2022-07-02 13:29:31
ሁሉን ወሬ ላውራ አትበል የደበቁህን ምስጢር አታውጣጣ የሰማኽውን ወሬና የተገለጠልህን ምስጢር ምን መፍትሔ ሰጠኸውና? ሰዎች ባላወቀ ዝም ሲሉህ እንዳላዋቂ አትያቸው አውቀው እንዳላወቁ እሚኖሩ ብዙ ናቸውና!
ያየህውን ሥራ ሁሉ እሰራለሁ የሰማኸውን ትምህርት ሁሉ እማራለሁ አትበል። ይህ የተሰወረው የቅንዓት ፀባይ ነውና። ሁሉን ልያዝ ማለትም ዝንጉ አድረጎ እንዳያስቀርህ ሁሉም ውስጥ ልኑር አትበል።
የሚበልጥህ ልኩራብህ እንዳይልህ ያነሰህ ልድረስብህ ብሎ እንዳያጠፋህ የሀብትህን ልክ እንዳታወራ በገዛ አፍህ ባንዱ ትከብራለህ ባንዱ ትቀላለህና።
ቂም አፍን የሚያመር ልብን የሚያነቅዝ ተግባርን የሚያልፈሰፍስ ነውና ለበደለህ ሰው ቅያሜህን ግለጥለት ቂመኝነት በክፉ መሸነፍ እንጂ ጀግንነት አይምሰልህ።
ከህሊናህና ከመንፈሳዊ አማካሪህ ሳትመክር ምንም ነገር አትወስን አጥርተህ ሳትሰማ ቃል አትግባ።
የራስህን ማንነት ከመረዳት ይልቅ የሌሎችን ማንነት በመጠየቅና በመመርመር ዕድሜህን አታባክን።
የራስህን የታሪክ አሻራ ትተህ እለፍ በማያገባህ አትግባ!
መልካም ቃል ከስጦታ ይበልጣልና መልካም ቃል ተናገር ማንኛውም ስጦታ ከልመና ወንበር አያስነሣም። የተስፋ ቃል ግን እንደሚያስነሣ አውቀህ ለሰዎች የተስፋ ቃል ስጣቸው እንጂ ውድቀታቸው አትሁን!
ትምህርት ለዕውቀት ያዘጋጃል እንጂ ዕውቀትን አይጨርስም። ዕውቀትህን የምትይዝበትን ሥነሥርዓት ግን ያሳይሃል። ተከታይ ለማበጀት ግልጽ መሆንና ታማኝነት ግድ ይልሃል።
አንተው እውነትን ጠልተሃት ዘመኑ እውነትን ጠልቷል አትበል። ዘመን እኔና አንተ ነን በራሱ ክፉና ደግ የሆነ ዘመን የለም። መቋጫውን ላላወከው ነገር ውሳኔ አትወስን!
መልካም ምክር ብትሰማ ሕይወት ቀላል ይሆንልሃል። ትክክለኛም ውሳኔ ከመልካም ምክር ነውና..!!
57 views@medi, 10:29