Get Mystery Box with random crypto!

በሬን ላልከፈትኩለት ድንግል ሆይ አሳስቢ ቅድስት ሆይ ለምኝልኝ | ኬልቅያስ

በሬን ላልከፈትኩለት ድንግል ሆይ አሳስቢ
ቅድስት ሆይ ለምኝልኝ

ድንግል ሆይ አንቺ የቤቴ በረከት ነሽ። ልጅሽም የነፍሴ እረፍት ነው። ንዒ በሚል ዝማሬ አንቺን እጠራሻለሁ።

እርግጥ ነው ልጅሽን ይዘሽ ወደኔ ስትመጪ እንደ ቤተልሔም የእንግዶች ማረፊያ የኔም ልብ የብዙ እንግዳ ኃጢአቶች ማደሪያ ነውና ልጅሽን ለማስተኛት ቦታ የለኝም ብዬ የልቤን በር ልዘጋብሽ እችላለሁ።

በሩን ብዘጋውም ግን ልጅሽ ከደጅ ቆሞ "በሩን ማንኳኳት" እንደማይሰለቸው አውቃለሁ። ራዕ 3:20 እኔ ፈቅጄ ባልከፍትለትም እንኳን የድንግልናሽን ማኅተም ሳይከፍት እነደተወለደ የእኔንም የተዘጋ ልብ ሳይከፍት መግባት አይሳነውም።

ስለዚህ አመፄና እንቢታዬን ቸል ብለሽ ለልጅሽ ማደሪያ አድርጊኝ። አንቺ እርሱን ከወለድሽ ወዲያ በታተመ ድንግልናሽ ጸንተሽ እንደኖርሽ ለልጅሽ ማደሪያ ሆኜ ለሌላ የኃጢአት ጽንስ ዳግም ማደሪያ አንዳልሆን ነፍሴን አትሚልኝ።

ድንግል ሆይ አንቺን ያሳደደሽ ሔሮድስ እኔን የማያሳድደኝ ልጅሽ በእቅፌ ስለሌለ ነው። እኔ በልቤ ያነገሥኩት " የተወለደውን የአይሁድ ንጉሥ" አይደለምና ከሔሮድስ ምንም ጠብ የለኝም። አሁን ግን ፍቀጂልኝና ሔሮድስን ማስደሰት ትቼ ልጅሽን በልቤ ልቀበለው።

በሬን ለዘጋሁት ለእኔ እናቴ ሆይ ልጅሽን በሬን ሲያንኳኳ ሳልከፍት እስካሁን ለዘገየሁት የንጉሡ እናት ሆይ አሳስቢልኝ።

ቅድስት ሆይ ለምኚልኝ