Get Mystery Box with random crypto!

ነፍስ ስታፈቅር ምዕራፍ -21 ደራሲ ዘሪሁን ገመቹ // ሄኖክ ነገሮች ሁሉ ከእቅድና ከቁጥጥሩ | ✍ ልብ ወለድ በፅዮን ✍ fiction ❤️😘

ነፍስ ስታፈቅር
ምዕራፍ -21

ደራሲ ዘሪሁን ገመቹ

//
ሄኖክ ነገሮች ሁሉ ከእቅድና ከቁጥጥሩ ውጭ እያፈተለኩ ተቸግሯል።‹‹ፊት ለፊት ተቃጥረውና ተዘጋጅተው የሚገጥሙት ጠላት እንዴት የተባረከ ነው›› አለ.‹‹.እኔ ነኝ እንጂ ከመንፈስ ጋር ድብብቆሽ የምጫወት"ሲል ተማረረ......አሁን ቢላል እስኪገኝና በቀጠራቸው ሰዎች እስኪያስገድለው ድረስ ዝም ብሎ እያማረረ ከሚቀመጥ መስራት የሚችለው አንድ ነገር እንዳለ ተሠማው....ከሲፈን ጋር ያለውን የሻከረ ግንኙነት ማለስለስ...አዎ ይሄ ሁሉ ፈተናና ውጣ ውረድ እሷን የራሱ ለማድረግ ነው...ከሰሞኑ ደግሞ በመካከላቸው በተፈጠረ ተደጋጋሚ ግጭት እና መፋተግ የተነሳ በጣም እንደተራራቁ ይሰመዋል ..ደግሞም ተራርቀዋል፡፡:ስልኩን እንኳን ማንሳት ካቆመች ቀናቶች አልፈዋል...፡፡ይሄም ቢሆን ግን በህይወቱ ሌላ ጥሩ ዜና አልጠፋም. …ከእሷ አባት ጋር ተዋውቀዋል..ከዛም አልፈው እሷን በተመለከተ ሊመካከሩና መፍትሄ ሊያበጅ ከሶስት ጊዜ በላይ በአካል ተገናኝተው አውርተዋል...በእሷ ላይም ዶልተዋል።ይሄንን ጉዳይ እሷ ፈፅሞ አታውቅም።
እና ለሄኖክ ከሲፈን ጋር ቀለበት ካሠረበት ቀን ብኃላ የገጠመው አንድ መልካም ነገር ከአባትዬው ጋር የፈጠረው መግባባትና በመተባበር ለአንድ አላማ አብሮ መስራት መቻሉ ብቻ ነው፡፡..እና አሁን ከሲፈን ጋር የተፈጠረውን መሻከር ለማለዘብ ሽማግሌ በሚቀጥለው እሁድ መላክ አለበት ..ይሄ የእሱ ብቻ እቅድ አይደለም የሲፈን አባትም ምክር አለበት...ክፍሉን ለቀቀና ወደ አባቱ ክፍል አመራ...አንኳክቶ ገባና ቀጥታ ወደጉዳዩ ገባ
"አባዬ በዚህኛው እሁድ ሌላ ኘሮግራም እንዳይዙ ለሽማግሌዎቹ ደውልና ቀድመህ አሳውቃቸው"
‹‹እሺ..እደውልላቸዋለው..አንተ አታስብ"
‹‹እሺ አባዬ አመሰግናለው"አለና እንደአመጣጡ በፍጥነት ፊቱን አዙሮ ሊሄድ ሲል "ሄኖኬ"ጠሩት
‹‹አቤት አባዬ››
አንድ ነጭ ፓስታ አቀበሉት‹‹ምንድነው አባዬ?››
‹‹አላወቅኩም...ሲፈን ነች የላከችልህ"
የሲፈንን ስም ሲሰማ ጊዜ አላጠፋም …ተስገብግባ የመንጠቅ ያህል ከአባቱ እጅ ፓስታውን ተቀበለና ወደክፍሉ ተንደረደረ….ገባና መቀመጥ እንኳን ሳይሞክር ፓስታውን ከፈተው..ውስጡ ያለውን ወረቀት ሲያወጣ የሆነ ነገር ተስፈንጥሮ ወለሉ ላይ ወደቀ...አይኑን የወደቀው ነገር ምንነት ለማወቅ አንከራተተ..ኪሊሊሊሊሊ እያለ የሚሽከረከረው ጥቂት አንፀባራቂ ብረት ነው..ጎንበስ ብሎ አነሳው. ቀና ማለት ከበደው ፡፡ከወገብ ላይ የሆነ ደም ስር ጧ ብሎ የተበጠሰ መሠለው...፡፡እጅ ላይ ያለው ቀለበት ነው..፡፡ሲፈን ጣቶች ላይ በደስታ በሰከረ መንፈስ ውስጥ ሆኖ በኩራት ያጠለቀላት ውድ ባለ አልማዝ ፈርጥ ቀለበት..
