Get Mystery Box with random crypto!

ክፉ ምክር #ዕለተ #ረቡዕ እንበለ ደዌ ወህማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሃነ ያብ | የአህዛብና የመናፍቃን ጥያቄዎችና መልሶቻቸው!!

ክፉ ምክር

#ዕለተ #ረቡዕ

እንበለ ደዌ ወህማም እንበለ ፃማ ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሃነ ያብጽህክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ በፍስሃ ወበሰላም አሜን።

አይሁድ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሞት ፍርድ ለመፍረድ የመጨረሻውን ምክር ያደረጉት ረቡዕ እንደ ሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል። ይሁን እንጅ ከዚያም በፊት በተለያዩ ጊዜያት በእርሱ ላይ ምን እንደሚያደርጉ ሲማከሩ ነበር።

በህዝቡ ፊት ያደርገው የነበረው መልካም ነገር ምክንያት አሳጥቷቸው እንጅ ሊይዙት ሲፈልጉ ቆይተዋል። የአይሁድ ክፉ ምክርና ጥላቻ ከቅንዓት የመጣ እንደሆነ እስከ ሀገረ ገዥው ጲላጦስ ድረስ የታወቀ ነበር።በዚህም ምክንያት ለሞት አሳልፎ ላለመስጠት ብዙ ሞክሯል። ይሁን እንጅ የእነሱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል እያወቀ አሳልፎ ሰጥቷቸዋል። ትልቁ በደል እንኳን ለሞት የሚያበቃ ለክስ የሚሆን መረጃ እንደሌላቸው እያወቀ ሁከት ስላበዙ እራሱን ነጻ ለማድረግ እጁን ታጥቦ ጌታን ግን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።


እሥራኤላውያን በዘመኑ በሮም ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ቢሆንም ነገር ግን የኦሪትን ህግ ምክንያት በማድረግ እንደ ህጋቸው ይፈርዱ ነበር። ለዚያ ነው ጲላጦስ መርምሮ ምንም ወንጀል ስላላገኘበት እንደ ህጋችሁ ፍረዱበት ብሎ የሰጣቸው። እስራኤል ዘሥጋ ከቀድሞ ጀምሮ ያላቸውን ታሪክ ስንመለከት ወንድማቸው ዮሴፍን በቅንአት ተነሳስተው ሊገድሉት ተማክረው ነበር።


ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ጠብቆት ከእነሱ አንዱ ሮቤል የተባለው ትልቁ ወንድማቸው ከምንገድለው እንሽጠው የሚል ሃሳብ በማቅረቡ ለግብጻውያን ነጋዴዎች ሸጠውታል። ለመግደል ምክንያታቸው ዮሴፍ ቅንና የዋህ ሰው በመሆኑ እግዚአብሔር ወደፊት የሚሆነውን በህልም አሳይቶት ነበር። አባቱም የዋህነቱንና ቅንነቱን አይቶ መክሮት ነበር። ወንድሞቹ በምድረ በዳ እንስሶችን ሲጠብቁ ሳሉ የሚበሉትና የሚጠጡት ይዞ በብዙ ድካም ወደ እነሱ ሲቀርብ ያለ ርህራሄ ከጉድጓድ ውስጥ ነበር የጨመሩት ለአባታቸውም አውሬ በላው ብለው በደም የተለወሰ ልብሱን አምጥተው ሰጥተውታል። "እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ። አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ። አሁንም ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን። ዘፍ 37፥18"


ዮሴፍ ገና በልጅነቱ ወደማያውቀው ሀገር በመሸጡ የሚወደውን አባቱን እንዲሁም ወገኖቹን ለመፈለግ አልቻለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜም ከቅኖች ጋር ነውና ከብዙ ችግር ጠብቆት የንጉሥ ታማኝ አገልጋይና በኋላም ባለሟል ለመሆን ችሏል። ወንድሞቹም በሀገራቸው ረሀብ ስለጸና ወደ ምድረ ግብጽ እህል ፍለጋ ሄደዋል። እነሱ ባያውቁትም እሱ ግን አወቃቸው። ያለፈውን በደላቸውን ይቅር ብሎ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አድርጎላቸዋል። ከዮሴፍ ሞት በኋላም የዮሴፍን መልካምነት የማያውቅ ፈርዖን በግብጽ በመነሳቱ መከራቸው እጅግ በመብዛቱ ምክንያት ሁልጊዜም የአባቶቻቸውን ቃል ኪዳን የማይረሳው አምላክ ሙሴን አስነስቶ ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል።


