን አንጠልጥለው እንዲአሥሩዋቸው አዘዘ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በውህኒ ቤት ውስጥ ተገለጠላቸው አጽናናቸውም ቃል ኪዳንም ገባላቸው።

ከዚህ በኋላ ንጉሥ ወደ እስክንድርያ ከተማ ላካቸው በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃዩአቸው። ከዚህም በኋላ ዝፍትና ድኝ በተመሉ ከሁለት የብረት ምጣዶች ውስጥ ጨመሩአቸው ነበልባሉም ሃያ ክንድ ከፍ ከፍ እስሚል ድረስ ከታች እሳትን አነደዱባቸው ከምጣዶችም ውስጥ አውጥተው በእሳት ምድጃ ውስጥ ጨመሩአቸው ጌታችንም ዳግመኛ ተገልጾ ያለ ምንም ጉዳት አዳናቸው።

ከዚህም በኋላ ወደ መኰንኑ ቀርበው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው መቶ ሠላሳ ሰዎች በጌታችን አምነው በሰማዕትነት ሞቱ። ከዚህም በኋላ አስጨናቂ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው ወደ እነርሱም አጵሎን የሚሉትን ጣዖት በወንበር እንደ ተቀመጠ አምጥቶ እንዲሰግዱለት አዘዛቸው እነርሱም ግን በእግሮቻቸው ረገጡትና ከመንበሩ ወድቆ ተሰበረ።

መኰንኑም አይቶ እጅግ ተቆጣ እግሮቻቸውንም እንዲቆርጡ አዘዘ የቅዱስ ቀሲስ አብሲዳንን ግን ራሱን በሰይፍ ቆረጡትና ምስክርነቱን ፈጸመ እንዲሁ ደግሞ እሊያ አምስቱንም ራሶቻቸውን ቆረጡ ቅዱስ ኮቶሎስን ግን በእሳት አቃጠሉት ሁሉም የሰማዕትነት አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀዳጁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰባቱ መስተጋድል ሰማዕታት በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

+ + +
#ቅዱሳን_አባ_ሖር፣ #አባ_ብሶይና #እናታቸው_ይድራ #ከአንጾኪያ_ንጉሥ_ሠራዊት_ውስጥ_የሆነ_አባ_ሖርሳ፦ እሊህም ወደ እስክንድርያ በደረሱ ጊዜ በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በጌታች ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ መኰንኑም አባ ብሶይን ይዘው ቀኝ እጁንም አሥረው በከተማዎች ሁሉ በበሬዎች እንዲጐትቱት አዘዘ።

ከዚህም በኋላ የተዘረጉ ብረቶችን በእሳት አግለው በሥጋው ውስጥ አደረጉ የግራ እጁንም ቆረጡ እርሳስም አቅልጠው በአፉ ጨመሩ ጊንጦችና እባቦች ወደ ተከማቹበት ውስጥ ጣሉት እነርሱ ግን ከቶ አልቀረቡትም።

ከዚህም በኋላ በብረት በትሮች ይደበድቡት ጀመር እርሱም "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ" ብሎ ጮኸ ጌታችንም አጸናው እንደቀድሞውም ያለ ምንም ጉዳት ጤነኛ አድርጎ አስነሣው።