‹‹.እስከወዲያኛው አልፈልግህም እያለቺኝ ነው"ሲል ድምፅ አውጥቶ ጨኸ.."እገድላታለው...የእኔ ካልሆነች የማንም አትሆንም...መሞት አለባት….ቢላል የተባለው ጂል ተሳክቶለት ባይገድላት እንኳን እኔ አለቃትም"...ወሰነ
/// ሲፈን
በመከራ ስትገላበጥ ቆይታ ነው እንቅልፍ የወሰዳት...‹‹ ከመቼው ነጋና ነው የሚቀሰቅሱኝ...?ደግሞስ ለምን ይቀሰቅሱኛል..?.ምን ተፈጠረ.?.›ስትል አጉተመተመች፡፡እንደምንም ተንጠራራችና አይኖቾን አጨንቁራ ከፈተች..... እባብ እንደተጠመጠመበት ሰው ጆሮ ሰንጣቂ ጩኸቷን ለቀቅችው…. ከአ
ልጋው ተስፈንጥራ በመውረድ ወለሉ ላይ በባዶ እግሯ ቆመች….በአንድ ሜትር ርቀት ፊት ለፊቷ ተገትሮ ቆሟል...ጩኸቷን የሠሙት እናቷና ሰራተኛዎ እየተጋፍ መጥተው በራፍን በማንኳኳት ላይ ናቸው፡፡
"ልጄ ሰላም ነሽ..?"
"በራፍን ክፈቺ"
ሲፈን በቆመችበት ወደበራፍ አይኖቾን ላከች. ….እንደተቀረቀረ ነው ‹‹...ታዲያ በየት ገባ?›እራሷን ነው ምትጠይቀው
"እማዬ ሰላም ነኝ ...ቃዠቼ ነው።"
"እኔን ልጄ..ምነው አመመሽ እንዴ?"
"ደህና ነኝ እማዬ"
"ክፈቺልኝና አብሬሽ ልተኛ"
"እማዬ...ሠላም ነኝ አልኩሽ እኮ..አሁን ሂጂና ተኚ ..እኔም ልተኛበት"
"እሺ ካልሽ ልጅ ..ደህና እደሪ ...ከፈለግሺኝ ጥሪኝ ወይም ደውይልኝ"
"እሺ እማዬ.."
.የእግራቸው ኮቴ እየራቀ ሲሄድ ሰማች….ዘላ ተጠመጠመችበት...እያገላበጠች ሳመችው..ግንባሩን ..ጉንጩን ..ከንፈሩን ምንም አልቀራትም...አዎ ህልም አይደለም ሰውነቱን እየዳበሰችው ነው..ጠረኑን ወደውስጧ እየማገችው ነው፡፡ከራሷ አራቀችውና መላ ቁመናውን መረመረችው ...ድባይ ወይም አውስትራሊያ ለእረፍት ሰነባብቶ የመጣ ነው የሚመስለው።ጉንጮቹ ሞልተዋል ..ፊቱ ጠርቷል...ጥርሶቹ እንደበፊቱ ፍፅም ነጭ ናቸው...አለባበሱ ዝንጥ እንዳለ ነው፡፡
"እዚህ ክፍል እንዴት ገባህ...?ዘበኛቹን በምን አስማት አለፍካቸው?የሳሎኑን በር ማን ከፈተልህ?ይሄንንስ ክፍል እንዴት?"ማለቂያ የሌለው ግትልትል ጥያቄ፡፡
ወደ ላይ አይኑን አንጋጠጠ..ወደኮርኒሱ እሱን ተከትላ እሷም አንጋጠጠች"ዉይ በፈጣሪ ...አንተ ማፍያ ነበርክ እንዴ ?" ከበላዩ ያለው ኮርኒስ ሆነ ከእሱ በላይ ያለው ቆርቆሮ ሰው ሊያሾልክ በሚችል መጠን በክብ ተቀርፎ ወጥቷል..ቀጥታ ሰማዩ ላይ የተንጠባጠብት ደማቅና ደብዛዛ ኮከቦች ጭምር በጥራት ይታያሉ።
እስከአሁን እራሷም ቆማ እሱንም አቁማ መሆኑን ስታስታውስ ጎተተችና አልጋው ጠርዝ ላይ አስቀመጠችው...