አስቀድሞ ለአብርሃም በገባው ቃልኪዳን መሰረትም ከነዓን ወደተባለችው ምድር ገብተዋል። ይሁን እንጅ በመንገድ እያገለገሉ ይመሩዋቸው የነበሩትን ሙሴና አሮንን ሊገድሏቸው የተነሱበት ጊዜም ነበር። "፤ ማኅበሩ ሁሉ ግን በድንጋይ ይወግሩአቸው ዘንድ ተማከሩ" (ኦሪት ዘኍልቍ 14: 10)


ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "፤ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። " (ኢሳ 53: 4) ብሎ እንደተናገረው በጌታ ላይ የደረሰውን መከራና ስቃይ ስናስብ አይሁድ ባይሆኑ ማን ሊፈጽመው ይችላል? ለምን ወደ እነሱ መጣ? ስንልም አስቀድሞ ያወቃቸው በመሆኑ እራሱን አሳልፎ ለእነሱ ሰጠ ብንል አይፈረድብንም።
ጌታ አምላክነቱን ገልጦ ልዩ ልዩ ተአምራት ማድረግ ከጀመረ አንስቶ አይሁድ ጤናማ መንፈስ አልነበራቸውም። በተለይ ዘመኑ ምድረ እሥራኤል በቅኝ ግዛት የነበረችበትና ህዝቡም በካህናቱና በመሪዎቹ ተስፋ የቆረጠበት ወቅት በመሆኑ ብዙዎች ተመልካች አጥተው በየስፍራው ሰቆቃ ላይ ነበሩ።


በተለይ ድሆችና ህሙማን አስታዋሽ አጥተው በከፋ ችግር ውስጥ የወደቁበት ዘመን ነበር። ቅኝ ገዢዎቻቸው የራሳቸው ጥቅም እንዳይነካ ይጠብቃሉ እንጅ በህዝቡ ላይ ስለሚደርሰው መከራ አይገዳቸውም ነበር። በዚህም ምክንያት አይሁድ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው ህዝቡን ያወናብዱት ነበር። ጌታ ይህን ሁሉ አይቶ ከክፉ ስራችሁ ተመለሱ፣ ህዝቡን አትበድሉ፣ እናንተ የማታደርጉትን በህዝቡ ላይ አትጫኑ፣ ለድሆች ራሩላቸው፣ ሰንበትን መልካም በመስራት አክብሩ እያለ ይገስጻቸው ነበር። እነሱ ግን እንዲህ ይሉ ነበር። "፤ ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። " (ማቴ 21: 23) እንዲረዱትም በምሳሌ እያደረገ ይነግራቸው ነበር ። ትምህርቱን ቢረዱትም " የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው። " ማቴ 21፥45


ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ ላይ "፤ እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። " (ማቴ 5: 17) እያለ ይናገር ነበር ነገር ግን አይሁድ በቅንአት አይናቸው ታውሮ ሰለነበር የሚላቸውን አይሰሙም ነበር። ህዝቡ እሱን ከተክተለ ክብራችን ይቀርብናል በማለት ተጨንቀዋልና በእለተ ረቡዕ የመጨረሻውን ምክር አድርገው ከሐዋርያት መካከል ይሁዳን በገንዘብ አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከተዋዋሉ በኋላ በ30 ብር የምስመው እሱ ነው ያዙት ብሎ አሲዞታል። ምክራቸው ፍጻሜ በማግኘቱ በጌታ ላይ እየተሳለቁ መከራ አጽንተው በመስቀል ላይ ሰቅለውታል።
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት "፤ አንድ ሆነው በአንተ ላይ ተማከሩ፤ በአንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ፤ "(መዝ 83: 5) ብሎ እንደተናገረው ከመስቀል ላይ አውጥተው እስኪሰቅሉት ድረስ እህል ላይቀምሱ ቃል ተገባብተው ተለያይተዋል።

ክፉ ሰዎች ከመከሩት ክፉ ምክር አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይጠብቀ

እንበለ ደዌ ወህማም እንበለ ፃር ወድካም አመ ከመ ዮም ያብጽሃነ ያብጽህክሙ ለብርሃነ ትንሳኤሁ በፍስሃ ወበሰላም አሜን።

@kidestaresema
@kidestaresema
@kidestaresema