Get Mystery Box with random crypto!

አዕምሮን ወዳጅ ማድረግ ከሁሉ የሚልቅ ወዳጅነት ነው! (እ.ብ.ይ.) ዓለማዊው ወይም ውጫዊው ወዳጅ | ዶ/ር ምህረት ደበበ

አዕምሮን ወዳጅ ማድረግ ከሁሉ የሚልቅ ወዳጅነት ነው!
(እ.ብ.ይ.)

ዓለማዊው ወይም ውጫዊው ወዳጅነት እና ጓደኝነት ግላዊ ነው፡፡ ወዳጅነት ሁለት ወይም ሶስት ቢበዛ እስከአራት ድረስ የሚደርሱ ሠዎች እርስበርሳቸው የሚያቋቁሙት ፈቃዳዊ ውል ነው፡፡ ጓደኝነት ክፉንም ደጉንም፣ ሃሳቡንም ጭንቀቱንም የሚካፈሉበት መድረክ ነው፡፡

በዚህ ወዳጅነት ውስጥ ሚስጥር መጠበቅ ዋነኛው መስፈርት ነው፡፡ ‹‹አትንገር ብዬ ብነግረው፤ አትንገር ብሎ ነገረው›› የሚለው ብሂል ወዳጅነትን አፈር የሚያስግጥ፤ የሞቀ ጓደኝነት ላይ ውሃ የሚቸልስ ክህደት ነው፡፡ ወዳጅነት ሚስጥርን መጠበቅ ካልቻለ እውነተኛ ጓደኝነት አይሆንም፡፡ በዚህ ዘመን የምናየው አብዛኛው ወዳጅነት ግን እውነተኛ ጓደኝነትን የማይገልፅ ተግባቦት ብቻ ሆኗል፡፡ አንድ ሠው ወዳጅነቱን ለማስፋት ሲል ብዙ ሠዎችን ጓደኛ ያደርጋል፡፡ ለሠው ከብዙ ሠዎች ጋር መግባባቱ ክፋት ባይኖረውም የልብን የሚያዋዩት ሠው ግን አንድ አልያም ሁለት ወዳጅ ግድ ይለዋል፡፡ እውነተኛ ወዳጅ የውስጥን የሚተነፍሱለት፣ ጭንቀትንና ጥበትን ተካፍሎ አዲስ የተስፋ መንገድ የሚያሳይ፤ እንዲሁም አብሮ አዝኖ አብሮ የሚደሠት የልብ ጓደኛ ነው፡፡

አርስጣጢሊስ ‹‹ለሁሉም ጓደኛ የሆነ ለማንም ጓደኛ መሆን አይችልም፡፡›› ይለናል፡፡ እውነት አለው! ከብዙ ሠዎች ጋር በስራ፣ በጉርብትና፣ በዝምድና፣ በተለያዩ ጉዳዮች መግባባትና ማሕበራዊ ሕይወትን መካፈል ደስ የሚያሠኝ ቢሆንም ወዳጅነት ግን በጥቂት ሠዎች ብቻ የሚመሠረት ማሕበራዊ ውል ነው፡፡

የሠው ወዳጅ መልካም ቢሆንም የአዕምሮ ወዳጅ ግን ከሁሉ ይልቃል፡፡ የገዛ አዕምሮን ወዳጅ ማድረግ፣ ከህሊና ጋር ጓደኛ መሆን፣ ከልቦናችን ጋር አለመጣላት ከወዳጆች ሁሉ የበለጠ ወዳጅነት ነው፡፡ አዕምሮን መቅረፅ፣ በአዕምሮ መንገድ መመላለስ፣ ሕሊናን ማርቀቅ፣ ናላን ማጫወት፣ ልቦናን ማትጋት ከሠው ልጅ የሚጠበቅ ትልቅ ተጋድሎ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተጋዳላይ የምንሆነው ከውጫዊው ሕይወታችን ጋር ነው፡፡

