Get Mystery Box with random crypto!

በገና አባት የተሸፈነ ቅዱስ አባት +++ቅዱስ ኒቆላዎስ ገባሬ መንክራት (St.Nicholas | JUSTIN APOLOGETICS]

በገና አባት የተሸፈነ ቅዱስ አባት

+++ቅዱስ ኒቆላዎስ ገባሬ መንክራት (St.Nicholas the wonder worker)+++

ቅዱስ ኒቆላዎስ (St.Nicholas-Santa Claus) በሮማ መንግስት ዘመን በኤዥያ ውስጥ በምትገኝ ሜራ በምትባል አገር (የአሁኗ ቱርክ) ግሪካዊ ከሆኑ ክርስቲያን ቤተሰቦቹ ተወለደ፡፡ የዚህም ቅዱስ እናቱ ጦና (Tona) አባቱ ኤጲፋንዮስ ይባላሉ፡፡ እኒህም እግዚአብሔርን የሚፈሩና ባለጠጎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከሞቱ በኋላ ንብረታቸውን የሚያወርሱት፣ ለልባቸውም ደስታን የሚመግብ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ዕድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱም ምክንያት በተስፋ መቁረጥ ተከበው ይኖሩ ነበር፡፡ በልብ መታሰቡ በቃል መነገሩ ከፍ ከፍ ያለ አምላክ በእርጅና ዘመናቸው ልክ ጻድቁ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥን እንደጎበኘ እነርሱንም በቸርነቱ ጎበኛው፡፡ ቅዱስ የሆነም ልጅን ሰጣቸው፡፡ ይህም ልጅ ገና ታናሽ ሳለ መንፈሰ እግዚአብሔር የሞላበት ነበር፡፡ ዕድሜውም ለትምህርት በደረሰ ጊዜ ዕውቀትና ጥበብን ይቀስም ዘንድ ወደ መምህራን የተላከ ቢሆንም፣ ከመምህሩ ከተማረው ይልቅ ከመንፈስ ቅዱስ የተረዳው ይበልጥ ነበር፡፡

መሠረታዊ የሆኑትን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በልጅነቱ ተምሮ በማጠናቀቁ በዲቁና መዓርግ ተሾመ፡፡ በኋላም የአጎቱ ልጅ አበምኔት በሆነበት በአንዱ ገዳም አርዑተ ምንኩስናን (የምንኩስናን ቆብ) ጭኖ የቅድስና እና የትሕርምት ሕይወትን ኖሯል፡፡ በአሥራ ዘጠኝ ዓመቱም የቆሞስነትን መዓርግ አግኝቷል፡፡

ለዚህም ቅዱስ አባት እግዚአብሔር ተአምር እና ድንቅን የማድረግ ፤ሕሙማንንም የመፈወስ ታላቅ ጸጋ ሰጥቶታል፡፡

#ለጋስ (የስጦታ) አባት

በሜራ ከተማ የሚኖር ቀድሞ ባለጠጋ የነበረ በኋላ ግን ሃብት ንብረቱን ያጣ አንድ ሰው ነበረ፡፡ በድህነቱ ምክንያት ሊድራቸው ያልቻለ ሦስት ዕድሜያቸው ለጋብቻ የደረሱ ሴቶች ልጆች ነበሩት፡፡ ሰይጣንም እነዚህን ልጆቹን በዝሙት ሥራ ገንዘብ እየሰበሰቡ ሕይወታቸውን እንዲመሩ ያደርጋቸው ዘንድ ክፉ ሐሳብን በሕሊናው አመጣበት፡፡ እግዚአብሔርም በዚህ ሰው ልቡና ውስጥ ሰይጣን የተከለበትን ክፉ ሐሳብ እና ምን ሊያደርግ እንደተነሣሣ ለቅዱስ ኒቆላዎስ ገለጠለት፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም የእናት የአባቱ ገንዘብ ከሆነው ላይ መቶ ዲናር ወስዶ በስልቻ (sack) ጠቅልሎ ማንም ሳያየው በምሽት ወደዚያ ደሃ ሰው ቤት በመሄድ በመስኮት በኩል ወረወረለት፡፡ ያም ደሃ ከየት እንደመጣ ያላወቀውን 100 ዲናር በቤቱ ባገኘ ጊዜ ተደነቀ አምላኩንም አመሰገነ፡፡ ያሰበውንም ክፉ ሐሳብ ተወ። በገንዘብ እጦት ምክንያትም ከትዳር የዘገየችውን የመጀመሪያ ልጁን ዳረ፡፡ በሌላም ቀን ቅዱስ ኒቆላዎስ ሁለተኛ ልጁን መዳር ይችል ዘንድ፣ አሁንም ተጨማሪ መቶ ዲናር ገንዘብ በጥቅል ስልቻ አድርጎ በመስኮቱ በኩል ወረወረለት፡፡ ይህንንም ገንዘብ ዳግመኛ በቤቱ ያገኘው ደሃ ሰው እንዲህ ያለውን ቸርነት በስውር የሚያደርገው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ አይቶ ያውቅ ዘንድ ጉጉት አደረበት፡፡ ቤቱንም በንቃት መከታተል ጀመረ፡፡

