Get Mystery Box with random crypto!

++ምናለ ብታስተምረኝ++ በክብር በሞገስ በመወደስ ፈንታ መቀመጥ እንድችል ከመዋረድ ተርታ ስድብን | መንፈሳዊ ግጥሞች ዘ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ

++ምናለ ብታስተምረኝ++
በክብር በሞገስ በመወደስ ፈንታ
መቀመጥ እንድችል ከመዋረድ ተርታ
ስድብን እየሰማሁ ያለ አንዳች ሁካታ
ለመቆም እንድችል ልቤ ሳይረታ
ምናል ብታስተምረኝ ብታስችለኝ ጌታ!?
ለእኔም አስተምረኝ ባላጠፉት ጥፋት
በጸጋ መቀበል የአይሁድን ትፋት
እንዴት እንደሚቻል ሳያጉረመርሙ
ንገረኝ ጌታዬ ይረዳኝ ትርጉሙ!
የመናቅን ጥበብ የውርደትን ዘዴ
እባክህ አስረዳኝ አስተምረኝ አንዴ
ብዔል ዜቡል ተብለህ ያልተበሳጨኸው
የኃጢአተኞች ወዳጅ መባል ያልጠላኸው
ጋኔን ይዞታልን የሰማህ በጸጋ
ለእኔም አስተምረኝ በቂም አልወጋ!
አልወጋ እባክህ በመራርነት ጦር
በቁጣ ጥላቻ ነፍሴ አትሰበር
እንዴት ነበር ያኔ የይሁዳን እግር

ዝቅ ብለህ ያጠብኸው ስታውቅ ሁሉን ነገር?
ለእኔም አስተምረኝ ብዙ ሳልናገር!
በችንካር ተጣብቀህ ከመስቀሉ ጋራ
የደምህ ነጠብጣብ ገና ሳያባራ
አያውቁትምና የሚያደርጉትን
ይቅርታን የለመንህ ላጠጡህ ሐሞትን
ምናል ብታስተምረኝ እንዲህ ዓይነት ሕይወትን?
አሁን ምን ቸገረህ ብትሰጠኝ ለአንድ አፍታ
የትሕትናን ቀሚስ የትዕግሥትን ኩታ
እያየህም አይደል ነፍሴ እንዲህ ተራቁታ?
የመሰደብን ዘውድ የመናቅን ካባ
ምናለ ብትኖር ይ’ች ልቤ ደርባ!?
ትዕቢት ለተሞላው ለአትንኩኝ ባይ ልቤ
ለክብሩ ለሚኖር ለኮርማው ሃሳቤ
ምናለ ብትቀባው የትሕትናን ሽቶ
እንደዚህ ከሚኖር ሸትቶ ተበላሽቶ!?
ኸረ እኔ አልቻልኩም አቅቶኛል በጣም
ስድብን መቀበል ሐሜትን ማጣጣም

ስተርከው እንጂ ስኖረው አቃተኝ
ይህን መራር ኑሮ አንተው ይዘህ ጋተኝ!
እንኳን እንደ አንተ ዝም ልል ሲረግጡኝ
ቁጣዬ ነደደ ስለገላመጡኝ
ያንን ሁሉ ታሪክ ያን ሁሉ ጥቅስ ረሳሁ
በቂምና በቀል በጥላቻ ከሳሁ
እንደ አራስ ነብር ለክብሬ ተነሣሁ!
ዲ/ን ሄኖክ ሃይሌ /