እርግጥ ነው ለመኖር መስራት ይጠበቅብናል፤ ሆዳችንን ለመሙላት መውጣት መውረድ ግድ ይለናል፡፡ ሆኖም ግን አዕምሮን ማስደሰት፣ ሕሊናን ማጥገብ፣ ልቦናን ማርካት እንዳለብንም መዘንጋት የለብንም፡፡ ነፍስያችን የሚደሠተው፣ መንፈሳችን ሐሴት የሚያደርገው ከአዕምሯችን ጋር ተግባብተን እውነተኛ ወዳጅ ስንሆን ብቻ ነው፡፡ የስጋ ፍላጎትን መሙላት ጊዜያዊ ደስታ ሲሠጥ የአዕምሮን ፈቃድ መሙላት ግን የማይነጥፍ ደስታን ያጎናፅፋል፡፡ በሕይወታችን ታላቁን ፍስሃ የምናገኘው ሕሊናችንን አርቅቀን ልባዊ መሻታችንን ስንሞላ ነው፡፡ ስጋ ደንድኖ ሕሊና ቢቀጥን ደስታ አይገኝም፡፡ ቦርጫችን ገፍቶ አዕምሯችን ቢራብ እውነተኛ እርካታ እውን አይሆንም፡፡ ምግባራችን፣ ተግባራችን፣ የሕይወት ምልልሳችን ትርጉም ያለው የሚሆነው ከውስጣችን ጋር ተግባብተን፣ ሕሊናችንን ስለን፣ ከአዕምሯችን ጋር ወዳጅ ስንሆን ብቻ ነው፡፡

ብዙ ሠው ከራሱ ጋር ተጣልቷል፡፡ ግብ ግቡ ቀላል አይደለም፡፡ ገላጋይ የማይፈታው ነው፡፡ ገላጋዩም፣ አስታራቂው ሽማግሌም ሌላ ሳይሆን ራሱና ራሱ ብቻ ነው፡፡ ከራሱ ጋር እርቅ የማይፈፅምና ከሕሊናው ጋር ወዳጅ የማይሆን መጨረሻው አያምርም፡፡ ከአዕምሮው ጋር ፀብ የገባ ሠው ራሱንና ጨርቁን ይጥላል፡፡ በየመንገዱ የምናያቸው የአዕምሮ ሕመምተኞች ከአዕምሯቸው ጋር ጦርነት ገጥመው በሽንፈት እጅ የሠጡ ናቸው፡፡ የአዕምሮውን ሠላም ማስጠበቅ የማይችል ሠው መጨረሻው ከራሱ ጋር መጋጨት ነው፡፡ የዚህም ዋና ምክንያቱ ከአዕምሮው ጋር ወዳጅነት መፍጠር ባለመቻሉ ነው፡፡ ሕሊናውን ከመስማት ይልቅ ዓይቶ ባላየ፣ ሠምቶ ባልሠማ በመሆኑ ነው፡፡ አብዛኛው ሠው ከሌሎች ሠዎች ጋር መወዳጀትን እንጂ ከራሱ ጋር መግባባትን ይዘነጋዋል፡፡ ከራሱ ያልተግባባ ከሌላው ጋር እንዴት ይግባባል??? ከሌላው ጋር ወዳጅ ለመሆን ከራስ ጋር መወዳጀት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ከውጫዊ ዓለም ጋር ተግባብቶ ለመኖር ከውስጣችን ዓለም ጋር መዋሃድ ግድ ይለናል፡፡

ወዳጄ ሆይ…. አዕምሮን ወዳጅ ማድረግ ከሁሉ የሚልቅ ወዳጅነት ነው! ወዳጅ በማብዛት እውነተኛ ወዳጅነት አይገኝም፡፡ ከራስ ጋር መወዳጀት ግን ከሁሉ የሚበልጥ ዓላማ ያለው ተግባር ነው፡፡ ከራሱ ጋር ወዳጅ የሆነ ከሌላ ሠው ጋር ወዳጅ ሆኖ ፀንቶ ለመቆየት አይከብደውም፡፡ ከራሳቸው ጋር ሳይወዳጁ ወዳጅ የሚያንጋጉ ሠዎች የወዳጃቸውን ሚስጥርና ገበና አደባባይ ያወጣሉ፡፡ ወዳጅነት ልክ፣ ገደብ፣ ወሰንና ድንበር አለውና የጓደኝነት ሚዛኑን በማስተዋል እንያዝ የዛሬው መልዕክት ነው፡፡ ከራስ ጋር መግባባት፣ ከራስ ጋር እርቅ መፈፀም የመግባባትና የእርቆች ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ከአዕምሮ ጋር መወዳጀት የወዳጅነት ቁንጮ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ ቀድመህ ከራስህ ጋር ታረቅ፤ ቀጥለህ አዕምሮህን ወዳጅ አድርግ! በመጨረሻም ከዓለሙ ጋር ተስማምተህ መኖር የሚያስችልህ ዕውቀትና ልምድን ታገኛለህ! አዲዮስ!

‹‹ከሕሊናህ ጋር ተጨዋወት!
አዕምሮህን ተወዳጀው!
ጠላት አርገኸው!
እንዳይፈጅህ!
እንዳትፈጀው፡፡››

ቸር ወዳጅነት!

ቸር ጊዜ!
@mihret_debebe
@mihret_debebe
@mihret_debebe