Get Mystery Box with random crypto!

ታላቁ ሀዲስ ዘጋቢ ኢማሙ አል ቡኻሪ ሙሉ ስማቸው ማን ነው ? መልሱ B) ሙሀመድ ቢን ኢስማዒል | 🍂 ረውደቱል ኢስላም የቁርአን እና የተርቢያ ማዕከል 🌿

ታላቁ ሀዲስ ዘጋቢ ኢማሙ አል ቡኻሪ ሙሉ ስማቸው ማን ነው ?

መልሱ B) ሙሀመድ ቢን ኢስማዒል ቢን ኢብራሂም አል -ሙጊራ አል ቡኻሪ ።

ኢማም ቡኻሪ ማናቸዉ?

ኢማሙ ቡኻሪ የተወለዱት በ 13 ሸዋል ፥ 194 ዓ.ሂ . ነበር። በቡኻራ ወረዳ በኹራሳን ግዛት (ምዕራብ ቱርኪስታን ) ሙሉ ስማቸው ሙሐመድ ኢብን ኢስማኢል ኢብን አል -ሙጊራ አል ቡኻሪ ነው ።

አባታቸው የሞተው ገና ልጅ ሳሉ ነው ። በእናታቸው ቅርብ ክትትል ነበር ያደጉት የሐዲስ ትምህርታቸውን የጀመሩት በአስር አመታቸው ነው። ከእናታቸውና ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በመሆን ወደ መካ በአስራ ስድስት ዓመታቸው ተጓዙ ። ኢማም ቡኻሪ መካና ኡለማዎቿን እጅግ በጣም በመውደዳቸው እናታቸውንና ወንድማቸውን በመሰናበት በቅድስቷ ከተማ ለሁለት አመታት ተቀመጡ ። ከዚያም ወደ መዲና በመሄድ ለአራት ዓመታት ሐዲስ በመቅሰም ኖሩ ።ከዚያም ወደ በስራ ፥ኩፍ ፥ባግዳድ ግብፅና ሶሪያ በመዘዋወር ከተለያዩ ሙሁራን ጋር ለመማርና ለመተዋወቅ በቅተዋል። ባግዳድ ለበርካታ ጊዜ ጎብኝተዋል ከእውቅ ሙሁራን መካከል ኢማም አህመድ ኢብን ሐንበልን አግኝተዋል ።

ኢማም ቡኻሪ እጅግ በጣም ታማኝና ቅን ሰው የነበሩ በመሆናቸው ልዑላኖችን ፣መሳፍንቶችንና ንጉሶችን ላለመገናኘትና ላለመወዳጀት ብርቱ ጥረት ያደርጉ ነበር ። እነርሱን ለማስደሰት ሲሉ አንዳች ነገር መናገር የሚሹ አልነበሩም -ቡኻሪ።

ኢማም ቡኻሪ ሐዲስ ለመሰብሰብ ያደረጉትን ብርቱ ጥረት በተመለከተ በርካታ ገጠመኞች ተወስተዋል ። ከታላቁ ነብዩ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) አንደበት የፈለቁ ትምህርቶችን በማሰባሰብ ያረገጡት ቦታ ፥ ያላወያዩት ዓሊም እጅግ ጥቂት ነበር ። ታላቁ ኢማም ቡኻሪ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አቻ የማይገኝለት የማስታወስ ችሎታ የነበራቸው ሊቅ መሆናቸውን በተግባር ያስመሰከሩ የኢስላም ባለ ውለታ "ዓሊም"ናቸው ። 300,000 ሐዲስ ሰብስበዋል ። ከዚህ ውስጥ 200,000 ያህሉን በአዕምሮአቸው ሸምድደዋል። ኢማም ቡኻሪ የተወለዱበት ዘመን የሐዲስ ትምህርትን በማዛነፍ ፍትህ የሚጎድላቸውን መሪዎች ለማስደሰት ወይም የኢስላምን ዲን ለማግሸብና ለማጭበርበር ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት ነበር ።

