Get Mystery Box with random crypto!

ሰኔ 22 - '#ቅዱስ_ዻውሎስ_የዋህ' °°° በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ግብጽ ውስጥ | ✞ የማርያም ✞ ፳፩ እና ✞ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ልጆች ፲፫ ✞

ሰኔ 22 - "#ቅዱስ_ዻውሎስ_የዋህ"

°°°
በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ግብጽ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ቅዱሱ ስሙ ዻውሎስ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚጠራው "የዋህ ዻውሊ" በሚል ነው:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ የዋህ ዻውሊ ከሕጻንነቱ ጀምሮ መጻሕፍትን የተማረ: ግን ደግሞ ትዕቢት: ቁጣና ቂምን የማያውቅ ገራገር ሰው ነበር::

°°°
ዕድሜው ለአካለ መጠን ሲደርስ ቤተሰቦቹ ሚስት አግባ አሉት:: እርሱ ባያስብበትም ወገኖቹን ላለማሳዘን አገባ:: እንዳለመታደል ሆኖ ግን ያገባት ሴት በጣም ቆንጆ በዚያም ላይ ክፉ ነበረች:: የዋህ ዻውሊ ክፋቷን ሁሉ ታግሶ ለበርካታ ዓመታት አብሮ ኖረ:: ልጆችንም አፈሩ::

°°°
አሁንም ግን እርሷ ከክፋቷ ልትታገስ አልቻለችም:: ይባስ ብላ ዻውሊ በሌለበት ከሌሎች ወንዶች ጋር ትዘሙት ጀመረች:: የዋሁ ሰው ይህንኑ ያውቃል፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሥራ ዝም ብሎ በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: እሱ ያርሳል: ይቆፍራል: ነዳያንን ያበላል: እንግዳ ይቀበላል እንጂ ክፋትን ለማሰብ ጊዜ አልነበረውም::

°°°
አንድ ቀን ግን ለሥራ ወደ በርሃ ወጥቶ አንድ ግሩም ዜና ሰማ:: "አባ እንጦንስ ምንኩስና የሚባል ሕይወተ መላእክትን ጀምሯል: ደቀ መዛሙርትንም ይቀበላል" አሉት:: ነገር ግን ሚስትና ልጆች አሉትና ምን ያደርጋል? የዋህ ዻውሊ ሙሉ ቀን ሲሠራ ውሎ ወደ ቤቱ ሲመለስ የጠበቀው ሌላ ነው:: ሚስቱ በራሱ መኝታ ላይ ከአገልጋይ እረኛው ጋር ራቁታቸውን አገኛቸው::

°°°
ልብ በሉልኝ በትክሻው ሞፈርና ምሳር: መጥረቢያም ይዟል:: እርሱ ግን ክፉን አላሰበም:: ጥሩ ልብስ አንሥቶ ሁለቱንም አለበሳቸው:: እንዲህም አላቸው:- "ከዚህ በኋላ እኔ አልመለስም:: ሃብት ንብረቴን ውረሱ: በደስታም ኑሩ:: የልጆቼን ነገር ግን አደራ" ብሏቸው ተነሣ::

°°°
በእጁ ምንም አልያዘም:: በትከሻው ያለችውን ብጣሽ ጨርቅ ይዞ ወደ በርሀ ተጓዘ:: አባ እንጦንስም ተቀብለው አስተምረው አመነኮሱት:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ራስን ዝቅ በማድረግ: በመታዘዝ አገለገለ:: ጾም: ጸሎትና ስግደቱንማ ማን ቆጥሮት::

°°°
እያለ እያለ ከብቅዐት ማዕርግ ደረሰ:: ምዕመናንም ሆነ መነኮሳት ሊጠይቁት ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይመለከት ነበርና ስለ እነሱ ሲያለቅስ ቅንድቡ
ተላጠ:: ሰውነቱም አለቀ::

°°°
አንድ ቀን ጋኔን የያዘውን ሰው ፈውስ ብለው አመጡለት:: እርሱ ግን በአጋንንት ላይ ሥልጣን እያለው በትሕትና ተጠግቶ ጋኔኑን "አባ እንጦንስን ከምጠራብህ ቀስ ብለህ ውጣ" አለው:: ጋኔኑ ግን የፈራው መስሎት በትዕቢት "እንጦንስ ማነው?"አለው::

°°°
ያን ጊዜ የዋህ ዻውሊ እንደ እሳት ከጋለ ድንጋይ ላይ ቁሞ "ሕያው እግዚአብሔር ምስክሬ ነው:: ይህ ጋኔን ካልወጣ አልወርድም" አለ:: ወዲያው በዘንዶ አምሳል ከሴትዮዋ ወጥቶ እየጮኸ ወደ ቀይ ባሕር ገባ:: ቅዱስ ዻውሊ የዋሕም እንዲህ በቅድስና ተመላልሶ በዚህች ቀን በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::
ምንጭ፦ ገድለ ቅዱሳን

°°°
"አምላከ ቅዱሳን ልዑል እግዚአብሔር ከቅዱሳን አባቶቻችን ከጸናች ገድላቸው፣ ከበዛች ትዕግስታቸው፣ ከፍጹም ጸሎታቸውና በረከታቸው ያሳትፈን፤ ፍጻሜያችንን ያሳምርልን።"
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!