Get Mystery Box with random crypto!

#በ ጁመአው ለይል ሹክ ልበላችሁ አዘጋጅና ፀሀፊ ፦ ካሊድ (kalido ye umi) የዋሻው | ካሊድ ታረቀኝ(ye umi) official

#በ ጁመአው ለይል ሹክ ልበላችሁ

አዘጋጅና ፀሀፊ ፦ ካሊድ (kalido ye umi)

የዋሻው እግረኛ እንዴት ነው ሷሂቡ

ቁረይሾች ነብዩን ﷺ ለመግደል የመጨረሻ በዳይ ውሳኔ ላይ በደረሱበት ወቅት ጅብሪል የቁረይሾችን ሴራ በወህይ አሳወቃቸው። አላህ እንዲሰደዱ መፍቀዱንም አበሰራቸው።

የአላህ መልእክተኛ ﷺ በ14ኛው ዓመተ ነብይነት በወርሃ ሶፈር 27ኛው ሌሊት ማለትም ሴፕቴምበር 12/13_622 ቤታቸውን ለቀው ወደ ባልንጀራቸው አቡበክር ቤት ሄዱ። አቡበከር ከርሳቸው ዘንድ ለጉዞ ጓደኝነት ከማንም በላይ ታማኝ፣ ገንዘባቸውንም ለመሰዋት ዝግጁ ነበሩ። ከ አቡበክር ቤት በጓዳው በኩል በመውጣት ጎህ ሳይቀድ በፊት መካን በፍጥነት ለቀቁ።

ቁረይሾች ለፍለጋ እንደሚሰማሩና መጀመሪያ የሚያስቡት ወደሰሜን አቅጣጫ የተዘረጋውን የመዲና ዋነኛ መንገድ መሆኑን ነቢዩ ﷺ በመረዳታቸው በስተደቡብ በኩል ወደ የመን የሚያደርሰውን መንገድ ይዘው ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ተጓዙ።በዚህ መንገድ 5 ማይሎች ያህል ተጉዘው "ሰውር" ከተባለው ተራራ ደረሱ። ትልቅና መንገዱም አስፈሪ፣ ድንጋያማና አስቸጋሪ ነው። በጉዞው ምክንያት የመልእክተኛው እግር ቆሰለ። ቁስላቸውን ለመደበቅ በእግራቸው ጫፍ ይጓዙ እንደነበር ይነገራል።

ከጋራው ሲደርሱ አቡበክር ተሸከሟቸው። በከፍተኛ ድካምም ከተራራው ጫፍ ወዳለ ዋሻ አደረሷቸው። የዚህ ዋሻ ስም በታሪክ ጸሐፍት ዘንድ "ጋር ሰውር" (ሰውር ዋሻ) በመባል ይታወቃል።

ከዋሻው አጠገብ ደርሰው ሊገቡ ሲሉ አቡበክር፦ "እኔ ከመግባቴ በፊት አይገቡም። አንዳች መጥፎ ነገር ቢኖር እንኳ እርስዎን ሳይሆን እኔን ይጉዳኝ።"በማለት ወደ ውስጥ ዘለቁ።

ከጎኑ ሦስት ሽንቁሮች አዩ። ሽርጣቸውን በመቅደድ አንዱን ደፈኑት። ሁለቱን በእግሮቻቸው ደፈኗቸውና መልእክተኛውን "ይግቡ" አሏቸው። "የአላህ መልእክተኛ ﷺ ገቡና የአቡበክርን ጭን ተንተርሰው ጋደም አሉ። ወዲያውም እንቅልፍ አሸለባቸው። በዚህ መሀከል አቡበክርን እግራቸውን አንዳች ነገር ነደፋቸው። ነብዩ ﷺ ከእንቅልፍ እንዳይነቁ በመስጋት አልተንቀሳቀሱም ነበር። በስተመጨረሻም ከአይናቸው የሚወርደው እንባ ከነቢዩ ﷺ ፊት ላይ ሊያርፍ ቻለ። ነቢዩም፦ እንባው ቢያገኛቸው "አቡበክር ሆይ ምን አገኘህ?" በማለት ጠየቋቸው። "አንዳች ነገር ነደፈኝ፣ ወላጆቼ ለርስዎ መስዋእት ይሁኑ" አሉ። የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከተነደፉበት ቦታ ላይ ተፉላቸው። ሕመሙ ወዲያውኑ ለቀቃቸው።