ቅዱስ ኒቆላዎስም እንደ ለመደው ለሦስተኛ ጊዜ መቶውን ዲናር የያዘውን ስልቻ በመስኮት ሲወረውር ወዲያው ተዘጋጅቶ ይጠብቀው የነበረው ሰው ፈጥኖ በሩጫ ከቤቱ ወጣ። ሊያየው ይመኘው የነበረ ያንንም ቸር ሰው ሊቀ ጳጳሱ ኒቆላዎስ ሆኖ አገኘው፡፡ ከእግሩ ስርም ተደፍቶ ልጆቹን ከድህነት እና ከኃጢአት ሕይወት ስለታደገለት ሊያመሰግነው ቢሞክርም ቅዱስ ኒቆላዎስ ግን ምስጋናውን እምቢ አለ፡፡ ይህን ሐሳብ በልቡ ያኖረ እግዚአብሔርንም ያመሰግን ዘንድ ለመነው፡፡

ከዚህ ታሪክ በተጨማሪም ለሕፃናት እና ለተቸገሩ ሰዎች ያደረገው ልግስና የብዙ ብዙ ነው። ለዚህም ይመስላል በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት መታሰቢያውን በልግስና የሚያከብሩት።

በአጠቃላይ ይህ ቅዱስ አባት በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ስለ እምነቱ ብዙ ስቃይ እና እስራት ደርሶበታል፡፡ ፋታ በማይሰጥ መከራ እና ግርፋት ውስጥ እያለ የራሱን ሕመም ከማዳመጥ ይልቅ በውጪ ላሉ ለልጆቹ ምዕመናን የሚያበረታታ እና በእምነታቸው እንዲጸኑ የሚያደርግ መልእክትን ይጽፍላቸው ነበር፡፡ ቅዱስ ኒቆላዎስ በ325 ዓ.ም ለአውግዞተ አርዮስ ከተበሰቡት 318ቱ ሊቃውንት መካከል አንዱ የነበረ የዚህች ኦርቶዶክሳዊት እምነት ባለውለታ ነው፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ በሊቀ ጵጵስና መንበር በጎቹን ከነጣቂ ተኩላ እየጠበቀ ቤተ ክርስቲያንን ካገለገለ በኋላ በሰማንያ ዓመቱ አርፏል፡፡

(ቅዱስ ኒቆላዎስ በእኛ (በኢትዮጽያ) የስንክሳር መጽሐፍ ላይ የእረፍቱ መታሰቢያ የሚያዝያ ወር በገባ በአስራ አምስተኛው ቀን እንደሆነ ተመዝግቧል፡፡ ኒቆላዎስም ማለት ‹መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ› ማለት ነው።)

የልደት በዓል እግዚአብሔር አብ ልጁን ለዓለም የሰጠበት በመሆኑ ‹የሥጦታ በዓል› በመባል ይጠራል፡፡ ይህንንም በማሰብ ለድሆች በመራራት ለተቸገሩት ቸርነት በማድረግ እናከብረው ዘንድ ምሳሌ እንዲሆነን ቅዱስ ኒቆላዎስን እናስባለን፡፡ ምንም ዓለም አፈ ታሪክ አድርጋ ብታወራውም፣ የዚህንም ቅዱስ ማንነት እንዳይታወቅ በፈጠረቻቸው ተረቶች ብታጠለሸውም እኛ ግን የ‹ገና አባት› ብላ ከሰየመቻቸው የፈጠራ ሰው ጀርባ እውነተኛ የሆነውን ይህን ቅዱስ አባት እናስበዋለን፡፡

+++++ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛ ኃጢአተኞቹንም በዚህ ጻድቅ ሰው ጸሎት ይማረን!!!+++

ምንጭ:– -መጽሐፈ ስንክሳር
-Coptic synaxarium

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
selam@dnabel.com