የኢስላም ምሁራን የኢማም ቡኻሪን የሀዲስ ስብስብ፦ "ከአላህ መፅሀፍ(ቁርአን) በመቀጠል እጅግ በጣም አስተማማኙ መፅሀፍ በኢማም ቡኻሪ የተፃፈዉ "ሶሂህ አል-ቡኻሪይ" ነዉ" በማለት ገልፀዋል።

ኢማም ቡኻሪ "ሶሂህ አል-ቡኻሪ"ን ከማዘጋጀታቸው በፊት በሕልማቸው ያዩት ለጥረታቸው ልዩ እገዛ ማድረጉም ይነገራል ። " ነብዩ ሙሐመድ (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ፊት ለፊት ቆመውና በእጃቸው ማራገቢያ ቢጤ ይዘው ከታላቁ ነብይ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ፊት ላይ ዝንብ እንዳያርፍ ይከላከላሉ ።" ኢማም ቡኻሪ ይህን ሕልም በዘርፍ ዕውቀት ላላቸው ሰዎች ይገልጻሉ በነብዩ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) ስም የሚነገሩ ግን ከሳቸው አንደበት ያልፈለቁ ጥቅሶችን የማጥፋት ሚና ገልጹላቸው።

በመሆኑም ኢማም ቡኻሪ የፈጠራ ሐዲሶችን ከእውነተኛና ትክክለኛ ሐዲሶች የማበጠሩን ሥራ ተያያዙት ። ምንም እንኳ ማንኛውም ታሪክ ከሚዘገብበት መስፈርት አኳያ ኢማሙ የሰበሰቧቸው ሐዲሶች ውስጥ ውድቅ የሚደረጉበት ምክንያት ባይኖርም የኢማሙ ቡኻሪ የሐዲስ አሰባሰብ መስፈርት (ሸርጥ) ጥብቅ በሆኑ 7275 (ሰባት ሽ ሁለት መቶ ሰባ አምስት) የሚደርሱ ሐዲሶችን ብቻ ነው በ "ሶሒሕ ቡኻሪ"እንዲካተቱ ያደረጉት ። ከነኝህ ሐዲሶች መካከል የተደጋገሙትን ስንቀንስ 2230 ብቻ ሐዲሶችን እናገኛለን ። እዚህ ላይ አንባቢያን ልብ እንዲልልን የምንሻው ሐዲስ የሚቆጠረው በ "መትን" (ፍሬ የቃሉ) ሳይሆን በሰነዱ መሆኑን ነው። በመሆኑም አንድ ሐዲስ እስከ አራት መቶ ሠነድ ( የተዘገበበት መስመር ) ሊኖረው መቻሉን ልናስታውስ እንሻለን ።

ታላቁ የሐዲስ ሊቅ አንድን ሐዲስ በስብስባቸው ውስጥ ከመጻፋቸው በፊት ውዱእ የደርጋሉ ። ሁለት ረከዓ ይሰግዳሉ ። ጌታቸውንም ይለምናሉ ። በርካታ እውቅ ሙስሊም ዓሊሞች "ሶሕሒህ ቡኻሪ " ን መርምረዋል ግን አንድም እንከን ሊያገኙበት አልቻሉም። ለዚህም ነው በአንድ ድምፅ ከቁርአን በመቀጠል እጅግ በጣም ትክክለኛው መጽሐፍ "ሶሒሕ ቡኻሪ "ነው በማለት የገለጹት ።

ኢማም ቡኻሪ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ256 ዓ.ሂጅራ ነው ። በሰመር ቀንድ አቅራቢያ የምትገኝ ኸርታንቅ በተባለች መንደር መካነ መቃብራቸው ይገኛል ።

አላህ ይዘንላቸው ።

ዋናውን የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ
https://t.me/LAILAHA_ILELLAH_ISLAMIC
https://t.me/LAILAHA_ILELLAH_ISLAMIC