Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! #አቡነ_ሙሴ_ጸሊም | ✞ የማርያም ✞ ፳፩ እና ✞ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ልጆች ፲፫ ✞

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
#አቡነ_ሙሴ_ጸሊም
መሴ ማለት መዋሴ፣ ዋስ፣ መሆን፣ ከችግር ማዳን፣ ከግዞት፣ከእስራት ነጻ ማውጣት ማለት ነው፡፡ አቡነ ሙሴ ጸሊም ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ተጋድሎአቸውን የፈጸሙት ግን በግብፅ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ እንደ አብርሃም በየዋህ ልቦና ሆነው ሥነ-ፍጥረትን በመመርመር እግዚአብሔር አምላካቸውን ያገኙ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ ወላጆቻቸው ፀሐይ ያመልኩ ስለነበር ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃጢአት በሠሩ ቁጥር ‹‹ተው አምላካችን ፀሐይ ይጣላሃል›› ይሏቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን ሽፍታና ዘራፊ ሆኑ፡፡ እየዘረፉ ብዙ ይመገቡ ስለነበረር ከትልቅነታቸውና ከኃይለኝነታቸው የተነሳ ‹‹በግ ፈጅ›› እየተባሉም ይጠሩ ነበር፡፡
ብዙ ወርቅ ከባለ ሀብቶች ሰብስባ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን ልትሰጥ ትሄድ የነበረችን አንዲት ክርስቲያን ሴት ልጅ ሙሴና ግብረ-አበሮቻቸው ለወርቁ ሲሉ እርሷን ማርከው ወሰዷት፡፡ ማታ ላይ ስለ ውበቷ ሲያወሩ እርሷ ግን ‹‹ስምህ ማን ነው?›› ስትላቸው ‹‹ ሙሴ ነኝ›› አሏት፤ ‹‹ይሄ ስምስ እጅግ የተባረከ ነው…›› ብላ ስለ ሊቀ ነቢያት ሙሴና ስለ ክርስቶስ አስረዳቻቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ወላጆቻቸው ስለ ፀሐይ አምላክነት ሲነገሯቸው ያደረጉትን ነገር መመርመር ጀመሩ፡፡ ‹‹ፀሐይ አምላክ ከሆነ እስከ ዛሬ ድረሰ ሽፍታና ዘራፊ ሆኜ ሰው ስገድልና ይህን ኹሉ ኃጢአት ስሠራ እንዴት ፀሐይ ሳታቃጥለኝ ቀረች? ደግሞ ፀሐይ ጠዋት ወጥታ ማታ ትጠልቃለች ይህችስ እንዴት አስገኝ ትሆናለች በራሷ አስገኚ አላት እንጂ…›› በማለት ፀሐይን ፣ ጨረቃን፣እሳትን ነፋስን በየተራ አምላክ መሆናችውንና አለመሆናቸውን ከመረመሩ ከፈተኑ በኋላ ‹‹የሁሉ አስገኚ አምላክ ተናገረኝ›› ብለው ሲጸልዩ ከሰማይ ድምጽ መጥቶላቸው ወደ ገዳም ሄደው ከአባቶች ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩ ተነገራቸውና ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደው መምህር ኤስድሮስ ሁሉንም ነገር አስተምረው ለማዕረገ ምንኩስና አበቋቸው፡፡
መጀመሪያ ወደ ገዳሙ ሲሄዱ ይዘርፉበትና ይቀሙበት የነበረውን ስለታም መሳሪያ እንደያዙ ስለነበር ያዩአቸው መነኰሳት ኹሉ ‹‹ሊገድለን መጣ›› አሉ፡፡ ከዚህም በኋላ ለመነኰሳቱ ሁሉ የሚላላኩ ሆኑ፡፡ ትንሹም ትልቁም ሙሴ ይሄን አድርግልኝ ይሏቸዋል እርሳቸውም ይታዘዛሉ፡፡ እራሳቸውን በትህትና ዝቅ በማድረግ በተጋድሎ እየኖሩ ታምራትን ማድረግ ጀመሩ፤ በጸሎታቸውም ዝናብ ያዘንቡ ነበር፡፡ ለቅድስና ደረጃ ከበቁም በኋላ 40 ዓመት ሙሉ ከሰው ሳይገናኙ ብቻቸውን ዘግተው ከኖሩ በኋላ ለ500 መነኰሳት አበምኔት ሆነው ተሾሙ፡፡ ቀን ወንጌል ሲያስተምሩ ይውሉና ሌሊት እየተነሱ ከበረሃ መነኰሳት ውኃ ይቀዱላቸው ነበር፡፡ አገልግሎታቸው የታይታ እንዳይሆንባቸው አረጋውያን መነኰሳት መተኛታቸውን ካረጋገጡ በኋላ የግብፅ በረሃን አቋርጠው ከሩቅ ስፍራ ውኃ እየቀዱ መነኰሳቱ ሳያዩአቸው በየደጃፋቸው ላይ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡ ብዙ መነኰሳትም ወደ አቡነ ሙሴ እየመጡ የሕይወትን ትምህርት ይማሩ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ሰው አባ ሙሴን ‹‹አንድን አገልጋይ ባጠፋው ጥፋት የተነሳ ጌታው መታው፤ አገልጋዩ ምን ማለት አለበት?