Get Mystery Box with random crypto!

ግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች:: | ✞ የማርያም ✞ ፳፩ እና ✞ ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ልጆች ፲፫ ✞

ግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች::

እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት::

ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ::

ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መባዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበር::

እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኀዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር::

ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ::

ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው::

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት:: ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገኑት::

የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርግ ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች::

ከዚህም በኋላ ይቺን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ማለት ነው::

ደግሞም ሀብትና ሥጦታ ማለት ነው:: በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናት:: ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነት ያገኘንባት::

እንግዲህ እዚህ ጋር ልብ ይሏል::

በዚህ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ የኛ ልጅነት የኛ የመዳንችንን መንገድ እግዚአብሔር እንዴት እንዳከናወነልን እንረዳለን::

እግዚአብሔር ሰውን ሲያድን ማዳኑን የፈጸመው እጅግ በጣም ልዩ በሆነ ሁኔታ ነው::

ይህም ገናናነቱን ከእኛ ታናሽነት ጋር አዋሕዶ፤ ከሃሊነቱን ከእኛ ነፃነት ጋር አስማምቶ በመሆኑ ነው::

ይህ ማለት ምን ማለት ነው?

ሊያድነን ሲነሣ እንዲሁ በማንኛውም መንገድ ቢያድነን ታላቅ ቸርነትና ደግነት ሆኖ ሳለ እርሱ ግን ከዚያም በላይ በሆነ መንገድ እኛን አሳትፎ ፈቃዳችንን ተቀበሎ አስፈቅዶ አስወድዶ ያዳነን::

እርሱ ሁሉን ማድረግ ስለሚችል ብቻ ያለ እኛ ፈቃድ ሱታፌ እንዲሁ አፍአዊ በሆነ ሁኔታ እና ያለ ፈቃዳቸው አላዳነንም::

ባሕርያችንን ሲዋሐድም ያለ እኛው ፈቃድና ሱታፌ አላደረገውም:: የሚጠቅመንን የመዳናችንን ነገር ሲፈጽም እኛን አስወድዶና አሳትፎ ነው::

አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል እኛን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ሲወርድ መከራ ተቀብሎ እኛን የሚያድንበትን መሣሪያ የወሰደው ከእኛው መዳኑ ከሚያስፈልገንና ከሚደረግልን ከሰዎች ነበር::

ይህ እንዲሆን ደግሞ ሰዎችን የሚወክልና እኛን ሁሉ ወክሎ የሚሳተፍ አንድ ሰው ያስፈልግ ነበር::

በዚህም ያ የሚያስፈልግ አንድ ሰው በዛሬዋ ቀን የተወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት:: በእወነት ምስጋና ይድረሳትና።

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲ የነቢያት ትንቢታቸው ከተፈጻሚነት የደረሰው:: ታዲያ የዛሬውን በዓል ስናከብርና ተድላ ደስታ ስናደርግ ከመንፈሳዊነት ሳንወጣ ልንጠነቀቅ ይገባል::

ይህን በዓል ስናከብርም ሌሊት በቤተ ክርስቲያን በማኅሌት÷ በዝማሬ÷ ጠዋት በኪዳንና በቅዳሴ÷ ታምሯን በመስማት÷ ወንግል በመማር ነው:: ክርስቲያኖች ከዚህ የወጣ ባዓል የላቸውም::

ብዙዎች የእኛን መንፈሳዊ በዓል ይዘው የራሳቸውንና የቤታቸውን ጣጣ ይዘውና አስታከው መንፈሳዊ በዓላ ላይ ለጥፈው ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም ከመንፈሳዊነታችን ጋርም የሚፃረር ነገር ሲፈጽሙ ይታያል ይህ አግባብ አይደለም::

የበግና የፍየል ከለር እየመረጡ÷ ቄጣና ፈንዲሻ እየረጩ÷ የቡና አተላ እየገለበጡ የሚከበር መንፈሳዊ በዓል የለም:: አስፀያፊም የተወገዘም ግብር ነው።

እስኪ አንድ በዓለም ያለ ሰው ልደቱን ሲያከብር ወይ ሲደግስ የበግ ከለር መርጦ የሚያርድ ማን አለ? ወይ ቡና እያንቃረረ ቂጣና ፈንዲሻ በየጥጋ ጥጉ የሚጥል ማን አለ? ታዲያ እንደዚህ ያለን ኮተታ ኮተት ከየት የመጣ ነው::

የኛ አይደለም እንዲህ ያለ ነገር እንዲህ የሚያደርጉ ካሉ ፈጥነው ንሰሐ ሊገቡና ከክርስቲያኖች ማኅበር ሊገቡ ይገባል::

የእመቤታችንን የልደቷን በዓል ግን የምናከብረው በዝማሬ÷ በማኅሌት÷ በኪዳን÷ በቅዳሴ ጊዜ ሥጋወ ደሙ እየተቀበልን÷ ወንጌልን እየተማርን÷ የተራበ እያበላንና የታረዘ እያለበስን እየዘመርን ነው::

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋር ለዘላለሙ ይኑር አሜን። 
@muzemur
@muzemur

“አንተ ግን አቤቱ፥ መጠጊያዬ ነህ፥ ክብሬንና ራሴንም ከፍ ከፍ የምታደርገው አንተ ነህ።” መዝ ፫፥፫
join join join

  @muzemur
  @muzemur