በጎጃም የተደረገው ሕግ ማስከበር ውጤታማ መሆኑን የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ አረጋገጡ ። የጎጃም ኮማንድፖስት የመጋቢት ወር የስራ አፈፃፀም ግምገማ በፍኖተ ሰላም ከተማ ባካሔደበት ዕለት ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እንደተናገሩት ፣ በወሩ ውስጥ የተከናወኑት የኦፕሬሽን ፣ የማዳበሪያ ስርጭት ፣ የጸጥታ ሀይል የማደራጀት እና ሌሎች ተግባራት ለውጥ አስገኝተዋል ። በመጋቢት ወር በጎጃም በሚገኙ 66 ወረዳዎች የተሰማራው ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል 594 ጽንፈኞችን በመደምሰስ ፣ 232 አቁስሏል በርካቶች ደግሞ እጃቸውን በሰላም ሰጥተዋል ። በማዳበሪያ ስርጭት ፣ በምዕራብ ጎጃም 105 ሺህ ኩንታል ፣ በምስራቅ ጎጃም 223 ሺህ 761 ኩንታል ፣ በሰሜን ጎጃም 281 ሺህ 971 ኩንታል ፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርም 157 ሺህ 252 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉ በግምገማው ተገልጿል ። የፀጥታ ሀይል በማደራጀት በኩልም በወሩ ውስጥ 11 ሺህ 151 ሰላም አሰከባሪ ፣ ሚሊሺያ እና የፖሊስ ሀይል በአራቱም የጎጃም ዞኖች ተሰልፎ የሕግ ማስከበሩ አካል እንዲሆን ተደርጓል ። በዚሁ ወርሃዊ ግምገማ ላይ የተሳተፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶክተር) እንዳሉት ፣ ኮማንድፖስቱ ያከናወናቸው የሰላም ተልዕኮዎች ለግብርናውም ሆነ ለሌሎች ዘርፎች ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ነበራቸው ። በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው ፣ የዕቅድ አፈፃፀሙ ውጤት የሕዝባችንን የሰላም ጥያቄ እየመለሰ የመጣ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ። ኮማንድፖስቱ በቀጣይ ወረዳዎችን ማጠናከር ፣ የሚደረጉ ስምሪቶች ደምሳሽ እንዲሆኑ ፣ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት እንዲቀላጠፍ ፣ ፖሊስ እና ሚሊሺያ የማደራጀቱ ስራ የበለጠ እንዲጠናከር አቅጣጫ አስቀምጧል ። በዚሁ የግምገማ መድረክ ላይ የሁሉም ዞኖች ኮማንድፖስት ከፍተኛ አመራሮች እና የከተማ ከንቲባዎች ተገኝተዋል ። 23.4K views07:48