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ አባ ሙሴም ‹‹አገልጋዩ ብጹዕ ከሆነ ፣ አጥፍቻለሁና ይቅር በለኝ ማለት አለበት›› አሉት፡፡ ‹‹ ሌላ አይጠበቅበትምን?›› ሲል ደግሞ ጠየቃቸው፡፡ ‹‹አይጠበቅበትም ፣ ለጊዜው ለጥፋቱ ኃላፊነቱን ወስዶ አጥፍቻለሁ ካለ ጌታው ይቅር ይለዋል፤ የዚህ ሁሉ አላማው በባልንጀራ ላይ አለመፍረድ ነው፡፡ በእውነቱ ጌታችን የግብፅን በኩራት ሁሉ ሲመታ ሰው ያልመታበት አንድም ቤት አልነበረም›› ብለው መለሱለት፡፡ ያም ሰው ‹‹ምን ማለት ነው?›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹ሁላችንም የየራሳችን ጥረቶች ካየን የባልንጀራችንን ለማየት ዕድል አንሰጥም፤ በራሱ ቤት ሰው ለመፈለግ የጎረቤት ለቅሶ አይሄድም፡፡ ለባልንጀራ መሞት ማለት ለራሱ ጥፋት ትኩረት በመስጠት፣ የሌላውን ጥፋት ከቁምነገር አለመቁጠር ነው፡፡ ማንንም አትጉዳ በማንም ላይ ክፉ አታስብ ክፉ የሚሠራውን ሰው አትናቀው በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትተማመን፣ በባልንጀራው ላይ ክፉ በሚሠራ ሰው ላይ አትደሰት፣ ለባልንጀራ መዋቲ መሆን ማለት ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ አትማረር ነገር ግን ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል በል፡፡ ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፣ በሐሜቱም አትደሰት፣ ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፡፡ አትፍረድ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡፡ በማንም ላይ የጥላቻ ሃሳብ አይኑርህ፣ ጥላቻ ልብህን እንዲያሸንፈውም አትፍቀድለት፡፡ ባልጀራውን የሚጠላውን አትጥላው፣ ሰላም ማግኘት ማለት ይህ ነው….›› ብለው መከሩት፡፡
በዕድሜአቸው መጨረሻ አካባቢ ቡራኬ ለመቀበል ከመነኰሳትና ደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ወደ አባ መቃርስ ሄዱ፡፡ አባ መቃርስም ‹‹ልጆቼ ከእናንተ መካከል በሰማዕትነት የሚሞት አለ›› ብለው ትንቢት ሲናገሩ ሙሴ ጸሊምም ‹‹አባቴ ያ ሰው እኔ ነኝ ሰይፍ የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ›› የሚል ቃል ተጽፎአል፤ (ማቴ 26፥52) ይህን ጊዜ በጉጉት ስጠብቀው ነበር አሏቸው፡፡ እንደተባለውም የበርበር ሰዎች ገዳሙን ዘርፈው መነኰሳቱን ሊገድሉ ሲመጡ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ‹‹ሸሽተን እናምልጥ›› አሏቸው፤ አቡነ ሙሴ ግን ‹‹በጎልማሳነቴ ጊዜ ደም አፍስሻለሁና አሁን የኔም ደም ሊፈስ ይገባል›› በማለት እራሳቸውን ለሰይፍ አዘጋጅተው ጠበቋቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሰኔ 24 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ ተቆርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ የአባታችን የሙሴ ጸሊም ቅዱስ ሥጋቸው በገዳመ አስቄጥስ በክብር ይገኛል፡፡ በረከታቸው ይደርብን አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ምንጭ፦ ስንክሳር ዘሰኔ