‹‹ሰላም ነህ ግን..?.ውዴ አንተን ለመፈለግ እኮ ያላስበረበርኩት የአዲስአባ ጥግ አልነበረም...ምነው እንዲህ ጨከንክብኝ..?.እኔስ ይሁን እንዴት በእናትህ እንዲህ ልትጨክን ቻልክ....?በጣም ነው አኮ ውስጤን ያሰቃየኸኝ...፡፡ልቤ እስኪደክማት ድረስ...አእምሮዬ እንዴት እንደሚታሰብ ግራ እስኪገባው ድረስ....ማን መሆኔ ሁሉ እስኪጠፋኝ ድረስ ነው የተሰቃየውብህ...››ከአንጀቷ ያለምንም ይሉኝታ የውስጧን አውጥታ ተናዘዘችለት፡፡
"እንግዲያው ባለውለታሽ ነኛ"
‹‹እንዴት ማለት የእኔ ውድ?"
‹‹እንዲህ ከስርሽ ርቄ ባልጠፋ ስለእኔ እንዲህ አይነት ስሜት እንደሚሰማሽ ማወቅ አትቺይም ነበር"
"እሱስ እውነትህን ነው....በጣም እንደማፈቅርህ አሁን መናዘዝ አለብኝ"
"ግን እኮ ሌላ ሰው ልታገቢ ነው?"
"እሱን አሁን እርሳው....ደግሞም እኮ አንተም ልትገድለኝ እቅድ አለህ?"
"ያ እቅድ የእኔ አይደለም ...የአማልክቱ ነው....እስከአሁንም የውሳኔ ለውጥ መኖሩን አላውቅም"ኮስተር ብሎ ነው እንዲህ ሚላት።
"ጉዳዬ አይደለም...አንተ የሌለህበት ኑሮም ያው ከሞት አንደማይለይ በሰሞኑ ሁኔታዬ አረጋግጬያለው... ለማንኛውም ስትገባ ዘበኞቹ እንዳላዩህ እርግጠኛ መሆን አለብኝ..በራፍን ከውጭ ቆልፌብህ ሄዳለው ...እስከዛ ሻወር መውሰድ ትችላለህ"
"አዎ መታጠብ ፈልጋለው..ለራስሽ እርግጠኛ ለመሆን ሂጂ....ስገባ ማንም ሊያየኝ እንደማይችል ግን እርግጠኛ ነኝ"
"እንደዛ ከሆነ ደስ ይለኛል...ለማንኛውም መጣው"አለችና በለበሰችው ስስ ቢጃማ ላይ ወፈር ያለ ጋወን ደርባበት እንዳለችውም ክፍሉን ከውጭ ቆለፈችና በዝግታ እየተራመደች ወደሳሎን አመራች...ከውስጥ እንደተቆለፈ ነው… ቀስ ብላ ከፈተችውና ወደውጭ ወጣች...ሁሉ ነገር ፀጥ ብሏል..ዘበኞቹ በንቃት የበራፍን ግራና ቀኝ ይዘው ሁለቱም ዘመናዊ ክላሻቸውን ሰድረው ከወዲህ ወዲያ ይንጎራደዳሉ፡፡