Get Mystery Box with random crypto!

የኡስታዝ ኢብኑ ሙነወር 'ሸይሁል ኢስላም፤ ሙሐመድ ኢብኑ-ተይሚያህ' የሚለው መፅሀፍ #ክፍል_6 በአ | Bilal Media & Communication

የኡስታዝ ኢብኑ ሙነወር "ሸይሁል ኢስላም፤ ሙሐመድ ኢብኑ-ተይሚያህ" የሚለው መፅሀፍ #ክፍል_6 በአላህ ፍቃድ እነሆ

#የኖሩበት_ዘመን_ባጭሩ

የተንጣለለው ፅኑው የኺላፋ ስርአት ዛሬ በትላንቱ መልክ የለም፡፡ የተለያዩ አካባቢዎች የራሳቸው ገዢ አላቸው፡፡ ግብፅና ሻም በመምሉካውያን መዳፍ ስር ናቸው፡፡ በቋፍ የነበረው የዐባሳውያን ኺላፋ ባግዳድ ላይ በተታሮች ፈርሷል፡፡ መምሉካውያን የዐባስ ዘሮችን እያስመጡ ስለሚሾሙ የፈረሰው የዐባሳውያን ኺላፋ ለይስሙላ ካይሮ ላይ ቀጥሏል፡፡ እውነተኛው ስልጣን የነበረው ግን በመምሉካውያኑ ሱልጣኖች እጅ ነው፡፡ በራሳቸው በመምሉካውያኑ መካከል ደግሞ የተጧጧፈ የስልጣን ሽኩቻ አለ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ!

የአውሮጳውያኑ የመስቀል ጦርነት እያባራ ነው፡፡ ከዛሬዋ ሞንጎሊያ አካባቢ የተነሱት ተታሮች ግን በሙስሊሙ ላይ በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እልቂት ፈፅመዋል፡፡ ሰራዊታቸው እየሰለመ፣ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ጭፍጨፋቸው እየቀነሰ ቢመጣም አረመኔያዊ ጥቃታቸው ገና አልተገታም፡፡

መምሉካውያኑ ከሞላ ጎደል ለዲን ክብር አላቸው፡፡ ግና በጊዜው ወደተንሰራፋው የሱፍያ መዝሀብ ያዘነበሉ ነበሩ፡፡ በውጭ ከሃዲያን እየተጠቃ ያለው ሙስሊሙ አለም ከውስጥም በቢድዐ እግር ከወርች ተጠፍሯል፡፡ ዘርፈ ብዙ የሺርክ አይነቶች እዚህም እዚያም እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ በአፈንጋጭ ሺዐዎች የተጀመረው የቀብር አምልኮ ዱላውን በተቀበሉት ሱፍዮች ቀጥሏል፡፡ ኢብኑ ዐረቢ፣ ኢብኑ ፋሪድ፣ በደዊ፣ ቲልሚሳኒ፣ ሻዚሊ እና መሰል የሱፍያ አውራዎች ግብአተ መሬታቸው የተፈፀመው ኢብኑ ተይሚያ በተወለዱበት በሰባተኛ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ፈተናቸው ግን ከህልፈታቸው በኋላ ይበልጥ ጨምሯል፡፡ ከራማና ሰይጣናዊ የጥንቆላ ስራ ብዙው ሰው ዘንድ ተቀላቅሏል፡፡

የመዝሀብ ጎጠኝነት ነግሶ በየከተማው ለአራቱም መዝሀብ ቃዲ የሚመደብበት ዘመን ነው፡፡ በአንድ መስጂድ ውስጥ ለአንድ ሶላት አራት ጀመዐ የሚቋቋምበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ሆኖም ግን መንግስታዊ ልዩ ድጋፍ ከሚደረግለት የሻፍዕይ መዝሀብ ጀምሮ የማሊኪያ እና የሐነፍያ መዝሀብ ተከታዮችም ዘንድ የሰለፎች ዐቂዳ ተረስቷል፡፡ በጥቂት አካባቢዎች በስሱ ከሚገኘው የአህሉል ሐዲሥ አስተምህሮት ውጭ የአሻዒራ ዐቂዳ ከጫፍ እስከጫፍ ተንሰራፍቷል፡፡ ይህንን የዒልመል ከላም ዐቂዳ መፃረር ህይወትን ሊያስከፍል ይችላል፡፡

ራፊዳ ሺዐዎች መነቃቃታቸው ጨምሮ ሙስሊሞችን ከሚፈጁ ወራሪዎች ጋር እየተባበሩ አደጋቸው ከመቼውም በላይ ጨምሮ ነበር፡፡ በሙስሊሙ ግዛት ውስጥ የሚገኙት ክርስቲያኖች በአንድ በኩል ከውጭ ወራሪ ጋር የሚያብሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ለአመታት የሚዘልቁ ከውስጥ የሚፈጠሩ ሁከቶችም ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል እንደ ኢብኑ ደቂቀል ዒድ፣ አልሓፊዝ ሸምሰዲን አዝዘሀቢ፣ ኢብኑ ቀይም አልጀወዚያ፣ ዒማድ ኢብኑ ከሢር፣ ኢብኑ ዐብዲል ሃዲ እና ሌሎችም ታላላቅ ዐሊሞች የነበሩበት ዘመን ነው፡፡ አንባቢ ስለ ኢብኑ ተይሚያ ዘመን ጥቅል ምስል እንዲይዝ በማለም ነው በወፍ በረር ስለዚህ ርእስ የቃኘሁት፡፡

``ኢንሻአላህ ይቀጥላል``
t.me/linkbi7