በዚህ ዋሻ ውስጥ ሦስት ሌሊቶችን ፣ማለትም ጁመዓ፣ ቅዳሜና እሁድ ሌሊት ፣አሳለፉ። አብደላህ ቢን አቡበክር ከነርሱ ጋር ያድር ነበር። አኢሻ እንዳሉት አብደላህ ብልህ ወጣት ነበር። ከነርሱ ጋር አድሮ ጎህ ከመቅደዱ በፊት ወደ መካ በመመለስ እዚያው ያደረ መስሎ ይተኛል። መካውያን የሚነጋገሯቸውን ጉዳዮች ሁሉ ይዞም መሸትሸት ሲል ወደነርሱ በመሄድ ያደርስላቸዋል። የአቡበክር አገልጋይ ዓሚር ቢን ፈሒራህ የሚታለቡ ፍየሎችን ምሽት ላይ ይወስድላቸዋል። እነርሱም በቂ ወተት ያገኛሉ። ጎህ ከመቅደዱ በፊትም ይዟቸው ይመለሳል። በነዚህ በሦስት ሌሊቶቹ ያለማቋረጥ ይህን ያደርግ ነበር። አሚር ፍየሎችን ይዞ አብደላህ ቢን አቡበክር እስከ መካ ድረስ በመከተል ኮቴውን ያጠፉለት ነበር።

የአቡበክርና የነቢዩ መሰውር ያንገበገባቸው ቁረይሾች አስቸኳይ ስብሰባ በመቀመጥ ሁለቱን ለመያዝ የሚያስችላቸውን የትኛውንም መንገድ ለመጠቀም ወሰኑ። ወደ መካ የሚያደርሱ ጎዳናዎችን ሁሉ በጥብቅ የመሳሪያ ጥበቃ ስር አዋሉ። ሁለቱንም በሕይወት ወይም ገድሎ ወደ መካ ለሚያመጣ ማንኛውም ሰው ስለእያንዳንዳቸው መቶ ግመል ሽልማት ለመስጠት ቃል ገቡ። በዚህ ጊዜ ፈረሰኞች፣ እግረኞችና የኮቴ አዋቂዎች በፍለጋ ላይ ተሰማሩ። ጋራዎችን ፣ሸንተረሮችን ፣ሸለቆዎችንና ሜዳዎችን ሁሉ አሰሱ።ግና ድካማቸው ፍሬ አልያዘም። ያለ ውጤት ተመለሱ።

ነገር ግን አሳዳጆች ከዋሻው በር ላይ መድረስ ችለው ነበር። ግና አላህ ፈቃዱን ፈጻሚ ነው። ቡኻሪ አነስን በመጥቀስ እንደዘገቡት አቡበክር እንዲህ ብለዋል፦

ከነቢዩ ﷺ ጋር ከዋሻው ውስጥ ነበርኩ። ራሴን ቀና ሳደርግ የሰዎችን እግሮች አየሁ። "የአላህ መልእክተኛ ሆይ፡ ከመካከላቸው አንዱ ወደ ታች ቢመለከት ያየናል።" አልኳቸው። "አቡበክር ሆይ ፣አይዞህ ፣ አላህ አብሮን አለ።" አሉ።

በሌላ ዘገባም፦ "አቡበክር ሆይ ፡አላህ ሦስተኛ አብሯቸው ያለ ፡ሁለት ሰዎችን ምን ክፋት ያገኛቸዋል ብለህ ታስባለህ?" ብለዋል።

በዚህ ጊዜ አላህ ነቢዩን ﷺበተአምር አዳናቸው። አሳዳጆቻቸው ከርሳቸው ለመድረስ ጥቂት እርምጃዎች ሲቀሯቸው ትተዋቸው ተመለሱ።

ፍለጋው ጋብ ሲል በቁረይሾች የገነፈለው የብቀላ ስሜታቸው ሲሰክን የአላህ መልእክተኛ ﷺእና ባልንጀራቸው ወደ መዲና ለመጓዝ ተዘጋጁ።

{ፊዳከ ነፍሲ ኡሚ ወ አቢ ያረሱለላህ}

ሳምንት በአላህ ፍቃድ በሌላ ፅሁፍ እመለሳለሁ !

መልካም ኸሚስ (የጁመዓ ለይል) ውዶቼ

join @kalidoyeumi